በአሜሪካ ሰሞኑን በተከሰው ተቃውሞ ወቅት አይፎን ስልክ የሰረቁ እየታደኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ሽፋን በማድረግ አይፎን ስልክ የሰረቁ ዱካቸው እየተደረሰበት ነው።
አሜሪካ ውስጥ ባለፉት ስምንት ቀናት በነበረው ተቃውሞ በአንዳንድ ከተሞች መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የመደብሮችና መጋዘኖች ዝርፍያ ተስተውሎ ነበር።
በዚህ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ካልሲ፣ ጡት መያዣና ዱቄት ሳሙና የዘረፉ ላይደረሰባቸው ይችል ይሆናል። አይፎን የዘረፋችሁ ግን ወዮላችሁ ተብለዋል።
የአይፎን ዘራፊዎች እየታደኑ ስለመሆኑ ኩባንያው በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም በአንዳንድ የተሰረቁ ስልኮች ላይ "የሰረቃችሁትን መልሱ" የሚሉ መልዕክቶች ስለመምጣታቸው ተስተውሏል።
በአንዳንድ በስርቆት በተገኙ ስልኮች ላይ ለምሳሌ "እባክዎ የሰረቁትን ስልክ ይመልሱልን፤ አለበለዚያ ለፖሊስ ያሉበትን እንጠቁማለን" የሚል መልዕክት እየታየ እንደሆነ መረጃዎች ወጥተዋል።
ይህም ከአፕል መደብሮች የተሰረቁ አይፎን ስልኮች በሙሉ ሶፍትዌር የተገጠመላቸው ስለመሆኑ ጥርጣሬን አጠናክሯል።
ስለዚህ ኩባንያው እነዚህን ስልኮች አገልግሎት እንዳይሰጡ እያደረገ ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር ዘራፊዎቹ የት እንዳሉ መጠቆም ሊጀምር ይችላል ተብሏል።
የጆርጅ ፍሎይድ ግድያን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ አፕል በአብዛኛዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ የችርቻሮ መደብሮቹን በጊዜያዊነት ዘግቷቸዋል።
አሁን ግለሰቦች በማኅበራዊ ድረ ገጾች እያጋሯቸው የሚገኙ መልዕክቶች እንደጠቆሙት፤ አፕል ዘራፊዎችን ስልኮቼን መልሱልኝ እያለ በሰረቁት ስልክ በራሱ መልዕክት እየላከላቸው ይገኛል።
በእርግጥም አፕል ይህን እያደረገ ስለመሆኑ ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦለት በእንደዚህ ዓይነት የደኅንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ፖሊሲዬ አይፈቅድልኝም ሲል ተናግሯል።
ለጊዜው ኩባንያው የዘራፊዎቹን አድራሻ ለጸጥታ አስከባሪዎች እያቀበለ እንደሆነ ማረጋገጥ አልተቻለም።
ሆኖም በአፕል መደብሮች የሚሸጡ የአይፎን ስልኮች የያዛቸው ሰው ያለበትን ቦታ የሚያሳብቅ የደኅንነት መተግበርያ እንደተገጠመላቸው ውስጥ ውስጡን ሲወራ ቆይቷል።
አሁን በየማኅበራዊ ድር አምባው እየተጋሩ ያሉ መረጃዎችም ይህንኑ የሚመሰክሩ ናቸው።
በአንድ ግለሰብ የትዊተር ሰሌዳ ላይ የተጻፈ አንድ መልዕክት በአንድ የተሰረቀ አይፎን ላይ የተላከን አጭር መልዕክት ቅጂ ያጋራል። ይዘቱም የሚከተለው ነው፣
"እባክዎ ይህንን የሰረቁትን ስልክ ዋልኖት ጎዳና ላይ ወዳለው የአፕል መደብር ወስደው ይመልሱ። ይህ ስልክ አገልግሎት እንዳይሰጥ ከመደረጉም በላይ ዱካው በጥብቅ ክትትል ሥር ነው። የአካባቢዎ ፖሊስ ያሉበትን እንዲያውቅ ይደረጋል።"
ፊላደልፊያ ውስጥ የአፕል መደብር ለከፍተኛ ዘርፍያ ከተጋለጡት መካከል ይመደባል።
እስካሁን ባለው አሰራር አዲስ የሚገዙ አይፎኖች ገዢው በፍቃዱ መተግበርያውን እስካልጫነባቸው ድረስ ዱካቸውን የሚከታተል ሶፍትዌር አይደረግባቸውም። ነገር ግን ከየትም ቦታ አፕል ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል።
አፕል መደብሮቹን ቀስ በቀስ ወደ ሥራ እያስገባ የነበረ ቢሆንም በዋሺንግተን ዲሲ፣ በሎስ አንጀለስ፣ በሳን ፍራንሲስኮ፣ በኒው ዮርክና በፊላደልፊያ በነበሩ ከፍተኛ ዘረፋዎች ምክንያት እነዚህ መደብሮች ተዘግተው እንዲቆዩ ተደርገዋል።
የአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ ለሠራተኞቻቸው ባሰራጩት የቢሮ ማስታወሻ የጥቁር አሜሪካዊው የጆርጅ ፍሎይድ የግፍ ግድያን "የሚያበሳጭና ስሜት የማይሰጥ" ሲሉ ካወገዙት በኋላ በሰብአዊ መብት ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች አፕል ድጋፍ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።













