ጄኮብ ብሌክ በሆስፒታል ታስሮበት የነበረው ካቴና ወልቋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ዊስኮንሲን ግዛት ፖሊሶች ከጀርባው ተኩሰውበት ሆስፒታል የገባው ጄኮብ ብላክ፤ ሆስፒታል ሳለ ታስሮ እንደነበረ መገለጹ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር። አሁን ከጄኮብ እጆች ላይ ካቴና መውለቁ ተዘግቧል።
የኪኖሻ ፖሊስ፤ ጄኮብ ከዚህ በፊት በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማዘዣ ወጥቶበት ስለነበረ እንደታሰረ ገልጿል።
ጠበቃው በበኩላቸው የእስር ማዘዣው እንደተሰረዘና ጄኮብን ይጠብቁ የነበሩ ፖሊሶች ከሆስፒታሉ እንደወጡ ተናግረዋል።
ጄኮብ ላይ ፖሊሶች ሰባት ጊዜ ከተኮሱበት በኋላ ሰውነቱን ማንቀሳቀስ ተስኖታል።
ክስተቱን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ላይ ሁለት ሰዎች በመግደል የተከሰሰው ወጣት የፍርድ ሂደቱ በአንድ ወር ተገፍቷል።
ካይል ሪተንሀውስ የተባለው የ17 ዓመት ወጣት ግድያን ጨምሮ ስድስት ክስ ይጠብቀዋል ተብሏል።
ወጣቱ “የኪኖሻ ህንጻዎችን ከተቃዋሚዎች መጠበቅ ሥራዬ ነው” ሲል ለጋዜጠኛ ተናግሯል።
ሰዎች አንድ መሣሪያ የያዘ ግለሰብን ሲያባርሩና መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ ሲተኩስባቸው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ ነው።
ጆሴፍ ሮሰንበርን የተባለ የ36 ዓመት ግለሰብና የ26 ዓመቱ አንቶኒ ኸበር ተገድለዋል።
ተኳሹ ኋላ ላይ እናቱ ቤት ሳለ በፖሊስ ተይዟል።
ለወጣቱ ጠበቃ ያቆመው ተቋም ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ለበርካታ ታዋቂ ሰዎች የተከላከለ ነው።
የጄኮብ ቤተሰቦች ምን አሉ?
የጄኮብ አባት “ልጄ ከሆስፒታል አልጋ ጋር በካቴና ታስሮ ማየት አሳዝኖኛል። የትም መሄድ አይችልም። ታዲያ ለምን በካቴና ያስሩታል” ብለዋል።
የኪኖሻ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ሉተነንት ኤሪክ ክሊንክሽመር፤ ጄኮብ የታሰረው ከዚህ ቀደም የእስር ማዘዣ ወጥቶበት ስለነበረ ነው ብለዋል።
አገረ ገዢው ቶኒ ኤቨርስ ጄኮብ ከሆስፒታል አልጋ ጋር በካቴና መታሰሩ አያሳስብዎትም ተብለው ሲጠየቁ፤ “ማሰር ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። ሰባት ጊዜ ከጀርባው የተተኮሰበት ሰው ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን የኪኖሻ ግዛት የፖሊስ ኃላፊ ከሥራ እንዲነሱ ጠይቋል። ኃላፊው “የነጭ የበላይነትን የሚደግፉ” እና “የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ሰዎችን የኮነኑ” ተብለዋል።
የከተማው ከንቲባ ግን የፖሊስ ኃላፊው እንደማይነሱ ተናግረዋል።
የተፈጠረው ምን ነበር?
ነገሮች ጄኮብ ላይ ወደመተኮስ እንዴት እንዳመሩ ገና በምርመራ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
የዊስኮንሰን ዓቃቤ ሕግ ጆሽ ኩዋል ፖሊሶች በቦታው የተገኙት “የወንድ ጓደኛዬ ያለሁበት ቦታ መምጣት ባይኖርበትም መጥቷል” የሚል ሪፖርት ስለደረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሦስት ፖሊሶች ጄኮብን ለማሰር አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመው ነበር። ከዛም ጄኮብ ወደ መኪናው ሲገባ ረስተን ሸስኪ የተባለ ፖሊስ ከጀርባው ሰባት ጊዜ ተኩሶበታል።
ፖሊሶች ከጄኮብ መኪና ስለት እንዳገኙ ገልጸዋል።
ጄኮብ ላይ የተኮሰውን ፖሊስ ጨምሮ ሌሎችም ፖሊሶች በጊዜያዊነት ከሥራ ታግደዋል።














