አል ቃኢዳ በጆርጅ ፍሎይድ ሞት አሜሪካዊያን በደንብ እንዲቆጡ አሳሰበ

በተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙ ነጭ አሜሪካዊያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ አሜሪካዊያንን በአንድ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል

አል ቃኢዳ ከሰሞኑ ከተደበቀበት ድምጹ ተሰምቷል።

በጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ የግፍ ግድያ የተቀሰቀሰው ቁጣ የተስማማው ይመስላል።

ለተጨቆኑት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እቆማለሁ የሚለው አልቃኢዳ ከሰሞኑ ባሰራጨው መልዕክት ሙስሊም አሜሪካዊያንን ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ያልሆኑትንም በተቃውሟቸው እንዲገፉበት ሲያበረታታ ነበር። ይህ በአል ቃኢዳ ያልተለመደ አካሄድ ይመስላል።

"ኡማህ" የሚባለው የዚህ ቡድን የበይነ መረብ መጽሔት በሰሞኑ ልዩ ዕትሙ የጆርጅ ፍሎይድን ምስል ከፊት ለፊት አውጥቶ አትሞታል።

የተጠቀመው ምስል የፍሎይድን የመጨረሻ የጭንቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶችን የሚያሳይ ነበር።

ምስሉ የተሰራው በጎዳና ላይ የሥዕል ጥበበኛ ባንክሲ ሲሆን አል ቃኢዳ በአሜሪካ ለተነሳው ተቃውሞ የማያወላዳ ድጋፍ እየሰጠ እንደሆነ ያረጋገጠበት ተደርጎ ተወስዷል።

ይህ የአል ቃኢዳ ልሳን የሆነው 'ኡማህ' መጽሔት በእንግሊዝኛ መታተሙ በራሱ የሚናገረው ነገር ቢኖር መልዕክቱ እንዲደርስለት የፈለገው ለአሜሪካዊያንን እንደሆነ ነው።

በዚህ የመጽሔት መጣጥፉ አል ቃኢዳ "የአሜሪካ መውደቂያ መቃረቡ አይቀሬ" መሆኑን የተነተነ ሲሆን ከሁሉ በፊት ግን የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት እንደሚንኮታኮት ይተነብያል።

"የትጥቅ ትግል በአሜሪካ ተቀጣጥሏል፤ የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ አይቀሬ ነው" የሚለው አል ቃኢዳ "ከዚህ ውጥንቅጥ የሚያወጣችሁ ታዲያ ዲሞክራቶች እንዳይመስሏችሁ፤ ከዚህ ቸግር የሚያወጣችሁ አል ቃኢዳ ብቻ ነው" ይላል።

የቢቢሲ የሚዲያ ቅኝት ባለሞያ ሚና አልላሚ በዚህ ዙርያ በሰጠችው አስተያየት በአል ቃኢዳና በአይኤስ መካከል የአቀራረብ ልዩነት እንዳለ አስምራበታለች።

"አይኤስ አሜሪካ በገጠማት ተቃውሞ እግሩን ዘርግቶ እየሳቀ ሲሆን አልቃኢዳ ግን የአሜሪካዊያንን ቋንቋና የጥቁሮችን ቁስል እየነካካ ወደ ራሱ ርዕዮተ ዓለም ለመማረክ እየሞከረ ነው።"

ሚና እንደምታምነው የአል ቃኢዳ 'ኡማህ' መጽሔት የቅርብ ጊዜ ትንታኔ የተጻፈው የአሜሪካንን ፖለቲካ በቅርብ በሚከታተልና ጠንቅቆ በሚያውቅ አባል ነው።

አል ቃኢዳ ወደ መድረኩ እየተመለሰ ይሆን?

አል ቃኢዳ ባለፉት ዓመታት በአይ ኤስ ተጋርዷል። በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የጽንፈኝነት ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር ሺራዝ ማሄር ግን በዚህ አይስማሙም።

እርሳቸው እንደሚያምኑት አል ቃኢዳ አሁንም ቢሆን ከጀርባ ሆኖ ሥራውን እየሰራ ነው። በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አሁንም ተሰሚነት ለማግኘትና ወደ መድረኩ ለመመለስ ፍላጎት አለው።

"ይህ ከሰሞኑ የተፋፋመው የጥቁሮች የመብት እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ መልክ ሊይዝ የሚችል ጉዳይ እንደሆነ አልቃኢዳ ጠንቅቆ ይረዳል። ለዚህም ነው ዝም ብሎ ቆይቶ አሁን "አለንላችሁ" ማለት የፈለገው" ባይ ናቸው።

ምጸቱ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ የመብቶች ሁሉ ጨፍላቂ እና የእልቂት ጌታ የሆነው አል ቃኢዳ አሁን ደርሶ ጥቁሮች ላነሱት አጀንዳ ፈውስ አለኝ እያለ የመብት ጠበቃ ልሁን ማለቱ ነው።

ኦሳማ ቢን ላደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኦሳማ ቢን ላደን

አል ቃኢዳ በቀድመው መሪው ኦሳማ ቢን ላደን መሪነት በአሜሪካ መሬት ላይ ከፍተኛውን ጥፋት ካደረሰ ሃያ ዓመት ሊደፍን ተቃርቧል።

አል ቃኢዳ የሌሎችን መብት ለማክበር ይቅርና በኢራቅ ፋሉጃ ግዛት ውስጥ ሲጃራ አጭሳችኋል ብሎ የወንዶችን ጣቶች በመቁረጥ የቀጣ ቡድን መሆኑ ሲታወስ፤ አሁን የመብት ታጋዮችን አይዟችሁ ማለቱ ወለፈንዲ ይሆናል ሲል የቢቢሲው የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢ ፍርንክ ጋርድነር* ያትታል።

አል ቃኢዳም ሆነ አይኤስ በኒው ዮርክ ከመንትያዎቹ ሕንጻዎች ጥቃት በኋላ በአሜሪካ ምድር ይህ ነው የሚባል ጉዳት አድርሰውም ሆነ ደጋፊም አግኝተው አያውቁም።

ለመጨረሻ ጊዜ በ2019 በታኅሣስ ወር የሳኡዲ ዜጋ በፍሎሪዳ ፔንሳኮላ ያደረሰው ጥቃት ተጠቃሽ ነው። ከዚያ ወዲያ አልተሰማም።

ደጋፊ በማግኘት ረገድም በአውሮፓ ውስጥ በርካታ አባላትን መመልመል ቢችልም በአሜሪካውያን ዘንድ ግን ይህን ማሳካት አልቻለም።

የምዕራቡ ዓለም የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ላለፉት ዓመታት አል ቃኢዳ ጨርሶ እንዳልጠፋና ጉዳት ለማድረስ እየጠበቀ ያለው ትክክለኛ ጊዜና ምቹ ሁኔታን ብቻ ስለመሆኑ ሲያስገነዝቡ ቆይተዋል።

አል ቃኢዳም ሆነ አይ ኤስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሜሪካና በእንግሊዝ በተለየ ጉዳት ያደረሰው ሁለቱ አገራት በመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝቦች ዘንድ ባደረሱት የዘመናት ግፍ የተነሳ ነው በማለት ብዙዎችን ለማሳመን ሞክረዋል።

ያም ሆኖ በዚህ ወረርሽኝ እየተጠቁ ያሉት አሜሪካና እንግሊዝ ብቻ ሳይሆን የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትም ጭምር ናቸው። ለምሳሌ ኢራን 175 ሺህ ዜጎቿ ተጠቅተውባታል። ግብጽ በበኩሏ በቀን በአማካይ 2 ሺህ ሰዎች እየተጠቁባት ይገኛሉ።

የምዕራቡ ዓለም ደኅንነት ተቋማት ምን ያስባሉ?

ዛሬ ሁለቱ ጽንፈኛ ቡድኖች ለጋራ ጠላት የጋራ አቋም የያዙ ይመስላሉ።

በአሜሪካ ለእኩልነትና ለጸረ ዘረኝነት ድምጻቸውን እያሰሙ ያሉ አሜሪካዊያንን "ጉዳያችሁ ጉዳያችን ነው" እያሉ ለተጨማሪ ጥቃት እያበረታቷቸው ነው። ለተጨማሪ ተቃውሞ፣ ለተጨማሪ መብት፣ ለተጨማሪ አመጽ ለመቀስቀስ እየሞከሩ ነው።

በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ለእኩልነት በሚታገሉ ሰልፈኞች መሀል የሁለቱ ጽንፈኛ ኃይሎች ጥሪ ትኩረት ያገኛል ማለት ዘበት ነው፤ የሚያስተውለው መኖሩን እንኳ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

አል ቃኢዳ ሽብርተኛ ድርጅት ሲሆን በመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት 3 ሺህ ንጹህ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል።

ለመሆኑ ይህ የአል ቃኢዳ ጥሪ የአሜሪካ ጸረ ሽብር ደኅንነት ሰዎችን ምን ያህል አሳስቧቸው ይሆን?

ዶ/ር ማሄር ላለፉት 20 ዓመታት የእነዚህን ጽነፈኛ ቡድኖች አስተሳሰብና ፍልስፍና እንዲሁም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ሲያጠኑ የቆዩ ጉምቱ ምሁር ናቸው።

እንደርሳቸው አመለካከት የአል ቃኢዳ መልዕክት ጥሩ አጋጣሚን ለመጠቀም ከመሞከር ያለፈ አይደለም።

"የአልቃኢዳ ሙከራ ለማንኛውም ብሎ መረቡን እንደሚዘረጋ አሳ አጥማጅ ያለ ነው" ይላሉ።

*(ይህ ጽሑፍ በቢቢሲው የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢ ፍርንክ ጋርድነር የተጠናቀረ ነው፡፡)