የሰውን አንጎል ከማሽን ጋር የሚያገናኘው መሣሪያ

የሰው ልጆችን አንጎል ከማሽን ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዲኖረው የሚያስችል አሠራርን ሊያሳይ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤለን መስክ የሰው ልጆችን አንጎል ከማሽን ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዲኖረው የሚያስችል አሠራርን ሊያሳይ ነው።

ይህም ለሰው ልጆች የላቀ ችሎታ የሚያጎናጽፍ ሂደት ነው።

የሰው ልጆች አንጎል ላይ ምርምር በሚያደርገው የኤለን ተቋም ኒውራሊንክ ውስጥ በሰው ላይ ምርምር የተጀመረው አምና ነበር።

ኤለን የሚያሳየው ሂደት ሰዎች በአዕምሯቸው ስልክ ወይም ኮምፒውተር የሚቆጣጠሩበት ነው።

ኤለን እንደሚለው፤ የረዥም ጊዜ እቅዱ ለሰው ልጆች ላቅ ያለ ብቃት መስጠት ነው።

ሰዎች፤ ከሰው ሰራሽ ክህሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ጋር መተሳሰር እንዳለባቸው ያምናል። ይህም ሰው ሰራሽ ክህሎት ከሰው ልጆች በልጦ ሰዎችን እንዳያጠፋ ይረዳል ሲል ያስረዳል።

ኒውራሊንክ የተመሠረተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2017 ላይ ነው። ሳይንቲስቶችን ሲመለምልም ነበር።

ተቋሙ እየሠራው ያለው መሣሪያ ከ3,000 በላይ ኤሌክትሮዶች የያዘ፣ ከሰው ልጅ ጸጉር የቀጠነ ገመድ ጋር የተያያዘም ነው። መሣሪያው ከ 1,000 በላይ ኒውሮኖችን ማንቀሳቀስ ይችላል።

አምና ከተቋሙ የወጣ መግለጫ እንደሚጠቁመው በመሣሪያው ኮምፒውተርን በአንጎል መቆጣጠር እንዲቻል ዝንጀሮዎች ላይ ሙከራ ተደርጎበታል።

በየደቂቃው 192 ኤሌክትሮዶችን አንጎል ውስጥ የሚከት ሮቦትም ተሠርቷል።

የፒትስበርግ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጄኔፈር ኮሊንገር፤ ኤለን እየሞከረ ያለው ነገር ለሕክምና ቴክኖሎጂ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል።

“ኒውራሊንክ አስፈላጊው ግብዓት፣ ሳይንቲስቶች፣ ኢንጂነሮች አሉት። ሁሉም ለአንድ ግብ ስለሚሠሩ ውጤታማ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው።” ብለዋል።

ሆኖም ግን በቴክኖሎጂ ውጤት ሕክምናን የሚያግዝ መሣሪያ ለመሥራት ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅሰዋል።

በፔልሰንቬንያ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት አሪ ቤንጃሚን ለቢቢሲ እንዳሉት፤ የሰው ልጆች አዕምሮ ውስብስብ መሆኑ መሣሪያውን የማዘጋጀት ሂደቱን ሊያከብደው ይችላል።

“ኒውሮሊንኮች መረጃው አላቸው። ግን መተንተን ያስፈልጋቸዋል። አንጎል እንዴት እንደሚሠራ መሠረታዊ እውቀቱ የለንም። ይህም ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

የስፔስኤክስ እና የተስላ ባለቤት የሆነው ኤለን፤ በሕዋ ጉዞ፣ በኤሌክትሪክ በሚሠራ መኪናና በሌሎችም ፈጠራዎች የበርካቶችን ቀልብ መግዛት ችሏል።

በእርግጥ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ካስተዋወቀ በኋላ እውን ሆነው እስኪታዩ ጊዜ የወሰዱባቸው አጋጣሚዎች አሉ።