የጆርጅ ፍሎይድ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ሳምንት በሜኔሶታ የ46 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድን ለሞት ያበቃው በትክክል ምንድነው የሚለውን ለመለየት የሕክምና ውጤት ይፋ እስኪሆን ሲጠበቅ ቆይቷል።

በሟች አስከሬን ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው የሕክምና ተቋም ውጤቱን በመጨረሻ ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት ጆርጅ ፍሎይድ የተገደለው በሰው እንደሆነ ብያኔ ሰጥቷል።

ከዚህ መረጃ መውጣት በፊት አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የጥቁሩ አሜሪካዊ ሞት ፖሊስ ኃይልን ከመጠቀሙ ጋር በፍጹም የሚያያዝ አይደለም ሲሉ መዘገብ ጀምረው ነበር። አንዳንዶች እንዲያውም የሞተው በራሱ የጤና ችግር ነው እስከማለት ደርሰው ነበር።

ይህ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ሲጠበቅ የነበረውም ለዚሁ ነው።

ይፋ በሆነው የአስከሬን ምርመራ ሪፖርት እንደተገለጸው ፍሎይድ ከክስተቱ በፊት ለሞት የሚያበቃው አንዳችም ነገር አልነበረም። ሆኖም የፖሊስ መኮንኑ በጉልበቱ አንገቱን በመጫኑ የልብ መታፈን ገጥሞታል። ያም ነው ለሞት ያበቃው ብሏል።

በሕክምና ስሙ "ካርዲዮፑልሙናሪ አሬስት" የሚባለው ችግር በድንገት የደም ዝውውር ሲቆምና ይህም ልብ ደም መርጨት እንዲያቆም ሲያስገደድ የሚፈጠር ውስብስብ ችግር ነው።

ጆርጅ ፍሎይድ ማጅራቱ አካባቢ የተጫነው ጉልበት የደም ዝውውሩን ሳያቋርጠው አልቀረም ይላል ሪፖርቱ።

የአስከሬን ምርመራውን ያደረገው የሄኒፒን ካውንቲ ጤና ጣቢያ ሲሆን ሟች የልብ ሕመም እንደነበረበት እና መድኃኒት ወስዶ እንደነበረ የሚያሳዩ መረጃዎችን ማግኘት ችሏል።

ይህ ሁኔታም ፖሊስ የሟችን ማጅራት በከፍተኛ ሁኔታ ሲጫነው ለመተንፈስ እንዲቸገር አድርጎት በዚህም የሟች የልብ ምት እንዲቆም አድርጎታል ይላል።

ይህ መረጃ ይፋ የሆነው የፍሎይድ ቤተሰብ የግል አስከሬን መርማሪ ቡድን መቅጠረን ተከትሎ ነው። የፍሎይድ ቤተሰብ የቀጠረው የሕክምና መርማሪ ቡድንም ተመሳሳይ ውጤት ላይ ነው የደረሰው።

የአስከሬን ምርመራ ሪፖርቱ ድምዳሜ ሟች ለህልፈት የበቃው በአሲፊክሲያ ነው ይላል። አሲፊክሲያ የኦክሲጅን እጥረት ሲሆን ይህም ሊፈጠር የቻለው ደግሞ በማጅራቱና በጀርባው አካባቢ ፖሊስ ሟችን እጅግ ስለተጫነው ነው ይላል።

ዶ/ር ማይክል ባደን የኒውዮርክ ከተማ የቀድሞ የአስከሬን ምርመራ ባለሞያ ናቸው። ባለፈው ሰኞ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "ጆርጅ ፍሎይድን ለሞት አብቅቶታል ብዬ በግሌ የምገምተው አሲፊክሲያ ነው፤ ይህም የሚፈጠረው ወደ ጭንቅላት የሚሄደው አየር ሲቋረጥ ነው" ብለው ነበር።

የሟች ቤተሰብ ጠበቃ ቤንጃሚን ክራምፕ በበኩላቸው "ወንድማችን ፍሎይድን፤ የፖሊስ መኮንኑ ዴሪክ ቾቪን ማጅራቱን ባይጫነው ኖሮ፣ ሁለቱ ባልደረቦቹ ጀርባው ላይ ባይቆሙበት ኖሮ ዛሬ ከእኛ ጋር ይቆም ነበር" ብለዋል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የመጣችው አምቡላንስ ግን ይላሉ ጠበቃው "የሬሳ ሳጥኑ ነበረች።"