"ከአብረሃም ሊንከን ቀጥሎ ለጥቁሮች ውለታ የዋልኩት እኔ ነኝ" ዶናልድ ትራምፕ

ጥቁር አሜሪካዊ የትራምፕ ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በመላው አሜሪካ ለስምንተኛ ቀን ተቃውሞ ተጠናክሮ በቀጠለበት ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ 'ለጥቁር አሜሪካዊያን የሰራሁላት ውለታ ተዘንግቷል' እያሉ ነው።

ከአብራሃም ሊንከን ወዲህ ለጥቁር አሜሪካዊያን እንደኔ ዉለታ የዋለላቸው የለም የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ለጥቁሮች ሥራ በመፍጠር፣ በጥቁሮች የሚፈጸም ወንጀልን በመቀነስ እንዲሁም የጥቁር አሜሪካዊያንን ድህነት በማጥፋት እኔን የሚያህል ሰው ከወዴት ይገኛል? ሲሉ ጠይቀዋል።

ለመሆኑ ዶናልድ ትራምፕ ለጥቁር አሜሪካዊያን ውለታን የዋሉ መሪ ናቸው? ጥቁሮችን በተመለከተ የሚናገሩት ምን ያህል እውነት ነው? ቢቢሲ ንግግራቸውን አንድ በአንድ ፈትሾታል።

1.የአፍሪካ-አሜሪካዊያን ሥራ አጥነት በትራምፕ ዘመን ዝቅተኛ ሆኗል?

የአፍሪካ አሜሪካዊያን የሥራ አጥነት መጠን በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር 16.7 ፐርሰንት ደርሷል። ይህ አሃዝ እንደሚያስረዳው የጥቁሮች ሥራ አጥነት ከመጋቢት 2010 ወዲህ እንዲህ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እንደማያውቅ ነው።

ሆኖም እንዲህ የሥራ አጡ ቁጥር በአንድ ጊዜ የተመነደገው የኮሮናቫይረስ የፈጠረውን ምስቅልቅል ተከትሎ ነው።

የኮሮናቫይረስ መከሰት ደግሞ ከየትኛውም ዘር በላይ ጥቁር አሜሪካዊያን ላይ የከፋ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳትን አድርሷል።

በኮቪድ-19 ምክንያት የጥቁር አሜሪካዊያን ሥራ አጥነት ከየትኛውም ሌላ ዘር ጋር ሲነጻጸር በ2 እጅ ከፍ ያለ ነው።

ያም ሆኖ ግን የጥቁር አሜሪካዊያን የሥራ አጥነት አሃዝ ባለፈው ዓመት መስከረም 5.5 ፐርሰንት ድረስ ዝቅ ማለቱ የሚካድ አይደለም።

ይህ አሃዝ የአገሪቱ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የየወሩን ሥራ አጥነት ደረጃ ይፋ ማድረግ ከጀመረበት እንደ እነርሱ አቆጣጠር ከ1970ዎቹ ወዲህ ዝቅተኛው ነው።

እርግጥ ነው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ወዲህ የጥቁር አሜሪካዊያን የሥራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ እያለ መጥቶ ነበር።

ነገር ግን ሥራ አጥነቱ እየቀነሰ መምጣት የጀመረው ከባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን ጀምሮ ነው።

ባራክ ኦባማ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ከ2009 እስከ 2017 ድረስ ሥራ አጥነቱ ከነበረበት 12.6 ፐርሰንት ወደ 7.5 ፐርሰንት ወርዷል። ስለዚህ ውለታው ከትራምፕ ይልቅ ለባራክ የሚገባው ይመስላል።

ያም ሆኖ በትራምፕ ዘመን በክፍያ ደረጃ የተለያዩ መዋዠቆች ተፈጥረዋል።

ለምሳሌ በአሜሪካ አማካይ የጥቁሮች የቤተሰብ ገቢ መጠን ከነጭ ቤተሰብ ጋር ሲነጻጸር በ60 እጅ ያነሰ ነው። ይህም በትራምፕ አስተዳደር እየባሰበት እንጂ እየተሸሻለ አልመጣም።

2.የጥቁር አሜሪካዊያን የድህነት መጠን በዶናልድ ትራምፕ ዘመን መሻሻል አሳይቶ ይሆን?

በ2018 የጥቁር አሜሪካዊያን የድህነት መጠን 20.8 ደርሶ ነበር። ይህም የድህነት መጠንን መለካት ከተጀመረበት ከ1960ዎቹ ወዲህ ዝቅተኛው ነው።

ይህ ማለት 8.9 ሚሊዮን ጥቁር አሜሪካዊያን በድህነት ውስጥ እንደሆኑ የሚናገር ቁጥር ነው።

እዚህ ላይ የአሜሪካ የድህነት መለኪያ አሰፋፈር ምን እንደሚመስል መረዳት ያሻል።

የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ አንድ ቤተሰብ የሚያገኘው ገቢ ያ ቤተሰብ ከሚያስፈልገው መሰረታዊ ገቢ ያነሰ ከሆነ ያን ቤተሰብ በድህነት ላይ ያለ ቤተሰብ ብሎ ይመዘግበዋል።

የጥቁር ቤተሰብ ድህነት እየቀነሰ መምጣት የጀመረውም በባራክ ኦባማ የመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዓመታት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

3.የጥቁር አሜሪካዊያን የወንጀል ተሳትፎ የቀነሰው በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ነው?

ይህን ጥያቄ በእርግጠኝነት መመለስ ያስቸግራል።

የአሜሪካ ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) የሚሰብስባቸው የወንጀል ድርጊቶች ቋት አለ። ነገር ግን ቋቱ ወንጀሉ ተፈጸመ ሲባል ወንጀል ፈጻሚዎቹን በዘራቸው ከፋፍሎ አያስቀምጥም። ስለዚህ ይህ ዘር ከዚህ ዘር ጋር ሲነጻጸር የወንጀል ተሳትፎው ቀንሷል ወይም ጨምሯል ለማለት ይከብዳል።

በመላው አሜሪካ ከፍተኛ የሚባሉ ወንጀሎች ግን እንዲሁ በደምሳሳው እየቀነሱ መጥተዋል ማለት ይቻላል፤ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን።

በአሜሪካ አደገኛ ወንጀሎች ከፍተኛ የነበሩበት ዘመን የ1990ዎቹ ነበሩ።

በወንጀል ተጠርጥረው የሚታሰሩ የጥቁር አሜሪካዊያን ቁጥርን ከተመለከትንም ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እየመጣ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ይፋ ባደረገው አንድ ሰነድ በ2018 በአሜሪካ ምድር በአንዳች የወንጀል ጥርጣሬ የተነሳ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ጥቁሮች ብዛት 2 ሚሊዮን 115ሺህ 381 ነበር።