ጥቁሮች 'ባሪያ' እየተባሉ የሚጠሩባት አፍሪካዊት አገር

ሪም ኮግሊን እና ኢሳም አብዱልራሂም ለመገባት ሲወስኑ በቆዳ ቀለማቸውን ልዩነት ምክንያት ትችት ገጥሟቸዋል

የፎቶው ባለመብት, ALI AL-NAYER

የምስሉ መግለጫ, ሪም ኮግሊን እና ኢሳም አብዱልራሂም ለመገባት ሲወስኑ በቆዳ ቀለማቸውን ልዩነት ምክንያት ትችት ገጥሟቸዋል

ጋዜጠኛ ዘይነብ ሞሐመድ ሳሊህ በአገሯ ጥቁሮች ስለሚደርስባቸው መድልዎ ይህን ፅፋለች።

[ማሳሰቢያ፡ ይህ ፅሑፍ አንዳንድ ፀያፍ ቃላት የይዟል]

ከጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በኋላ ዘረኝነትን የሚቃወሙ ሰልፎች ዩናይትድ ስቴትስንና የተቀረውን ዓለም በናጡበት በአሁኑ ወቅት አገሬ ሱዳን ሌላ ዓለም ውስጥ ናት።

የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት ወይም #BlackLivesMatter የተሰኘው የማኅበራዊ ድር-አምባ የንቅናቄ ጥሪ በሱዳን እምብዛም ቦታ አልነበረውም።

በምትኩ ሰዎች ታዋቂው ሱዳናዊ እግር ኳሰኛ ኢሳም አብዱልራሂም ቀላ ያለች አረብ የሜክ-አፕ ባለሙያ የሆነችው ሪም ኮግሊን ሊያገባ መሆኑን ተከትሎ እየዘለፉት ይገኛሉ።

"የምርሽን ነው? ንግሥት ባሪያዋን ስታገባ. . . ይህ ሃራም [ሃጥያት] ነው።" ይላል አንድ ግለሰብ ፌስቡክ ላይ የፃፈው አስተያየት።

መሰል አስተያየቶች በርካታ ናቸው። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ዜጎች ራሳቸውን አረብ እንጂ አፍሪካዊ አይደለንም ብለው በሚያስቡባት ሱዳን ይህ ብዙም አስደናቂ አይደለም።

ሱዳን ሁሌም ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ባላቸውና አረብኛ በሚናገሩ ኃያላን ነው ስትገዛ የቆየችው። በደቡባዊና ምዕራባዊ ግዛት የሚገኙ ጥቁር ሱዳናዊያን ደግሞ መገለለና አድልዎ ሲደርስባቸው ከርሟል።

ጋዜጦች ጭምር ጥቁሮችን ለመግለፅ 'ባሪያ' እንዲሁም ሌሎች አስፀያፊ ቃላት ሲጠቀሙ ይስተዋላል።

ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ እስላማዊ አምደኛ፤ የቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር አል-ባሽር ደጋፊ እንደሆነ በሚታመነው በዕለታዊው አል-ኢንታባሃ ጋዜጣ ላይ 'ጋነርስ' የተሰኘ የታዳጊ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝን ባሪያ ሲል ገልጿታል።

አነስ ያሉ ጸረ ዘረኝነት ተቃውሞዎች ተካሂደው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አነስ ያሉ ጸረ ዘረኝነት ተቃውሞዎች ተካሂደው ነበር

በመዲናዋ ካርቱም ያሉ ሁሉም መገናኛ ብዙሃን ማለት ይቻላል የስርቆት ወንጀል ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የአረብ ዘር ስለሌባቸው 'ኒግሮ' ሲሉ ይጠሯቸዋል።

አብዱልራሂም እየደረሰበት ስላለው ጥቃት እንዲነግረኝ ስጠይቀው "የበለጠ ጥቃት እንዳይደርስብኝ በመፍራቴ ማኅበራዊ ገፆቼ ላይ ምንም ዓይነት ነገር መለጠፍ አስፈርቶኛል" ሲል ነግሮኛል።

ነገር ግን የ29 ዓመቱና የ24 ዓመቷ ባልና ሚስት የጫጉላ ሽርሽራቸውን በፌሰቡክ ቀጥታ ሲያስተላልፉ ነበር። 'ፍቅር ውስጥ ነው ያለነው፤ የቆዳ ቀለማችን እዚህ ቦታ የለውም' ሲሉም ተደምጠዋል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ለሴቶች መብት የሚከራከር ቡድን ኃላፊ የሆነች ሴት አንድ ወጣት ጥቁር ከነጭ አውሮፓዊት ሚስቱ ጋር ሆኖ የተነሳው ፎቶ ላይ 'ምናልባት ሚስት በዝንጀሮና በሰው መካከል ያለውን ፍጥረት እያፈላለገች ይሆናል' ስትል ፅፋለች።

ከዚህ በኋላ ግን የደረሰባትን ወቀሳ ተከትሎ ኢህሳን ፋጊሪ ከኃላፊነቷ ራሷን ለማግለል ብትወስንም ድርጅቱ ግን አስባ ያደረግችው አይደለም በሚል አልቀበለውም ብሏል።

ዘረኝነት ሱዳን ውስጥ በረቀቀ መንገድ ነው የሚቀርበው። አገሪቱ ነፃነቷን ካገኘች ጀምሮ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ሰዎች ጠቅላላ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ናቸው - ከአረብ እና ከኑቢያ ጎሳዎች።

ሁሉም የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ማለት ይቻላል ከእነዚህ ጎሳዎች የመጡ ናቸው።

ካርቱም ውስጥ ወደ አንድ ባንክ ወይም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ብትገቡ በጣም ጥቁር ሰዎች ነው የምትመለከቱት።

የሱዳን ባለሥልጣናት ያላቸው ሃብት ተዘርዝሮ ሊቀመጥ ይቅርና የሱዳን ሕዝብ በጎሳ ሲከፋፈል የሚኖረው ድርሻ በውል አልተቀመጠም።

ነገር ግን ለጥቁሮች መብት የሚከራከርና መቀመጫውን ዳርፉር ያደረገ አንድ ቡድን ካርቱም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ጥቁሮች ናቸው ይላል።

ቀደም ባለው ዘመን ሱዳን ዋነኛ የባሪያ ንግድ ማዕከል ነበረች

የፎቶው ባለመብት, UNIVERSAL HISTORY ARCHIVE

የምስሉ መግለጫ, ቀደም ባለው ዘመን ሱዳን ዋነኛ የባሪያ ንግድ ማዕከል ነበረች

ሱዳን ውስጥ ያለው ዘረኝነት በአውሮፓውያኑ 1821 ካርቱም የባሪያ መነገጃ እንደሆን ከመወሰኑ ይጀምራል። ሱዳን ለዘመናት የባሪያ ንግድ መናኸሪያ ነበረች።

በባርነት ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም እስካዛሬ ድረስ ስማቸው በበጎ ይነሳል። መዲናዋ ካርቱም መሃል የሚገኝ አንድ መንገድ ዘል-ዙቢር ፓሻ ራህማ ይሰኛል። ሰውዬው ከሱዳን አንስቶ እስከ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ቻድ ድረስ የባሪያ ንግድን ያስፋፋ ነው።

የታሪካ አጥኚዎች ግለሰቡ በተለይ ሴቶችን ከጥቁር አባይና ኑባ ተራሮች እንዲሁም ከኢትዮጵያ፤ ኦሮሚያ ክልል እየወሰደ ይነግድ እንደነበር ይናገራሉ።

እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በባርነት ንግድ ስም ያተረፉ ሰዎች ዛሬም ይንቆለጳጰሳሉ።

የባርያ ንግድ እስከ 2005 9 (እአአ) የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ድረስ እንደዘለቀ ይነገራል። ይህ የእርስ በርስ ጦርነት ጥቁር አፍሪካዊ ሱዳናውያን ከአረብኛ ተናጋሪ ሱዳናውያን ጋር እንዲለያዩ ምክንያት ሆኗል።

አሁንም ቢሆንም ጥቁሮች በሚኖሩበት የሱዳን ክፍል በደልና ግፍ እንደሚፈፀም በስፋት ይደመጣል። ከአል-ባሽር መውደቅ በኋላ ሥልጣን የያዘው ወታደራዊውና ሲቪል ጥምር መንግሥት ሱዳን ውስጥ ያለውን ሥር የሰደደ ዘረኝነት መታገል ስለመቻሉ ማስረገጫ የለም።

የአዲሱ መንግሥት አካል የሆነው ሱዳኒዝ ኮንግረስ ፓርቲ የጥላቻ ንግግርን የሚቀጣ ሕግ እያረቀቅኩ ነው ብሏል። ሕጉ ከፀደቀ ዘረኛ ቃላትን የሚጠቀሙ እስከ አምስት ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል።

የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ጥቂት ጥቁር ሱዳንውያን ግን ሁኔታዎች እጅግ ከባድ ናቸው ይላሉ።