ቻድዊክ ቦስማን፡ የብላክ ፓንተር ፊልም ኮከብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ተዋናይ ቻድዊክ ቦስማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብላክ ፓንተር በተሰኘው ፊልም ላይ በነበረው ተሳትፎ በስፋት የሚታወቀው አሜሪካዊው ተዋናይ ቻድዊክ ቦስማን በ43 ዓመቱ በካንሰር ህመም አረፈ።

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው ብላክ ፓንተር ፊልም ድንበር ሳይለይ በርካቶችን አስደምሟል። በተለይ ለአፍሪካዊያንና ጥቁሮች ክብርን ያላበሰ ነበር ማለት ይቻላል።

ታዲያ ዛሬ በዚያ ፊልም ላይ በቴክኖሎጂ የዘመነ ከተማ ሆኖ በተሳለው ልብ-ወለዳዊ 'ዋካንዳ' መሪ በመሆን የተወነው እውቅ የፊልም ሰው ሕይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።

ቻድዊክ ሕይወቱ ያለፈው በሎስ አንጀለስ መኖሪያ ቤቱ ባለቤቱና ቤተሰቦቹ ከጎኑ ሳይለዩት መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨው መግለጫ ያመለክታል።

ተዋናዩ ከአራት ዓመታት በፊት የአንጀት ካንሰር ሕክምና ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም ይህን ግን በአደባባይ ተናግሮ አያውቅም። ደህና ነኝ ነበር የሚለው።

አሁን ግን በዚሁ በሽታ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

የሞቱ ዜናም አድናቂዎቹንና የፊልም ቤተሰቦችን አስደንግጧል። ዳሬክተር ጆርዳን ፒሌም " የሞቱ ዜና በጣም አሳዛኝ ነው" ብሏል።

"ቻድዊክ አልሸነፍ ባይ ነበር፤ ባለፈባቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖም የምትወዷቸውን በርካታ ፊልሞች ለእናንተ አቅርቧል" ያሉት ደግሞ ቤተሰቦቹ ናቸው።

"ቻድዊክ 21 ብሪጅስ፣ ዳ 5 ብለድስ፣ ኦገስት ዊለሶንስ ማ ሬኒይስ እና በርካታ ፊልሞችን ለተመልካቾች አድርሷል። እነዚህ ሁሉ የተቀረፁት በበርካታ ቀዶ ሕክምና እና ኬሞቴራፒ እየተከታተለ በነበረባቸው ፈታኝ ጊዜያት ነበር። በብላክ ፓንተር ፊልሙ ንጉሥ ቲ ቻላን እውን ስላደረገም ታላቅ ክብር ነው" ብለዋል ቤተሰቦቹ በሰጡት መግለጫ።

ብላክ ፓንተር

የፎቶው ባለመብት, Marvel Studios

ቻድዊክ እውነተኛ ሰዎችን ወክሎ በመጫዎትም ይታወቃል። የቤዝቦል ተጫዋቹን ጃኬ ሮቢንሰንን እንዲሁም የሶል ሙዚቃ አቀንቃኙን ጀምስ ብራውንን በመወከል ተውኗል።

በርካቶች ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በወጣው ብላክ ፓንተር ፊልሙ ይበልጥ ያስታውሱታል።

አፍሪካዊያን በቴክኖሎጂ በዘመነ ምድር ላይ ሲኖሩ የሚያሳየው ብላክ ፓንተር ፊልም ላይ የዋካንዳ ገዢ ሆኖ ነበር የተወነው።

በዚህ ፊልም ላይ በአተዋወን ብቃቱ ኮከብ ሆኖ የተመረጠ ሲሆን በዓለም አቀፍ ሲኒማ ከ1.3 ቢሊየን ዶላር በላይ ሽልማት አሸናፊም ሆኖ ነበር።

ባለፈው ዓመት ቻድዊክ "ፊልሙ ወጣትነት፣ ባለተሰጥኦን እና ጥቁር የመሆንን ትርጉም የለወጠ ነው" ብሎ ነበር።

ብላክ ፓንተር ፊልም በምርጥ ምስል ዘርፍ በኦስካር የታጨ የመጀመሪያው ፊልም ነው።

ቻድዊክ በካፒቴን አሜሪካ፣ ሲቪል ዋር፣ አቬንጀርስ በሚሉ ፊልሞችም ላይ የትወና ብቃቱን አሳይቷል።