የሊቨርፑል ተጫዋቾች የአሜሪካውን ግድያ ተቃወሙ

የሊቨርፑል ተጫዋቾች የፍሎይድ ግድያን በመቃወም ተነሱት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, LFC

የምስሉ መግለጫ, የሊቨርፑል ተጫዋቾች የፍሎይድ ግድያን በመቃወም ተነሱት ፎቶ

የሊቨርፑል ተጫዋቾች በአፍሪካ አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ላይ በፖሊስ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም በልምምድ ሜዳቸው ማሃል ላይ ክብ ሰርተው በጉልበታቸው ተንበርክከው አጋርነታቸውን አሳዩ።

29 የሊቨርፑል ተጫዋቾችን ተንበርክከው የሚያሳየው ፎቶግራፍ የወጣው "አንድነት ኃይል ነው" ከሚል የፎቶ መግለጫ ጋር ነው።

ተጫዋቾቹ ፎቶውን የተነሱት ዛሬ ሰኞ በነበራቸው ልምምድ ላይ ሲሆን፤ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ማርከስ ራሽፎርድ እና ጃደን ሳንቾም በዓለም ዙሪያ እየተስተጋባ ባለው ጸረ ዘረኝነት ተቃውሞ ላይ ድምጻቸውን በማሰማት ተሳትፈዋል።

የማንችስተር ዩናይትድ እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹ ማርከስ ራሽፎርድ በበኩሉ ክስተቱ ለመቀበል እንደተቸገረ እንዲህ ሲል ተናግሯል "በምድራችን ላይ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመረዳት እየሞከርኩ ነው።"

ጨምሮም "ሰዎች አንድ ላይ እንዲሆኑ፣ አብረው በመስራት ህብረት እንዲፈጥሩ በሚጠየቅበት ጊዜ፤ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ተከፋፍለን እንገኛለን።

"በዚህም ሰዎች እየተጎዱ ነው ምላሽን ይሻሉ። ስለጥቁሮች ሕይወት ግድ ይለናል። ስለጥቁሮች ባሕል ያገባናል። ስለጥቁሮች ማኅበረሰብ ግድ ይለናል። እኛም ድርሻ አለን። [ብላክ ላይቭስ ማተርስ]" ብሏል።

ከሳምንት በፊት ጆርጅ ፍሎይድ ሚኒያፖሊስ ውስጥ ዴሪክ ቾቪን የተባለ ፖሊስ መሬት ላይ በደረቱ እንዲተኛ አድርጎት በጉልበቱ አንገቱ ላይ ለደቂቃዎች በመጫን ትንፋሽ እንዲያጥረው በማድረግ ካሰቃየው በኋላ ህይወቱ በማለፉ አሁን ድረስ መላዋን አሜሪካ ያናወጠ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

የፖሊስ መኮንኑ በዚህ ድርጊቱ ከሥራው የተባረረ ሲሆን በግድያ ወንጀልም ክስ ተመስርቶበታል።