ሱዳን የሴት ልጅ ግርዛት ላይ እገዳ ጣለች

የሴት ልጅ ግርዛት ሲፈጸም የብልት ከንፈሮችን እና ቂንጥርን መቁረጥን ያካትታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሴት ልጅ ግርዛት ሲፈጸም የብልት ከንፈሮችን እና ቂንጥርን መቁረጥን ያካትታል

ሱዳን የሴት ልጅ ግርዛት ወንጀል መሆኑን በመደንገግ ሲፈፅም የተገኘ ግለሰብ የሦስት ዓመት እስር እንደሚጠብቀው አስታወቀች።

ይህ የተገለፀው አዲስ ባሻሻለችው ሕግ ላይ መሆኑን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን ሕጉ የተሻሻለው ከአስር ቀን በፊት ነው ብሏል።

የሴት ልጅ ግርዛት ሆነ ተብሎ የሴት ልጅን የመራቢያ ክፍል አካል መቁረጥ ማለት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ብዙ ጊዜ የሴት ልጅ ግርዛት ሲፈጸም የብልት ከንፈሮችን እና ቂንጥርን መቁረጥን ያካትታል ይላል።

ሱዳን ይህ ተግባር በከፍተኛ ሁኔታ ከሚፈፀምባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷናት።

የተባበሩት መንግሥታት በዓለማችን በህይወት ያሉ ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እና ህጻናት ላይ በተለያየ ደረጃ የግርዛት ተግባራት ተፈጽሞባቸዋል ይላል።

የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ ያለው ወደ 27 በሚጠጉ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሲሆን፤ በእስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ አገራትም ውስጥ ድርጊቱ ይፈጸማል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከሆነ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውስትራሊያ እና በኒው ዚላንድ የሚኖሩ ስደተኞች ሕግን በመተላለፍ ሴት ልጆቻቸውን ያስገርዛሉ።

የሴት ልጅ ግርዛትን በሕግ ካገዱ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሞሪሺየስ፣ ማሊ፣ ላይቤሪያ፣ ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ኮትዲቯር፣ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ኒጀርና ናይጄሪያ ይገኙበታል።

የተባበሩት መንግሥታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም ጥሪ እያቀረበ ነው።

የግርዛት አይነቶች

አራት አይነት የግርዛት አይነቶች አሉ።

  • ክሊቶሪዲክቶሚይ (Clitoridectomy)፡ ይህ ማለት በቂንጥር እና በአከባቢው የሚገኝ ስስ ቆዳ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።
  • ኤክሲሺን (Excision)፡ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልትን የውስጠኛውን ከንፈር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።
  • ኢንፊቢዩሊሽን (Infibulation)፡ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልት ክንፈሮችን ቆርጦ በመጣል ብልትን በመስፋት ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ምቹ እንዳይሆን ማድረግ ማለት ነው። ይህ ተግባር የሚያስከትለው ህመም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል። በተጨማሪም ሽንት እና የወር አበባ ፍሳሽ በቀላሉ እንዳይወጣም ያደርጋል።
  • ሌላኛው የግርዛት አይነት የሴት ልጅ የመራቢያ አካላትን መውጋት፣ መብሳት፣ መቧጠጥ እና ማቃጠል የመሳሰሉትን ያካትታል።