ትራምፕ በአሜሪካ የፖሊስ ኃይል ላይ ለውጥ እንዲደረግ ልዩ ውሳኔ አሳለፉ

ትራምፕ ውሳኔውን በፈረሙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሪቱ ፖሊስ ኃይል ላይ አዳዲስና በርካታ የለውጥ እርምጃዎች እንዲካሄዱ የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔን ፈርመው አጸደቁ።

ትራምፕ ይህንን ከፍተኛ ውሳኔን ያጸደቁት በፖሊስ ላይ የሚያገኘውን በጀት እንዲቋረጥ ወይም ሙሉ ለሙሉ እንዲበተን የሚጠይቁ ሃሳቦችን ውድቅ አድርገው ነው።

ትራምፕ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ተረብሸው ቆይተዋል።

የፖለቲካ ምኅዳሩን በአሉታዊ መልኩ አውኮት የነበረውን ይህንን በነውጥ የታጀበ ተቃውሞ ረገብ ለማድረግ ሲሉ ነው ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔ ይፋ ያደረጉት።

ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔው በፌዴራል ደረጃ ሁሉንም ሕግ አስፈጻሚዎች የሚያስገደድ ከሕግ በታች ያለ ሕግ ሆኖ ያገለግላል።

በአሜሪካ ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በሚያደርጉት ግብግብ ያልተመጣጠነ ኃይልን እንዳይጠቀሙ አዲስ የሕግ ሐሳቦች በሕግ መምሪያው ምክር ቤት ሲዘጋጁ መቆየታቸው ይታወሳል።

እነዚህ ረቂቅ የሕግ ሐሳቦች ገና በሂደት ላይ ያሉ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ከፈረሙት ማሻሻያ በጠነከረ መልኩ አዲስና ጠንካራ የሕግ ማሻሻያ ሊቀርብ እንደሚችል ይጠበቃል።

ዶናልድ ትራምፕ የፈረሙት አዲስ ውሳኔ በዋናነት የፌዴራል ፖሊስ በጀትን ከማሳደግና የፖሊስ አሰራርና ስልጠናን ከማዘመን ጋር የተያያዘ ነው።

የፕሬዝዳንታዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ዶናልድ ትራምፕ ባጸደቁት በዚህ ልዩ ውሳኔ መሠረት ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን አንገት ማነቅና መጠምለል አይችልም።

ዶናልድ ትራምፕ ተግባራዊ እንዲደረግ የፈረሙት የትናንቱ ማሻሻያ የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ አስፈጸሚ አካላት ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ከፖሊስ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የፖሊስ ሠራዊት አሰራሩን ያዘምናል፤ ለዚህም የሚሆን በርከት ያለ ገንዘብ ከፌዴራል ካዝና እንዲለቀቅ ያስችላል።

ባለፉት ቀናት በፖሊስ ያልተመጣጠነ እርምጃ ቤተሰባቸውን ያጡ በርካታ ጥቁር አሜሪካዊያን በነጩ ቤተ መንግሥት ጠርተው ማነጋገራቸውን የጠቀሱት ትራምፕ ማሻሻያ ማድረጉ አስፈላጊና ጊዜ የማይሰጥ ነው ብለዋል።

የፖሊሶችን ተጠያቂነት ማሳደግ፣ የአሰራር ግልጽነት እንዲኖር ማድረግ እና በፖሊስ ሥልጠናና ምልመላ ዙርያ ትኩረት አድርጎ መስራት ያሻል ብለዋል ትራምፕ ፊርማ ባኖሩበት ወቅት ለጋዜጠኞች።

ባለፈው ወር የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን በማሰብ ተቃውሞዎች ከተቀጣጠሉ በኋላ ራይሻርድ ብሩክስ የተባለ ሌላ ጥቁር አሜሪካዊ ባለፈው አርብ በአትላንታ ፖሊስ በሽጉጥ ተመትቶ መገደሉ እየሰከነ የነበረውን ተቃውሞ አባብሶት ቆይቷል።

የዶናልድ ትራምፕ አዲስ ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔ ይፋ የተደረገው ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን በአሜሪካ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የፖሊስ አሰራርን በተመለከተ የማሻሻያ ረቂቅ እያሰናዱ ባለበት ጊዜ ነው።

የዶናልድ ትራምፕ አዲስ ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ፌዴራል መንግሥት ለፖሊስ ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ እንዲያደርግ የገንዘብ ድጎማ ማድረግ ላይ ነው።

በጥቁሮች ላይ ሚፈጸሙ ግፎችን የሚቃወሙ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በጥቁሮች ላይ ሚፈጸሙ ግፎችን የሚቃወሙ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል

ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን ያኖሩበት አዲስ ሕግ የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ይዟል።

• በፌዴራል ደረጃ በፖሊሶች ላይ የሚቀርብን ቅሬታ መዝግቦ የሚይዝና የሚከታተል አገር አቀፍ የመረጃ ቋት ማዘጋጀት። ይህም መጥፎ ባህሪ የተጸናወታቸውና ሥነ ምግባር የሌላቸው ፖሊሶችን ዱካ ለመከታተል ይረዳል ተብሎ የታሰበ ነው።

• የሱስ ተጠቂዎችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚደረግ ሂደት ውስጥ በዚህ ዘርፍ የሰለጠኑ የማኅበረሰብ እርዳታ ሰጪ ባለሞያዎች ከፖሊስ ጋር አብረው እንዲሆኑ ማድረግ።

• ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በሚያድንበት ወቅት ጆርጅ ፍሎይድ የደረሰበት ዓይነት ማጅራትን ቆልፎ የመያዝ የኃይል እርምጃ ተግባራዊ እንዳይደረግ ማድረግን ያካትታል።

ዋይት ሐውስ እንደሚለው ይህ የፕሬዝዳንቱ መመሪያ ማሳካት የፈለገው በአሜሪካ ፖሊስንና ማኅበረሰቡን ማቀራረብ ነው።

በዚህ መመሪያ ፖሊሶች የተጠርጣሪን ማጅራት መጠምለል ወይም ቆልፎ መያዝ እንዳይችሉ ቢያዝም ፖሊስ ሕይወቴ አደጋ ላይ ነው ብሎ ካሰበ ግን ተጠርጣሪውን በዚያ መንገድ ሊይዘው መብት ይሰጠዋል።

የፕሬዝዳንቱ ተቺዎች ውሳኔው አይረባም እያሉ ነው።

የሴኔት ዲሞክራቲክ ፖርቲ ተወካይ ቸክ ሹመር የፕሬዝዳንቱ ሕግ በቂ ስላልሆነ ሕግ አውጪ የምክር ቤት አባላት ጠንከር ያለ ሕግ በቶሎ ማርቀቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

"በሚያሳዝን ሁኔታ ፕሬዝዳንቱ ያወጡት ትዕዛዝ ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥና ተጠያቂነትን የሚያመጣ አይደለም፤ የአሜሪካ ሕዝብ የጠየቀው ይህን አልነበረም" ብለዋል ሹመር።

"የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በበኩላቸው የዘረኝነትን ወረርሽኝ ለማስቆምም ሆነ የፖሊስን ግፍ ለመገደብ የማይጠቅም መናኛ መመሪያ ብለውታል" የትራምፕን ልዩ ማሻሻያ።

የፕሬዝዳንቱ መመሪያ በፖሊስና በጥቁር ተጠቂዎች ዘንድ ከፍተኛ ችግር የፈጠረውን የሕግ ክፍተት የሚደፍን አለመሆኑ በብዙ አስተችቶታል። ይህም በሕግ ቋንቋ "ኳሊፋይድ ኢሚዩኒቲ" የሚባለው ነው።

በዚህም መሰረት አንድ ሕግ አስከባሪ አጥፍቶ እንኳ ቢሆን ጥፋቱ ጥፋት የሚሆነው በሕግ ፊት የሕገ መንግሥት መብቶችን ሆን ብሎ ስለመጣሱ ግልጽና የማያሻማ መረጃ ሲቀርብበት ብቻ ነው ይላል። ይህ የሕግ ክፍተት ፖሊሶች በእንዝላልነት ሰው ገድለውም ቢሆን እነሱን ፍርድ ቤት አስቀርቦ ማስወሰንን ዳገት ያደርገዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአሜሪካ ቢሮ ባልደረባ ክሪስቲና ሮዝ ትራምፕ የፈረሙት የሕግ ማሻሻያ መመሪያ መዋቅራዊ የዘረኝነት ችግሩን እንደማይፈታው ሲተቹ የሚከተለውን ብለዋል።

"በጥይት ለቆሰለ ሰው ጥይቱን ሳያወጡ ፋሻ የመጠቅለል ያህል ነው"

አዳዲስ ሕጎች እየተረቀቁ ነው

በሚኒያፖሊስ የከተማዋ ምክር ቤት አባላት የፖሊስን በጀት በመወሰን ለሌላ ተግባር ማዋል ሀሳብ አቅርበዋል።

በአትላንታ የራይሻርድ ብሩክስን በፖሊስ መገደል ተከትሎ ከንቲባ ኬይሻ በርካታ ለውጦች እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።

ከእነዚህም ማሻሻያዎች አንዱ አንድ ፖሊስ ከመስመር ሲወጣ ባልደረቦቹ ጣልቃ ገብተው የማስቆም መብትና ግዴታን የሚሰጥ ነው።

ከአትላንታ ሌላ ሳንፍራንሲስኮ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ኒው ዮርክና ቺካጎ ሁሉም ከፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ማሻሻያ እንደሚያደርጉና ዘረኛ ፖሊሶችን ከሥራ እንደሚያግዱ ዝተዋል።

የኒው ዮርኩ ገዢ አንድሩ ኩሞ ባለፈው ሰኞ የፈረሙት አዲስ መመሪያ ፖሊስ አሰሳ በሚያደርግበት ወቅት ካሜራ የተገጠመለት የደንብ ልብስ እንዲለብስ ያስገድዳል። በተጨማሪም የፖሊስን የሥነ ምግባር ጥሰት የሚመረምር አዲስ ቢሮ ለማቀቀም ያስችላል።

በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት አዲስ ረቂቅ ሕግ አቅርበዋል።

ይህ ረቂቅ ሕግ ተጠርጣሪን አንቆ መያዝ፣ ሳያንኳኩ በር ገንጥሎ መግባት፣ ባለቤት ሳያስፈቅዱ የሰው ቤት ዘው ብሎ መግባትን ይከለክላል።