ግብፃዊቷ ታዳጊ በግርዛት መሞቷን ተከትሎ ቤተሰቦቿ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግብፃዊቷ የ14 አመት ታዳጊ ግርዛት እየተፈፀመባት ባለበት ወቅት ህይወቷ በማለፉ ፖሊስ ወላጆቿን እንዲሁም አክስቷን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ግርዛቱ የተፈፀመው 'አስዩት' በተባለች ግዛት ሲሆን ግርዛቱን አከናውኗል የተባለውም ዶክተር በእስር ላይ ነው። ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የታዳጊዋ አጎት ለባለስልጣናት በማሳወቁ ነው።
ግርዛት በግብፅ እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2008 ቢታገድም ሃገሪቷ የሴት ልጅ ግርዛት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚፈፀምባቸው ሃገራት ትመደባለች።
የዩኒሴፍ መረጃ እንደሚያሳየው ዕድሜያቸው ከ15-49 አመት ከሆኑ ሴቶች መካከል 87 በመቶዎቹ የተገረዙ ሲሆን፤ ከህዝቡም ግማሹ የሴት ልጅ ግርዛትን በሃይማኖት ከተቀመጡ መስፈርቶች ውስጥ አንዱ መሟላት ያለበት ግዴታ እንደሆነ የያስባል።
ናዳ አብዱል ማክሱድ የተባለችዋ ታዳጊ በአንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ ግርዛቱ በሚከናወንበት ወቅት በተፈጠረ መወሳሰብ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።
የታዳጊዋን ሞት ተከትሎ በግብፅ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።
ልጅነትና እናትነት ላይ የሚሰራው ብሄራዊ ጉባኤን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶችም ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች ወደ ፍርድ ሊቀርቡ ይገባል ማለታቸውን የግብፁ ሚዲያ 'አክህባር ኤል ዮም' አስነብቧል።
ግብፅ የሴት ልጅ ግርዛትን በወንጀልነት የደነገገችው እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2008 ሲሆን ከሶስት አመታት በፊትም አንዲት ታዳጊ በግርዛት መሞቷን ተከትሎ ቅጣቱ ጠበቅ እንዲደረግ ውሳኔ ተላልፏል።
ግርዛት እንዴት ይከናወናል?
- የሴት ልጅ ግርዛት የሴትን ልጅ ብልት ውጫዊ ክፍል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመተልተልና ቆርጦ በማውጣት የሚፈፀም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው።
- የተባበሩት መንግሥታት በዓለማችን በህይወት ያሉ ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እና ህጻናት ላይ የተለያየ ደረጃ ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል ይላል።
- ከፍተኛ የመድማት፣ ሽንትን ለመሽናት መቸገር፣ ቁስለት ፣ መካንነት ፣ በወሊድ ጊዜ ለሚያጋጥም ውስብስብ የጤና ችግር ይዳርጋል፤ ለእናቶችና ለጨቅላ ህፃናት ሞትም ምክንያት ነው።
- በአፍሪካ ሰላሳ አገራት እንዲሁም በእሲያና በመካከለኛው ምስራቅ የተወሰኑ አካባቢዎችም ይፈፀማል።
- በአብዛኛው ድርጊቱ የሚፈፀመው ከጨቅላነት እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ነው።
- ትክክለኛ ወሲባዊ ባህሪ እንድታሳይ፣ ታዳጊዎች ወደ ሴትነት እንዲሸጋገሩና ለጋብቻ እንዲዘጋጁ ለማስቻል በሚል በማህበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት ድርጊቱ ይፈፀማል።
ምንጭ፦ የአለም ጤና ድርጅት












