በአሜሪካ በርካታ የፖሊስ አባላት ሥራቸውን ለቀቁ
የጭካኔ ተግባር ፈጽመዋል የተባሉ ሁለት ባልደረቦቻቸው ያለደሞዝ እረፍት እንዲወጡ መደረጋቸውን በመቃወም መኮንኖቹ የነበሩበት የነበሩበት ቡድን አጠቃላይ ሥራ አቁሙ።
ሐመስ ዕለት በስፋት በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ በኒውዮርክ ግዛት ቡፋሎ በተባለ ከተማ ውስጥ የፖሊስ መኮንኖቹ አንድ አዛውንትን ገፍትረው ወደ መሬት ሲጥሏቸው ታይቷል።
የፖሊስ መኮንኖቹ አፍሪካ አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በአንድ ፖሊስ መተንፈስ እስኪያቅተው ድረስ አንገቱ ላይ በጉልበቱ ቆሞ ከተገደለ በኋላ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማርገብ የተጣለውን ሰዓት እላፊ ለማስከበር በአካባቢው በተሰማሩበት ወቅት ነበር ጉዳቱ ያጋጠመው።
በዚህም ሳቢያ የ75 ዓመቱ አዛውንት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ድርጊቱን ተከትሎም ሁለት ፖሊሶች ከሥራ የታገዱ ሲሆን እርምጃውን በመቃወም በአድማ በታኝ ቡድኑ ውስጥ ያሉ ሁሉም 57 አባላት ሥራቸውን ለቀዋል።
ቡፋሎ ኒውስ እንደዘገበው ሁለቱ የፖሊስ አባላት ላይ የተወሰደው እርምጃ ድንገተኛ ምላሽ ከሚሰጠው ቡድን እንጂ በአጠቃላይ ከፖሊስ ኃይሉ እንዳልታገዱ አመልክቷል።
የአካባቢው ፖሊሶች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ጆን ኢቫንስ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ሁለቱ ፖሊሶች በምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሩ የተሰጣቸውን አደባባዩን ከሰዎች እንቅስቃሴ ነጻ የማድረግ ትዕዛዝ ተግባራዊ እያደረጉ ባሉበት ጊዜ ነው ከሰውዬው ጋር ተገናኝተው አደጋው የተፈጠው ብለዋል።
የኒው ዮርክ ገዢ አንድሩ ኩሞ ክስተቱን ተከትሎ ሁለቱ ፖሊሶች ከሥራቸው መባረር እንዳለባቸውና "የወንጀል ክስ ለመመስረት የሚያስችል" ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ጉዳቱ የደረሰባቸው አዛውንት በጎና ላይ በቡድን ሆነው ወደሚጓዙ የፖሊስ አባላት ሲጠጉ ተንቀሳቃሽ ምስሉ የሚያሳይ ሲሆን ፖሊሶቹም መንገድ ለማስለቀቅ እንደገፈተሯቸው ይታያል።
ወድቀው ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰብ ማርቲን ጉጊኖ እንደሚባሉና አሁን ሆስፒታል ውስጥ ሁኔታቸው ከባድ ቢሆንም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንሚገኙ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
አዛውንቱ ለረጅም ዘመናት የማኅበራዊ ፍትሕ ተከራካሪ ሆነው የተለያዩ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችን ሲቃወሙ የነበሩ እንደሆኑ አንድ የመብት ተከራካሪ ቡድን ከክስተቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።













