ሱዳን ጦሩን በሚሳደቡ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሬያለሁ አለች

የሱዳን ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በሱዳን የመብት አቀንቃኞች፣ ጋዜጠኞች የሱዳንን ጦር ተሳድበዋል በሚል እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ጦሩ አስታውቋል።

ጦሩ ባወጣው መግለጫም ድርጊታቸው "ከትዕግስት አልፏል" ብሏል።

የመብት ታጋዮችና ጋዜጠኞች ባለፈው አመት በተደረገው ተቃውሞ የተገደሉ ሱዳናውያን ላይ የሚደረገውን ምርመራ ጦሩ እያደናቀፈ ነው በማለት ይተቹታል።

የሱዳን የጦር ኃይል በበኩሉ ይህ ውንጀላ ነው በማለት በፍፁም አልተቀበለውም ግድያዎቹን የፈፀሙ አካላት ለህግ ይቀርባሉም እያለ ነው።

ባለፈው ወር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን መንግሥታቸው ቃል የገባውን ለውጦችና ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንዲያደርግ እንዲሁም የሲቪል አመራሩም ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን እንዲይዝ ለመጠየቅ ተቃውሟቸውን ወደ ጎዳናዎች ወስደውት ነበር።

አገሪቷ ከሰሞኑ የተለያዩ ማሻሻያዎችንም ለህዝቧ አድርጋለች። ከነዚህም ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የአልኮል መጠጥ እንዲጠጡ ከመፍቀዷ በተጨማሪ ሐይማኖት የመቀየር መብት እንዲከበር አዛለች።

ከዚህም በተጨማሪ ዜጎቿ ለፈጸሙት 'ኢ-ሞራላዊ ተግባር' በአደባባይ እንዲገረፉ የሚያዘው ትዕዛዝ እንዲቆም ታውጇል።

ቀደም ሲል ሱዳን የሴት ልጅ ግርዛትን ሕገ ወጥ ድርጊት በማለት ከልክላለች።

ለረዥም አመታት ሱዳንን በማንቀጥቀጥ የገዟትን ፈላጭ ቆራጩን ኦማር አልበሽር ከስልጣን መገርሰስ ተከትሎ ሱዳን ከጦሩና ከሲቪል ማህበረሰቡ በተውጣጣ የሽግግር መንግሥት እየተመራች ትገኛለች።