የሚኒያፖሊስ ከተማ ምክር ቤት የከተማውን ፖሊስ ለመበተን ቃል ገባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚኒያፖሊስ ከተማ ምክር ቤት የአካባቢውን ፖሊስ ጣቢያ ለመበተን ቃል ገቡ።
በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ምክንያት በአሜሪካና በመላው ዓለም የተቀሰቀሰውን ከባድ ተቃውሞ ተከትሎ አብዛኛዎቹ የሚኒያፖሊስ ከተማ ምክር ቤት አባላት የከተማውን ፖሊስ እንዲ በተን ጠየቁ።
ከአስራ ሦስቱ የምክር ቤት አባላት ዘጠኙ በዚህ ሀሳብ የተስማሙ ሲሆን “አዲስ የማኅበረሰብ ደኅንነትን የሚያስጠበቅ ሞዴል’’ ይፈጠራል ብለዋል።
ተመሳሳይ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ብለው ለዓመታት ሲከራከሩ የነበሩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ደግሞ ውሳኔውን "ወሳኝ ጅማሮ ነው" ብለውታል።
በፖሊስ እጅ የጆርጅ ፍሎይድ ሕይወት ማለፉ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የፖሊስ ጭካኔ ይቁም ያሉ በርካታ አሜሪካውያን ከባድ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
የተቃውሞ ሰልፎቹ ቀስ በቀስ መቀዛቀዛቸውን ተከትሎ ተቀምጠው የነበሩት ጥብቅ የደኅንነት እርምጃዎች ከእሁድ ዕለት ጀምሮ እንዲነሱ ሆኗል።
ዛሬ ደግሞ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጆርጅ ፍሎይድን አስክሬን ለመሰናበት በሂውስተን እንደሚሰባሰቡ ይጠበቃል። ፍሎይድ ወደ ሚኒሶታ፣ ሚኒያፖሊስ ከመሄዱ በፊት መኖሪያ ቤቱ የሚገኘው ቴክሳስ ሂውስተን ነበር።
ነገ ማክሰኞ ደግሞ ቤተሰብ ብቻ በተገኘበት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንደሚፈጸም ታውቋል።
የጆርጅ ፍሎይድ የመጨረሻ ሰዓት ትንቅንቅ በቪዲዮ ተቀርጾ ማኅበራዊ ድር አምባው በከፍተኛ ፍጥነት ከተጋራው በኋላ በአሜሪካ አብዛኞቹ ግዛቶች ለቀናት የዘለቀ ተቃውሞን ቀስቅሶ ቆይቷል።
ተቃውሞቹን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋትም ሆነ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊያቆማቸው አልቻለም ነበር።
ለጆርጅ ፍሎይድ ደማቅ የሽኝት ሥነ ሥርዓት የተደረገለት ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ሲሆን በርካታ ስመ ጥር የጥቁር መብት ተሟጋቾች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር አድርገዋል።
የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቃ "ደንበኛዬን ለሞት ያበቃው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው ይላሉ፤ በዘረኝነት ወረርሽኝ መሞቱን ማን በነገራቸው. . ." ሲል ስሜታዊ ንግግር አሰምቷል።
በሟች ጆርጅ ፍሎይድ የሽኝትና መታሰቢያው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ሁሉ ተነስተው እንዲቆሙና ለ8 ደቂቃ ከ46 ሴኮንዶች የሕሊና ጸሎት እንዲያደርጉ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም ነጩ የፖሊስ ባልደረባ ዴሪክ ሟች ፍሎይድ አንገት ላይ በጉልበቱ ቆሞ ትንፋሹን እስኪያጣ የቆየበትን ጊዜን ለመዘከር የተደረገ ነበር።
"አሁን ያለንበት ሁኔታ ላይ እራሳችንን ያገኘንበት ምክንያት በሚኒያፖሊስና በአጠቃላይ አሜሪካ የተዘረጋው የፖሊስ መዋቅር የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ነው" ብለዋል የከተማ ካውንስሉ ፕሬዝደንት ሊሳ ቤንደር።
ፕሬዝዳንቷ አክለውም የፖሊስ ጣቢያውን እንዴት እንደ አዲስ ማዋቀር እንደሚቻል በቅርቡ እቅድ እንደሚዘጋጅ የገለጹ ሲሆን፤ ለፖሊስ ይመደብ የነበረ ገንዘብ ወደ ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ለማዞር እንደሚጥሩም ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የሚኒሶታ ግዛት የሚኒያፖሊስ የፖሊስ ክፍል ላይ ምርመራ እንዲጀመር አድርጓል። የከተማዋ ገዢ ቲም ዋልትዝ በበኩላቸው በተጠና መልኩ የሚደረጉ የዘረኝነት ተግባራትን ማስወገድ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ምርመራውን እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የከተማ ምክር ቤት በፖሊስ ተግባራት ላይ በርካታ ለውጦች እንዲኖሩ የወሰነ ሲሆን፤ በዋነኛነት ተጠርጣሪዎችን ማነቅና አንገት ላይ በጉልበት መቆምን ከልክሏል።
በሚኒያፖሊስ ተግባራዊ የሚሆነው ሕግ በመላው አሜሪካ ፖሊስ እስከ ምን ድረስ ነው ኃይሉን መጠቀም አለበት የሚለውን ጥያቄ በድጋሚ አስነስቷል።
በሚኒሶታ አንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅት የሚመሩት ካንዲስ ሞንትጎመሪ "ውሳኔው እስኪታላለፍ ድረስ ይህን ያክል ጊዜ መቆየት አልነበረበትም፤ የታጠቁና ተጠያቂነት የሌለበት እርምጃ የሚወስዱ ፖሊሶች ባሉበት ጥቁር አሜሪካውያን ደህንነት አይሰማቸውም" ብለዋል።












