አሜሪካ፡ ትራምፕና ባይደን በፖርትላንድ በተፈጠረው አለመረጋጋት እየተወዛገቡ ነው

በፖርትላንድ በነበረው አለመረጋጋት ፖሊስ አንድን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ሲያውል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተቀናቃኛቸው ጆን ባይደን በፖርትላንድ ኦሪገን በተፈጠረው አለመረጋጋት ተጋጩ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፖርትላንድ ለተፈጠረው ሁሉ ተጠያቂው ዲሞክራቱ የከተማዋ ከንቲባ፣ ቴድ ዊለር፣ ናቸው ያሉ ሲሆን "ሞትና ውድመት ወደ ከተማዋ አምጥቷል" ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ጆ ባይደን ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕን "በግድየለሽነት አመጻን ያበረታታሉ" ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ቅዳሜ ዕለት በነበረው አለመረጋጋት የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎችና የጥቁር መብት ተሟጋቾች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።

በፈረንጆቹ ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ጆርጅ ፍሎይድ አንድ ነጭ ፖሊስ ማጅራቱ ላይ በጉልበቱ ቆሞበት ከተገደለ በኋላ የጥቁር መብት ተሟጋቾች በፖርትላንድ ተደጋጋሚ ሰልፎችን አድርገዋል።

የከተማዋ ከንቲባ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚሽከረከሩ ጽሁፎችን ከተመለከቱ በኋላ ወደ ከተማዋ ለበቀል የሚመጡ ሰዎችን አስጠንቅቀዋል።

"በትዊተር ላይ ወደ ፖርትላንድ ለበቀል እንደምትመጡ ዛሬ ማለዳ የገለፃችሁ ሰዎች እዚያው ባላችሁበት እንድትሆኑ እጠይቃለሁ" ብለዋል።

ከንቲባው ከፕሬዝዳንት ትራምፕ የተሰነዘረባቸውንም ነቀፌታ በማንሳት "ጥላቻን ያነገሱ እና መከፋፈልን የፈጠሩ" ሲሉ ተችተዋቸዋል።

"ፕሬዝዳንቱ ድጋፋቸውን ቢሰጡን አልያም ከዚህ ጉዳይ ቢርቁ እጅጉን ደስ ይለኛል" ብለዋል ከንቲባው።

አንዳንድ አክቲቪስቶች ከንቲባው ከተማዋ እንዲህ በአመጽ ስትናጥ ማስቆም አልቻሉም በማለት ስልጣናቸውን እንዲለቅቁ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ "ፖርትላንድ ይህንን ከንቲባ ይዛ ማገገም አትችልም" በማለት ወደ ከተማዋ የፌደራል ፖሊስ ለመላክ ሃሳብ አቅርበዋል።

አክለውም ጆ ባይደንን "ለመምራት ፈቃደኝነቱ የለውም" ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል።

ጆ ባይድን ደግሞ በምላሹ "ስለ ሕግና ሥርዓት ትዊተር ሰሌዳው ላይ መፃፍ ጠንካራ የሚያደርገው ይመስለዋል- ነገር ግን ይህ ደጋፊዎቹን ከግጭት እንዲታቀቡ ጥሪ ማስተላለፍ አለመቻሉ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ያሳያል" ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ተችተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በፓርቲያቸው በይፋ እጩ ሆነው የተመረጡ ዕለት ባደረጉት ንግግር ፖርትላንድ በዲሞክራቶች የምትመራ ሥርዓት አልበኝነት የነገሰባት ከተማ ሲሉ ጠቅሰው ነበር።

በዊስኮንሰን ባለፈው እሁድ ጃኮብ ብሌክ የተባለ ወጣት ሦስት ልጆቹ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው እየተመለከቱት በ7 ጥይት በፖሊስ መደብደቡ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዳግም ምርጫው የምረጡኝ ዘመቻቸው ዋነኛ ማጠንጠኛ ሃሳብ የሕግ የበላይነት ማስፈን ሲሆን ተቀናቃኛቸውን ዲሞክራቱን ጆ ባይደንን ወንጀል ላይ ቆራጥ አይደሉም ሲሉ ያጠለሿቸዋል።

ትራምፕ በመጪው ኅዳር በሚጠብቃቸው ምርጫ "ሥርዓት ማስከበርን" እንደ አጀንዳ ይዘው እንደሚሰሩበት ተናግረዋል።

"ዲሞክራቶች በሚበዙባቸው ከተሞች ሥርዓት አልበኝነት ነግሷል፣ ዝርፊያ ተጧጡፏል፣ ፖሊሶች እየተጎዱ ነው፤ ስለዚህ ይህን ጋጠወጥ ሁላ ልክ አስገባዋለሁ" ብለው ሲዝቱም ነበር፣ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት።

ከምርጫ ጋር በተያያዘ ዊስኮንሰን ግዛት ለየትኛው ፓርቲ ድምጽ እንደሚሰጡ ከማይታወቁት ግዛቶች አንዷ ናት።

ግዛቷ ቀድሞ ባራክ ኦባማ ያሸነፉባት በመሆኑ የዲሞክራቶች ግዛት ብትመስልም ትራምፕ በ2016 በ20ሺህ የድምጽ ብልጫ ሂላሪን ማሸነፋቸው ደግሞ ነዋሪዎቿ ቁርጥ ያለ የድጋፍ አቋማቸው አይታወቅም።

በኬኖሻ ከአንድ ሺህ በላይ ሰልፈኞች "የጥቁር ነፍስ ዋጋው ስንት ነው?" በሚል ቅዳሜ ሰልፍ ወጥተዋል።

የጄኮብ አባት ሰልፈኞች ከነውጥ፣ ከጥቃትና ካያልተገባ ድርጊት ራሳቸውን እንዲያቅቡ አደራ ብለዋል።

በኬኖሻ ከ1ሺህ በላይ የብሔራዊ ጥበቃ ልዩ ኃይል እንዲገባ ተደርጓል። ብዙዎቹ ታዲያ ከሌላ ግዛት የመጡ የልዩ ጥበቃ አባላት ናቸው።