ኮቪድ -19 ፡ በፈረንሳይ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፈረንሳይ ከመጋቢት ወዲህ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በአገሪቷ በድጋሜ እንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል እንደሚችል ተናግረዋል።
አርብ እለት ብቻ ተጨማሪ 7 ሺህ 379 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን በአጠቃላይ በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 267 ሺህ 077 አድርሶታል።
አርብ እለት የተመዘገበው ቁጥርም ከመጋቢት ወር ወዲህ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል።
በመጀመሪያው ዙር ወረርሽኝ ወቅት የተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር 7 ሺህ 578 ነበር።
በአገሪቷ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ሊጨምር እንደሚችልም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ እንዳለው በተከታታይ ሦስት ቀናት የተመዘገበው ቁጥር ከዕለት ተዕለት ያለውን የቫይረሱን ሥርጭት ያሳያል።
አርብ ዕለት የተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ሐሙስ ዕለት ከተመዘገበው 6 ሺህ 111 እና ረቡዕ ዕለት ከነበረው 5 ሺህ 429 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሬ አሳይቷል።
ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም በሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች እና የሞት ቁጥሩ በአንፃራዊነት ባለበት ነው የቆመው ማለት ይቻላል።
አዲስ በቫይረሱ እየተያዙ ያሉትም ለቫይረሱ እምብዛም ተጋላጭ ያልሆኑት ወጣቶችን መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አክሏል።
አርብ ዕለት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የ20 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን በአገሪቷ ያለውን የሟቾች ቁጥር 30 ሺህ 596 አድርሶታል።
በዚሁ ዕለት የተመዘገበው ቁጥር ይፋ ከተደረገ በኋላ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል በአገሪቷ ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ለሁለተኛ ጊዜ በመላ አገሪቷ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ አይቀርም ብለዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥታቸው አገሪቷ ኢኮኖሚዋን ለማንሰራራት እያደረገች ያለውን ጥረት ወደ ኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ገደቦች ዳግም እንዳይመለሱ እየሞከረ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ፕሬዚደንቱ ቫይረሱን ለመዋጋትም ዋናው እንቅስቃሴን መገደብ ነው በማለትም ሁሉም ሰው እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።















