የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች መለያ በስማቸው ምትክ የጥቁሮች ፍትህ ጥያቄ ሊሰፍርበት ነው

የተጫዋቾች አልባሳት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በተጫዋቾቹ ስም ምትክ የጥቁሮች የመብት ጥያቄ ይሰፍራል ተብሏል

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ቀሪዎቹን 12 ጨዋታዎች ሲያደርጉ ከመለያቸው ጀርባ ላይ በስማቸው ፈንታ 'ብላክ ላይቭስ ማተር' [የጥቁሮች ህይወት ዋጋ አለው] የሚለውን ጽሁፍ እንደሚያሰፍሩ ተገለጸ።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሪምየር ሊጉ ከጨዋታ በፊትም ሆነ በኋላ የጥቁሮች የፍትህ ጥያቄ መለያ በሆነው ተንበርክኮ ድጋፋቸውን ለመግለጽና መልዕክት ማስተላለፍ የሚፈልጉ ተጫዋቾች አይከለከሉም ብሏል።

ቀድሞ በተጀመረው የጀርመን ቡንደስሊጋ የሚጫወቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ነበሩ የጆርጅ ፍሎይድን ሞት አስመልከቶ ሜዳ ውስጥ ቀድመው መልዕክት ያስተላለፉት።

የፕሪምየር ሊጉ 20 ቡድኖች ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ "እኛ እንደ እግር ኳስ ተጫዋች በህብረት በመቆም የዘር መድሎን ለማስወገድ አብረን እንቆማለን" ብለዋል።

አክለውም ሁሉንም ያካተተ፣ መከባበር ያለበትና በቀልም እንዲሁም በጾታ ሳይለይ ሁሉም እኩል እድል የሚያገኝበት ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ የሚለውን መልዕክት የዘንድሮው የውድድር ዓመት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ተጫዋቾች በጀርባቸው ላይ የሚያደርጉ ሲሆን በተጨማሪም በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን የሚያመሰግን መልዕክትም ያስተላልፋሉ።

በርካታ የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች በስልጠና ሜዳዎች ላይ በመንበርከክ ዘረኝነትን ያወገዙበትን ምስል ቀደም ሲል በማኅበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ አጋርተዋል።

ባለፈው ወር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሳል ህይወቱ ባለፈቸው የ46 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ሞት ምክንያት ዘረኝነት ይቁም በማለት ሜዳ ውስጥ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ አራት የጀርመን ቡንደስሊጋ ተጫዋቾች በእግር ኳስ ማኅበሩ ምርመራ ተደርጎባቸው ነበር።

በመጨረሻ ግን የትኛውም ተጫዋች ቅጣት እንዳልተጣለበትና ተጫዋቾች በሚቀጥሉት ሳምንታት ዘረኝነትን በመቃወም መልዕክታቸውን ማስተላለፍ እንደሚችሉ የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር አስታውቋል።

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከሦስት ወራት በኋላ በዝግ ስታዲየሞች በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ የሚጀመር ሲሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በርካታ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ ተብሏል።

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንና የኒውካስል እንዲሁም የቶተንሀም አማካይ ጀርሜይን ጄናስ ለቀሪዎቹ 12 ጨዋታዎች የሚተላለፈው መልዕክት በዘላቂነት ቢታሰብበት ጥሩ ነው ብሏል።

"ሁሉም ክለቦችና ተጫዋቾች በዚህ ጉዳይ ላይ ተስማምተው ዘረኝነትን ለመዋጋት ማሰባቸው በጣም ደስ የሚል ሀሳብ ነው። ቀላል ለማይባሉ ሰዎች መልዕክቱ እንደሚደርስም እርግጠኛ ነኝ። ፕሪምየር ሊጉ በመላው ዓለም በርካታ ተከታታዯች ያሉት እንደመሆኑ እንዲህ አይነት ጠንከር ያሉ መልዕክቶች ለወደፊቱም ቢቀጥሉ ጥሩ ነው" ብሏል ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ።

አክሎም "በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጥቁር አሰልጣኞች እንደሌሉ በስፋት ይነገራል፤ አሰልጣኞችና ሌሎች አባላት ሲመለመሉ ብዝሃነትን ባማከለ መልኩ መደረግ ያለባቸው ይመስለኛል’’ ብሏል።