ጃፓን፡ ጋዜጠኛዋን የደፈረው 30 ሺ ዶላር ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጃፓን ፍርድ ቤት አንዲት ሴት ጋዜጠኛ ታዋቂው ጋዜጠኛ ደፍሮኛል ብላ ያቀረበችውን ክስ ተቀብሎ 3.3 ሚሊየን የን (30 ሾ ዶላር) ካሳ እንዲከፍል ብያኔ አስተላልፏል።
በአንድ የዜና ተቋም ውስጥ በጋዜጠኝነት የምትሰራው ሾሪ ኢቶ ኖሪዩኪ ያማጉቺ የተባለው ግለሰብ በአውሮፓውያኑ 2015 ራሷን በሳተችበት ወቅት እንደደፈራት በመግለጽ ክስ አቅርባ ነበር።
ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው አቃቤ ሕግ በእውነት ስለመደፈሯ ምንም ማስረጃ ማግኘት አልቻልንም ብለው ነበር። ሾሪ ኢዮ ግን ይግባኝ በመጠየቋ ክሱ እንደገና ሲታይ ቆይቷል።
የእሷ ጉዳይም ጾታዊ ጥቃቶች እምብዛም ወደ ሕግ በማይቀርቡባት ጃፓን በርካቶች ወደፊት እንዲመጡ አድርጓል።
የፍርድ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ'' በጣም ደስ ብሎኛል'' ብላለች የ30 ዓመቷ ሾሪ፤ 'ድል' የሚል ጽሁፍም በእጇ ይዛ ታውለበልብ ነበር።
በጃፓን የመደፈር ጥቃት ከሚደርስባቸው ሴቶች መካከል 4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ጉዳዩን ለፖሊስ እንደሚያሳውቁ በአውሮፓውያኑ 2017 የጃፓን መንግስት የሰራው ጥናት ያሳያል።
ሾሪ እንደምትለው ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር የቅርብ ግንኙት ያለው ታዋቂው ዘጋቢ ኖሪዩኪ ያማጉቺ በ2015 ስለአንድ የስራ ጉዳይ ለማውራት በማለት የእራት ግብዣ አድርጎላት ነበር።
'' የበላሁት ወይም የጠጣሁት ውስጥ መድሀኒት ሳይጨመርብት አልቀረም፤ ራሴን ስቼ ነበር። ከቆይታ በኋላ ስነቃ ግን አንድ ሆቴል ውስጥ ተኝቼ ኖሪዩኪ ያማጉቺ ከላዬ ሆኖ አገኘሁት።''
ኖሪዩኪ ያማጉቺ በወቅቱ በጃፓን ታዋቂ የዜና ወኪል የሆነው 'ቶክዮ ብሮድካስቲንግ ሲስተም' የዋሽንግተን ቢሮ ዋና ሀላፊ ነበር።
ጉዳዩን ለፖሊስ ካሳወቀች በኋላ ወደተደፈረችበት ሆቴል ተወስዳ ሁኔታው እንዴት እንደፈጠረ እንድታስረዳ መደረጓን ታስታውሳለች።
'' ፖሊሶቹ ወደ ሆቴሉ ከወሰዱኝ በኋላ ሰው የሚመስል አሻንጉሊት እላዬ ላይ ጭነው የሆነውን ነገር በሙሉ አስረጂን እያሉ ያዋክቡኝ ነበር። ደግሞ ሁሉም ፖሊሶች ወንዶች ነበሩ። በጣም አስጨናቂና አስፈሪ ሁኔታ ነበር'' ብላለች።
ሾሪ ለደረሰባት ጥቃት 11 ሚሊዮን የን (105 ሺዶላር) ካሳ ጠይቃለች። ተከሳሽ ደግሞ አልደፈርኩም በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነበር በማለት ስሜን ስላጠፋች 130 ሚሊዮን የን (1.1 ሚሊየን ዶላር) ካሳ ትክፈለኝ ብሎ ተከራክሯል።
ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ተከሳሽ ለሾሪ 3.3 ሚሊየን የን (30 ሾ ዶላር) ካሳ እንዲከፍል ብያኔውን አስተላልፏል።













