የሴት ልጅ ግርዛት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አንድ ጥናት አመለከተ

በኬንያ አንዲት ገራዥ የምትገርዝበትን ምላጭ ስታሳይ

የፎቶው ባለመብት, Barcroft Media via Getty Images

በአፍሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሴት ልጅ ግርዛት በአስደናቂ ሁኔታ መቀነሱን አንድ ጥናት አመልክቷል፤ ለበርካቶችም የምስራች ሆኗል።

ቢ ኤም ጄ ግሎባል ሄልዝ በተባለው ገፅ ላይ የታተመው ጥናት እንደሚያሳየው በተለይ ከ14 ዓመት በታች በሆኑ ሴት ህፃናት በጣም ከፍተኛና ወሳኝ ለውጥ ታይቷል።

የሴት ልጅ ግርዛት የሴት ልጅን ብልት ውጫዊ ክፍል ሙሉ በሙሉ በመተልተል የሚወገድበት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው።

አንዲት ልጃገረድ ወደ ሴትነት የምትሸጋገርበት አንዱ ሒደት እንደሆነ ማህበረሰቡ ቢያምንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ሰብዓዊነት የጎደለውና አካልን የሚጎዳ ድርጊት እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ።

አብዛኛውን ጊዜ በግርዛቱ ሳቢያ በሚያጋጥም የደም በመፍሰስ አሊያም ኋላ ላይ በሚከሰት ቁስለት ሕይወታቸው የሚያጡ በርካቶች ናቸው።

ዓለም አቀፉ የህፃናት መርጃ ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት ኤጀንሲ መረጃ መሰረት በዓለም 200 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገረዶችና ሴቶች ተገርዘዋል።

አኃዙ እንደሚያሳየው ተገራዦቹ በአብዛኛው በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ይገኛሉ።

አኃዙ የሚያሳየው ምንድን ነው?

ከ28 ዓመታት በፊት ከ29 አገራት የተወሰደ መረጃ እንዳመለከተው በምስራቅ አፍሪካ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ እየቀነሰ መጥቷል።

ከ23 ዓመታት በፊት ከ14 ዓመት በታች የሆኑ 71 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊዎች ተገርዘዋል፤ ከሶስት ዓመታት በፊት ግን 8 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ግርዛት የተፈፀመባቸው።

ይህም በ63 በመቶ ያህል መቀነሱን ያሳያል።

በኬንያ ፣ታንዛኒያ ከ3- 10 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ሴቶች ይገረዛሉ፤ ይህም በአጠቃላይ ለመጣው ለውጥ መቀነስ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በሰሜን አፍሪካ ከ28 ዓመታት በፊት 60 በመቶ ሴቶች ይገረዙ የነበረ ሲሆን ከሶስት ዓመታት በፊት ይህ አሃዝ ወደ 14 በመቶ አሽቆልቁሏል።

በምዕራብ አፍሪካ ደግሞ ከ22 ዓመታት በፊት 74 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ሴቶች ግርዛት ሲፈፀምባቸው ከሁለት ዓመታት በፊት ቁጥሩ ወደ 25 በመቶ ዝቅ ብሏል።

ምንም እንኳን አጥኝዎቹ ታዳጊዎችና ወጣት ሴቶች ለድርጊቱ ተጋላጭ መሆናቸውን ቢያምንም የጥናቱ አካል እንዳልሆኑ አስታውቀዋል፤ ጥናቱ ከ14 ዓመት በታች ባሉ ህፃናት ላይ የተሰራ ነው።

በአፍሪካ ላይ ትኩረት ያደረገው አንድ የዘመቻ ቡድን ቃል አቀባይ ኢማ ላይቶለርስ እንደተናገሩት በአብዛኞቹ አገራት ቁጥሩ እየቀነሰ ቢሆንም አሁንም ዕድሜያቸው ከ 14 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ይገረዛሉ ብለዋል።

አፍላ ወጣቶች እንዲሁም ለጋብቻ የተዘጋጁ ሴቶችም ድርጊቱ እንደሚፈፀምባቸው ጨምረው ተናግረዋል።

በእንግሊዝና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎችን ያካተተተው የጥናት ቡድን ለህዝብና ጤና ጥናት እንዲሁም ለህፃናት መርጃ ድርጅት የተሰበሰቡ መረጃዎችን ተጠቅሟል። በዚህም መሰረት 210 ሺህ ህፃናት የጥናቱ አካል ሆነዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት እንዴት ቀነሰ ?

በእንግሊዝ ኖርተምብሪያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ኒጊያንጋ ባክዊን የአጥኝ ቡድኑ የሴት ልጅ ግርዛት የቀነሰበትን ምክንያት እንደዋና ጉዳይ ባይመለከተውም የእናቶች የአመለካካት ለውጥ መኖር አንዱ መላምት እንደሆነ ተናግረዋል።

በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይህንን ለውጥ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውም ለተመዘገበው እምርታ ምክንያት ሆኗል።

በኬንያ የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወም ከ11ዓመታት በፊት የተደረገ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኬንያ የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወም ከ11ዓመታት በፊት የተደረገ ሰልፍ

የሴት ልጅ ግርዛት

የሴት ልጅ ግርዛት የሴትን ልጅ ብልት ውጫዊ ክፍል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመተልተልና ቆርጦ በማውጣት የሚፈፀም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው።

በአፍሪካ ሰላሳ አገራት እንዲሁም በኤዥያና በመካከለኛው ምስራቅ የተወሰኑ አካባቢዎችም ይፈፀማል።

በዓለም በየዓመቱ ቁጥራቸው ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ታዳጊ ሴቶች ለድርጊቱ ተጋላጭ ይሆናሉ።

በአብዛኛው ድርጊቱ የሚፈፀመው ከጨቅላነት እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ነው።

ትክክለኛ ወሲባዊ ባህሪ እንድታሳይ፣ ታዳጊዎች ወደ ሴትነት እንድሸጋገሩና ለጋብቻ እንዲዘጋጁ ለማስቻል በሚል በማህበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት ድርጊቱ እንደሚፈፀምም በጥናቱ ተገልጿል።

የሴት ልጅ ግርዛት ከፍተኛ የመድማት፣ ሽንትን ለመሽናት መቸገር፣ ቁስለት ፣ መካንነት ፣ በወሊድ ጊዜ ለሚያጋጥም ውስብስብ የጤና ችግር ይዳርጋል። ለእናቶችና ለጨቅላ ህፃናት ሞትም ምክንያት ነው።