በጥቁር አሜሪካዊው ሞት ያሾፉ ሦስት ፖሊሶች ከሥራቸው ተባረሩ

ፖሊሶቹ ለመሳለቅ የተነሱት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, AURORA POLICE DEPARTMENT/REUTERS

የምስሉ መግለጫ, ፖሊሶቹ ለመሳለቅ የተነሱት ፎቶ

በአሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛት አንድ ጥቁር አሜሪካዊ አንገቱ በክንድ ተይዞ ትንፋሽ አጥሮት የሞተበትን አያያዝ በማስመሰል እተሳለቁ ፎቶ የተነሱ ሦስት የፖሊስ አባላት ከሥራቸው መባረራቸው ተገለጸ።

ሌላ ተጨማሪ የፖሊስ አባል ደግሞ ከጉዳዩ ጋር በተያኣዘ በገዛ ፈቃዱ ከሥራው መልቀቁ የተገለጸ ሲሆን አንድ የአካባቢው ፖሊስ ፎቶ የመነሳት ድርጊቱን ለማሰብ የሚከብድ ነው ብሎታል።

ኤላእጃህ ማክሌይን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በፖሊስ እንዲቆም ተደርጎ አንገቱ ክፉና በክንድ ታንቆ ከተያዘ በኋላ ነበር ሕይወቱ ያለፈችው።

የኤላይጃህ ጉዳይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ ካለፈችው ከጆርጅ ፍሎይድ በኋላ በድጋሚ መነሳት ጀምሯል።

ተግባሩን በመጸማቸው ከሥራቸው የተባረሩት የፖሊስ አባላት ጄሰን ሮዘንብላት፣ ኤሪካ ማሬሮ እና ካይል ዲትሪች የሚባሉ የፖሊስ ኃይል አባላት መሆናቸው ታውቋል።

አራተኛው የፖሊስ አባል ጃሮን ጆንስ ደግሞ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሥራውን ለቋል።

የዴንቨር አካባቢ ፖሊስ ጊዜያዊ ኃላፊዋ ቫኔሳ ዊልሰን ምስሎቹን ሰብአዊነትና ሞራል ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው ብለዋል።

"በተፈጠረው ነገር በእጅጉ አዝነናል፣ ተቆጭተናል እንዲሁም ተበሳጭተናል" ሲሉም ተደምጠዋል።

"ምንም እንኳን ጉዳዩ በወንጀል የማያስቀጣ ቢሆንም ሰብአዊነትን ግን በእጅጉ የጣሰ ነው። አንዲህ አይነቱን ነገር አይደለም ማድረግ ማሰብ በራሱ ከባድ ነው" ብለዋል።

የፖሊስ አባላቱ ከተነሷቸው ፎቶዎች መካከል በአንደኛው ላይ አንገቱ የታነቀ ሰው በመምሰል የቆሙ ሲሆን ሦስተኛዋ ፖሊስ ደግሞ ከኋላ ሆና ፈገግ ብላ ትታያለች።

በመቀጠል ጄሰን የተባለው የፖሊስ አባል ፎቶውን ከጽሁፍ መልዕክት ጋር የላከው ሲሆን በሳቅ ቃላት ምላሽ ሰጥቷል።

ላይጃህ ማክሌይን እንዴት ሞተ?

ኤላይጃህ ማክሌይን የ24 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን፤ ከዓመት በፊት አውሮራ ከተማ ውስጥ በእግሩ በመጓዝ ላይ ሳለ ነበር በድንገት ሦስት የፖሊስ አባላት ያስቆሙት።

የአካባቢው ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ከሆነ የፖሊስ አባላቱ የኤላይጃህ አይነት አካላዊ ቅርጽ ያለው ተጠርጣሪ እየፈለጉ እንደሆነ አስታውቀው ነበር።

በሁኔታው የተደናገጠው ኤላይጃህ ፖሊሶቹ በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲሉ ታግሏቸው ነበር። ከዚያም ፖሊሶቹ የጦር መሳሪያ መያዝ አለመያዙን ለመፈተሽ ሲሞክሩ ግብግብ ተፈጠረ።

ከፖሊሶቹ ደረት ላይ ያለው ካሜራ ቀርጾ ባስቀረው ምስል ላይ ኤላይጃህ 'ጭንቀት አልችልም በጣም እየተጠጋችሁኝ ነው' ሲል ተደምጧል።

በመቀጠል አንደኛው ፖሊስ ሽጉጥ ሊያወጣ ነው በማለት ወደ መሬት ወርውረው፤ አንገቱን ተጭነው ያዙት።

ሪፖርቱ እንደሚለው በወቅቱ ኤላይጃህ እራሱን ስቶ ነበር። ከሰመመኑ ሲነቃ በድጋሚ ትግል ያደርጋል፤ ነገር ግን አልተሳካለትም።

በወቅቱ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አልውልም ያለ ሰው አለ በማለት እርዳታ ይጠይቃሉ። ወዲያውም አምቡላንስ መጥቶ ‘ኬታሚን’ የተባለ ማደንዘዣ መድኃኒት ወጉት።

በመቀጠል ኤላይጃህ በቃሬዛ ላይ ተደርጎ ወደ አምቡላንሱ እንዲገባ ተደረገ። ወዲያው ግን በቦታው የነበረው የህክምና ባለሙያ ደረቱ አካባቢ ምንም እንቅስቃሴ አለመኖሩን አስተዋለ።

እዚያው አምቡላንስ ውስጥም እያለ ሕይወቱ አለፈች።

ቤተሰቦቹ እንደሚሉት ፖሊሶች ለ15 ደቂቃዎች ያክል አላስፈላጊ ኃይል በመጠቀም ለሞት አብቅተውታል። በወቅቱም በተደጋጋሚ መተንፈስ እንዳልቻለ ይጮህ ነበር። ሲያስመልሰውም ነበር።

ቤተሰቦቹ አክለውም አርፎ ካልተቀመጠ በውሾች እንደሚያስነክሱት ሲዝቱበት ነበር ብለዋል።

በአስክሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራም የሞቱ መንስኤ ያልታወቀ ተብሎ ተመዝግቧል።