የሴት ልጅ ግርዛት ምንድነው? የት እና ለምን ይፈጸማል?

'ገራዟ' ተብላ የምትታወቀው ይህች ሴት ሞምባሳ ኬንያ ውስጥ ሴቶችን ለመግረዝ የምትጠቀምበትን ምላጭ ይዛ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, 'ገራዧ' ተብላ የምትታወቀው ይህች ሴት ሞምባሳ ኬንያ ውስጥ ሴቶችን ለመግረዝ የምትጠቀምበትን ምላጭ ይዛ።

የተባበሩት መንግሥታት በዓለማችን በህይወት ያሉ ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እና ህጻናት ላይ የተለያየ ደረጃ የግርዛት ተግባራት ተፈጽሞባቸዋል ይላል።

የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ ያለው ወደ 30 በሚጠጉ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ሲሆን፤ በእስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ ሃገራትም የሴት ልጅ ግርዛት ይፈጸማል። የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከሆነ በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ የሚኖሩ ስደተኞች ህግን በመተላለፍ ሴት ልጆቻቸውን ያስገርዛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም ጥሪ እያቀረበ ነው።

የሴት ልጅ ግርዛት አካላዊ እና አእምሯዊ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል የቦረና ማህብረሰብ አባል የሆነችው ቢሻራ ሼህክ ሃሞ ትናገራለች።

''የተገረዝኩት የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። አያቴ ግርዛት ንጹህ የሚያደርግ የሁሉም ሴት ልጅ ግዴታ እንደሆነ ትነግረኝ ነበር'' ትላለች ቢሻራ ሼክህ።

የሴት ልጅ ግርዛት ምንድነው?

የተባበሩት መንግሥትታት እንደሚለው በአፍሪካ፣ ኢሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ ቢያንስ 200 ሚሊዮን የሚሆኑ በህይወት ያሉ ሴቶች እና ህጻናት ተገርዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥትታት እንደሚለው በአፍሪካ፣ ኢሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ ቢያንስ 200 ሚሊዮን የሚሆኑ በህይወት ያሉ ሴቶች እና ህጻናት ተገርዘዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት ሆነ ተብሎ የሴት ልጅን የመራቢያ ክፍል አካል መቁረጥ ማለት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ብዙ ጊዜ የሴት ልጅ ግርዛት ሲፈጸም የብልት ከንፈሮችን እና ቂንጥርን መቁረጥን ያካትታል ይላል።

ኦምኒያ ኢብራሂም ግብጻዊት የፊልም ዳይሬክተር እና ጦማሪ ናት። ኦምኒያ ግርዛት በህይወቷ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ ትናገራለች። ማህብረሰቡ ያስተማረኝ ''የሰውነት ክፍል የግብረ ስጋ ግንኙነት አካልና ይህ ደግሞ ሀጢያት መሆኑን ነው። አእምሮዬ ውስጥ ሰውነቴ ሀጢያት እንደሆነ ነበር የምረዳው'' ትላለች።

ቢሻራ ሼክህ በግርዛት ምክንያት ከደረሰባት ችግር በመነሳት የሴት ልጅ ግርዛት እንዳይፈጸም የተለያዩ ቅስቀሳዎችን ታደርጋለች
የምስሉ መግለጫ, ቢሻራ ሼክህ በግርዛት ምክንያት ከደረሰባት ችግር በመነሳት የሴት ልጅ ግርዛት እንዳይፈጸም የተለያዩ ቅስቀሳዎችን ታደርጋለች

ቢሻራ ግርዛት እንዴት እንደተፈጸመባት ስታስታውስ፤ ''አራት ሴት ህጻናት አብረውኝ ተገርዘዋል። ዓይኔ ተሸፍኖ ነበር። ከዛ እጄን ወደኋላ አሰረች። ሁለት እግሮቼን ከፍተው ከያዙ በኋላ የብልቴን ከንፈር ቆርጣ ጣለች'' ስትል ታስታውሳለች።

የግርዛት አይነቶች

አራት አይነት የግርዛት አይነቶች አሉ።

  • ክሊቶሪዲክቶሚይ (Clitoridectomy)፡ ይህ ማለት በቂንጥር እና በአከባቢው የሚገኝ ስስ ቆዳ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።
  • ኤክሲሺን (Excision)፡ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልትን የውስጠኛውን ከንፈር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።
  • ኢንፊቢዩሊሽን (Infibulation)፡ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልት ክንፈሮችን ቆርጦ በመጣል ብልትን በመስፋት የግብረ ስጋ ግንኙነት ምቹ እንዳይሆን ማድረግ ማለት ነው። ይህ ተግባር የሚያስከትለው ህመም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል። በተጨማሪም ሽንት እና የወር አበባ ፍሳሽ በቀላሉ እንዳይወጣ ያደርጋል።
  • ሌላኛው የግርዛት አይነት የሴት ልጅ የመራቢያ አካላትን መውጋት፣ መብሳት፣ መቧጠጥ እና ማቃጠል የመሳሰሉትን ያካትታል።

የሴት ልጅ ግርዛት ለምን ይከሰታል?

አንዳንድ የኬንያ ማያሳ ሴቶች ዘንድ ያልተገረዙ ሴቶች የትዳር አጋር አያገኙም ወይም ከበርካታ ሰዎች ጋር የወሲብ ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአንዳንድ የኬንያ ማያሳ ሴቶች ዘንድ ያልተገረዙ ሴቶች የትዳር አጋር አያገኙም ወይም ከበርካታ ሰዎች ጋር የወሲብ ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

የሴት ልጅ ግርዛት ከሚፈፀምባቸው የተሳሳቱ ምክንያቶች መካከል የማህብረሰብ አስተሳሳብ፣ ኃይማኖት፣ ከንጽህና ጋር የተያያዘ የተሳሳተ ዕምነት፣ ድንግልናን ለማቆየት በማሰብ፣ ሴት ልጅ ትዳር እንድታገኝ በማሰብ እና የወንድ ልጅ የወሲብ እርካታን ለመጨመር ይገኙበታል።

በበርካታ ማህብረሰብ ዘንድ ሴት ልጅ የምትገረዘው ለትዳር እንደ ቅድመ ዝግጅት ስለሚወሰድ ነው።

ምንም እንኳ ግርዛት ለንጽህና የሚያበርክተው አስተዋጽኦ በሳይንስ ባይረጋገጥም፤ ያልተገረዙ ሴቶች ጤነኛ እና ንጹህ ያልሆኑ ተደርገው በበርካታ ማህብረሰብ ዘንድ ይታሰባሉ።

የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሃገራት
የምስሉ መግለጫ, የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሃገራት

የሴት ልጅ ግርዛት የት ይፈጸማል?

የሴት ልጅ ግርዛት በበርካታ የዓለማችን ሃገራት የተከለከለ ተግባር ቢሆንም አሁንም በየቀኑ በተለያየ ሃገራት ይፈጸማል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ምንም እንኳ የሴት ልጅ ግርዛት በ29 የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ውስጥ በህግ የተከለከለ ቢሆንም በ24 ሃገራት ውስጥ በስፋት እንደሚፈፀም ይጠቁማል። በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ የሚኖሩ ስደተኞች ህግን በመተላለፍ ሴት ልጆቻቸውን እንደሚያስገርዙም እኚህ መረጃዎች ያሳያሉ።

በምዕራባውያን ሃገራት የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸመው በጨቅላ ህጻናት ላይ በመሆኑ ጨቅላዎቹ ወደ ትምህርት ቤት ስለማይሄዱ እና ከእድሜያቸው አንጻር ሪፖርት ማድረግ ስለማይችሉ ተግባሩ እንደተፈጸመባቸው ማወቁ ከባድ መሆኑ ተጠቅሷል።