አሜሪካ፡ ፖሊሶች ጥቁር አሜሪካዊው ላይ መተኮሳቸውን ተከትሎ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካዋ ዊስኮንሰን ግዛት ፖሊሶች ጥቁር አሜሪካዊው ጃኮብ ብሌክ ላይ በተደጋጋሚ መተኮሳቸውን ተከትሎ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ጃኮብ ሆስፒታል ውስጥ በአስጊ ሁኔታ ይገኛል።
ኮኖሻ በተባለች ከተማ ጃኮብ ወደ መኪናው እየገባ ሳለ ፖሊሶች ከጀርባው ሲተኩሱ የሚያሳይ ተንቀሰቃሽ ምስል በማኅበራዊ ድረ ገጽ ተሰራጭቷል።
በከተማዋ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ አስቸኳይ የሰዓት እላፊ ታውጇል።
ትናንት ምሽት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ዋና ጽሕፈት ቤት ተቃውሞ አሰምተዋል። መኪኖች ተቃጥለዋል። ተቃዋሚዎችም “ወደኋላ አንልም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ፖሊስ ዘረፋ ይካሄዳል፣ ተኩስም ይኖራል የሚል መረጃ ደርሶኛል ብሎ፤ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋሞች እንዲዘጉ አሳስቧል።
ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል። ተቃዋሚዎቹ ሰልፍ የወጡት በአገሪቱ የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ ተላልፈው ነው።
የዊስኮንሰን አገረ ገዢ ቶኒ ኤቨርስ ምንም መሣሪያ ያልታጠቀው ጃኮብ ላይ ፖሊስ መተኮሱን ኮንነዋል።
“ሙሉ መረጃው ገና ባይኖረንም በአገራችን ወይም በግዛታችን በፖሊስ የተተኮሰበት፣ አካላዊ ጉዳት የደረሰበት ወይም ያለ ርህራሄ የተገደለ የመጀመሪያው ጥቁር ሰው አለመሆኑን እናውቃለን” ብለዋል።
አያይዘውም “ሀዘናችንን ከመግለጽ ባሻገር እርምጃም መውሰድ አለብን። በግዛታችን ለተንሰራፋው ዘረኛነት እውቅና ያልሰጡ ባለሥልጣኖች እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን” ብለወላል።
የጃኮብ ስም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተነሳ ሲሆን፤ በተኩሱ እጃቸው ያለበት ፖሊሶች ለፍርድ እንዲቀርቡ ፊርማ እየተሰበሰበም ነው።
በቅርቡ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ለበርካታ ሳምንታት የዘለቀ አገር አቀፍ ተቃውሞ መካሄዱ አይዘነጋም።
የተፈጠረው ምንድን ነው?
የኪኖሻ ፖሊስ እንዳለው ጃኮብ ላይ ፖሊሶች የተኮሱት ትናንት ከሰዓት ነው።
ፖሊሶች ጃኮብ ላይ ከተተኮሰ በኋላ “በፍጥነት እርዳታ አድርገዋል” ብሏል የፖሊስ ክፍሉ።
ፖሊሶች ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር በተያያዘ ምላሽ ለመስጠት በቦታው እንደተገኙ ቢገለጽም፤ ተኩስ ስለተከፈተበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
የዊስኮንሰን የፍትሕ ተቋም ክስተቱን እየመረመረ ይገኛል። ከተኩሱ ጋር በተያያዘ ሁለት ፖሊሶች ሥራ እንዲያቋርጡ መወሰኑም ተገልጿል።
በማኅበራዊ መዲያ የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ሦስት ፖሊሶች ጃኮብ ወደ መኪናው ሲያመራ መሣሪያ ደግነውበት ይታያል።
የመኪናውን በር ከፍቶ ሊገባ ሲል አንድ ፖሊስ ካናቴራውን ጎትቶ ሲተኩስበት ይታያል። ሰባት ጊዜ ሲተኮስና የአይን እማኞች ሲጮሁም ይሰማል።
በተኩሱ እጃቸው ያለበት ፖሊሶች ማንነት እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
ታዋቂው ጠበቃ ቤን ክራምፕ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት፤ የጃኮብ ቤተሰቦች ደውለውላቸው እርዳታቸውን ጠይቀዋል።
ጃኮብ ሲተኮስበት መኪና ውስጥ ሦስት ልጆቹ እንደነበሩም ጠበቃው በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
“ፖሊስ አባታቸው ላይ ሲተኩስ ተመልክተዋል። እስከ ወዲያኛው ጠባሳ ጥሎባቸዋል። እኛን መጠበቅ የሚገባቸው ፖሊሶች መብታችንን እንዲገፉ ልንፈቅድላቸው አይገባም” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠበቃው እንዳሉት ከተኩሱ በፊት ጃኮብ የሚደባደቡ ሰዎችን ለመገላገል ሲሞክር ነበር።
የአይን እማኞች እንደሚሉት፤ ጃኮብ በሁለት ሴቶች መካከል የተፈጠረ ድብድብን ለመገላገል ሲሞክር ፖሊሶች የኤሌክትሪክ ኃይል ያለው መሣሪያ (ቴዘር) ተጠቅመዋል።
የብላክ ላይቭስ ማተር የአካባቢው ቃል አቀባይ ክላይድ ማክለሞር፤ “የሚከሰተው ነገር እጅግ የሚያስቆጣ ነው። በጣም መሮናል፣ ታክቶናል” ብለዋል።
















