ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል የተጠረጠረው ዴሪክ ሾቪን በታክስ ወንጀል ተከሰሰ

የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪን በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ተወንጅሎ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኘው

ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል የተጠረጠረው የቀድሞው የሚኒያፖሊስ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪን በታክስ ወረራ ወንጀል ተከሰሰ።

ዴሪክ ሾቪን እና ባለቤቱ 38 ሺህ ዶላር ለሚኒሶታ ግዛት መገበር ሲገባቸው ይህን አላደረጉም ተብለው ነው የተከሰሱት።

ሾቪን ከሥራው የተባረረው ጆርጅ ፍሎይድ ላይ በፈፀመው ድርጊት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ግድያ ወንጀል ተከሷል። በድርጊቱ ተባባሪ ነበሩ የተባሉ ሌሎች ሶስት መኮንኖችም ክስ ተከፍቶባቸዋል።

ሾቪን እና አብራው የማትኖረው ሚስቱ ኬሊ በስድስት የተለያየ ወንጀሎች ተጠርጥረው ነው የተከሰሱት። ሁሉም ክሶች ከታክስ ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ናቸው።

ጠንዶቹ፤ በአውሮፓውያኑ ከ2014 እስከ 2019 ባለው ካስገቡት 464 ሺህ 433 ዶላር የሚገባውን ግብር አልከፈሉም ተብለዋል።

ተጠርጣሪው ከመደበኛ ሥራው ውጪ ቅዳሜና እሁድ በጥበቃ ሥራ ተሠማርቶ ካስገባው ገቢ ላይ ጭምር ለመንግሥት አልገበረም ተብሏል።

አቃቤ ሕግ ኢምራን አሊ ለአሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንዳስታወቁት ተጠርጣሪዎቹ ያልከፈሉት ግብር መጠን ምርመራው ሲጠናከር ሊጨምር ይችላል።

ዴሪክ ሾቪን በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ነው የሚገኘው። ነገር ግን ባለቤቱ ኬሊ እስካሁን በቁጥጥር ሥር እንዳልዋለች ታውቋል።

የቀድሞው የሚኒሶታ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የነበረችው ሚስት ወ/ሮ ኬሊ፤ ባለቤቷ ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል ከተወነጀለ በኋላ ፍቺ ጠይቃለች።

የዋሽንግተን ክፍለ ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፒት ኦርፑት ባወጡት መግለጫ «ግብር አለመክፈል ማለት ከሚኒሶታ ነዋሪዎች ኪስ ገንዘብ መመንተፍ ማለት ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

«አቃቤ ሕግ ብትሆኑ፣ ፖሊስ አሊያም ዶክተር ወይም መኖሪያ ቤት አሻሻጭ፤ ከሕግ በላይ አይደላችሁም» የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥተዋል።

የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ ለዘጠኝ ደቂቃዎች በጉልበቱ ቆሞ የሚያሳይ ምስል ከወጣ በኋላ በአሜሪካና በሌሎች ክፍለ ዓለማት ፀረ-ዘረኝነት ተቃውሞ ተቀስቅሷል።