ጃፓን፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በጤና እክል ምክንያት ሥልጣን ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በጤና ችግር ምክንያት ስልጣናቸውን እንደለቀቁ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንጀት ቁስለት [ulcerative colitis] ህመም ሳቢያ ለበርካታ ዓመታት እየተሰቃዩ ሲሆን በቅርቡ ሕመማቸው እየተባባሰ መምጣቱ ተገልጿል።
የጃፓኑ ብሔራዊ ቴሌቪዝን ጣቢያ ኤንኤችኬ እንዳለው የ65 ዓመቱ ሺንዞ አቤ መንግሥታቸው ላይ ችግር የሚፈጥር ነገር ማስወገድ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከ8 ዓመታት በፊት ሥልጣን ላይ የወጡት ሽንዞ አቤ ጃፓንን ለረዥም ጊዜ ያስተዳዳሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
አቤ፤ በፈረንጆቹ 2007 በተመሳሳይ ህመም ምክንትያ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሥልጣን ለቀው እንደነበር አይዘነጋም።
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ሆስፒታል የሄዱት አቤ፤ ጤናቸው አገሪቱን ለማስተዳደር የሚያሰችላቸው አይደለም የሚሉ ወሬዎች መሰማት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
የፓርቲያቸው ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደህና ናቸው፤ ምንም አልሆኑም በማለት ጤናቸውን በተመለከተ የተሰራጩ ወሬዎችን ሲያስተባብሉ ከርመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተለመከተ የወሰዷቸው እርምጃቸው አጥጋቢ አይደሉም ተብለው ሲተቹ ነው የከረሙት።
በጃፓን ሕግ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከለቀቁ፤ ምክትሉ ይተካሉ። የፋይናን ሚኒስቴሩ የሆኑት የአቤ ምክትል ታሮ አሶ ሥልጣን ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። እሳቸውን ተከትለው የካቢኔው ፀሐፊ ዮሺሂዴ ሱጋ ተሰልፈዋል።
ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሌላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪመረጥ ድረስ እያስተዳደረ ይቆያል።
ተጠባባቂ ጠ/ሚ ሥልጣን ላይ የሚቆየው ገዠው ፓርቲ አዲስ ፕሬዝደንት እስኪመርጥ ነው። ፓርቲው አዲስ መሪ ከመረጠ በኋላ የተመረጡት መሪ እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ አገሪቱን ያስተዳድራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ የሥልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው መስከረም 2014 ዓ.ም. [በፈረንጆቹ 2021] ነው።













