በአሜሪካ የትራምፕ ደጋፊዎችና የጥቁር መብት ሰልፈኞች ተጋጩ

የሕክምና ባለሙያዎች ግጭቱ በተፈጠረበት ስፍራ የተጎዱ ሰዎችን ህይወት ለማዳን ርብርብ ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት ሁለት ተጻራሪ ሰልፈኞች ለተቃውሞና ድጋፍ አደባባይ ወጥተው በመጋጨታቸው አንድ ሰው ተተኩሶበት ሞቷል፡፡

ሰልፈኞቹ ግማሾቹ ዶናልድ ትራምፕና የሚደግፉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የጥቁር መብት ተሟጋቾች ናቸው፡፡

ግጭቱ የተከሰተው በፖርትላንድ ከተማ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖርትላንድ ጎዳናዎች ተመሳሳይ ግጭቶች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ነበር፡፡

በተለይም በግንቦት 25 ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ ማጅራቱ ታንቆ ከተገደለ በኋላ የጥቁር መብት ተሟጋቾች በፖርትላንድ ተደጋጋሚ ሰልፎችን አድርገዋል፡፡

በሐምሌ ወር ዶናልድ ትራምፕ የልዩ ኃይል አባላትን ወደዚች ከተማ ፖርትላንድ መላካቸው ይታወሳል፡፡

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ደግሞ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ወደ አደባባይ መውጣት ጀምረዋል፡፡ የዛሬው ሦስተኛ ጊዜያቸው ነው፡፡

የፖርትላንድ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አንድ ሰው ደረቱ ላይ በጥይት ተመትቶ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ መሞቱ ተረጋግጧል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በፓርቲያቸው በይፋ እጩ ሆነው የተመረጡ ዕለት ባደረጉት ንግግር ፖርትላንድ በዲሞክራቶች የምትመራ ሥርዓት አልበኝነት የነገሰባት ከተማ ሲሉ ጠቅሰው ነበር፡፡

በዊስኮንሰን ባለፈው እሁድ ጃኮብ ብሌክ የተባለ ወጣት ሦስት ልጆቹ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው እየተመለከቱት በ7 ጥይት በፖሊስ መደብደቡ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ዊስኮንሰን ግዛት ኬኖሻ ከተማ ማክሰኞ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡