ኢላን መስክ በአሳማ ጭንቅላት ላይ የኮምፒወተር ቅንጣት የገጠመው ምን አስቦ ነው?

ገርትሩድ የተሰኘችው አሳማ
የምስሉ መግለጫ, ገርትሩድ የተሰኘችው አሳማ ጭንቅላት ውስጥ የኮምፒውተር ቅንጣት ተገጥሟል

የሕዋ ታክሲ (ስፔስ ኤክስን) ፈጥሯል፡፡ ቴስላን አስተዋውቋል፡፡ ፔይፓልም የሱ ሥራ ነው፡፡ የዓለም 31ኛው ሀብታም ነው፡፡ 97 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፣ ሀብቱ፡፡

አሁን ደግሞ በአንዲት አሳማ ጭንቅላት ውስጥ የኮምፒውተር ቅንጣት (computer chip) ገጥሞላታል፡፡

ይህን ያደረገው በኮምፒውተር የሚታገዝ የሰው ልጅ ጭንቅላት ለመፍጠር ያለውን ሕልም እውን ለማድረግ ነው፡፡

ከደቡብ አፍሪካ ወደ ካናዳ በልጅነቱ ከሄደ በኋላ በተማሪነት ወደ አሜሪካ አቀና፡፡ አሁን ዓለማችንን በምድርም በሰማይም በቴክኖሎጂ እየናጣት ይገኛል፡፡ ዕድሜው ገና 50 አልደፈነም፡፡ የሚኖረው በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ነው፡፡

7 ልጆች አሉት፡፡

ሰሞኑን ስሙ የተነሳው አዲስ የፈጠራ ሙከራ በመጀመሩ ነው፡፡ ሳንቲም የምታህል የኮምፒውተር ቅንጣት የእንሰሳ ጭንቅላት ውስጥ ገጥሟል፡፡

አሳማ ናት፡፡ ስሟ ገርትሩድ ይባላል፡፡ ሐሳቡ የሰው ልጅ ወደፊት ጭንቅላቱ በኮምፒውተር እንዲታገዝ ማስቻል ነው፡፡

‹‹ልክ አእምሮ ላይ ትንሽዬ የእጅ ሰዓትና ኤሌክትሪክ የማስቀመጥ ያህል ነው›› ብሏል ቢሊየነሩ ፈጣሪ ኢላን መስክ በዌብካስት፡፡

ኒውራሊንክ የሚባለው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኩባንያው ይህንን አሁን በአሳማ የሞከረውን ቀጥሎ በሰዎች ላይ ሙከራ ለማድረግ እንዲፈቀድለት ባለፈው ዓመት ማመልከቻ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡

ሐሳቡ ተግባራዊ ሲደረግ የነርቭ ችግር ያለባቸው ሰዎች ስልክና ኮምፒውተርን እንዲሁም ሌሎች ማናቸውም ተግባራትን በአእምሯቸው በማሰብ ብቻ እንደ ማንኛውም ጤነኛ ሰው ማዘዝ ይችላሉ፡፡

ቢሊየነሩ ፈጣሪ ኢላን መስክ ተስፋ የሚያደርገው ወደፊት የሰው አእምሮ ውስጥ የሚገጠመው ኮምፒውተር-ቅንጣት፣ ሕይወትን ከማቅለሉም በላይ ፓርኪንሰንና ህብለ ሰረሰር ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን ያድናል፡፡

የቢሊየነሩ ኢላን መስክ የረዥም ጊዜ ህልሙ የሰው ልጅን የላቀ ፍጡር ወይም ልዕለሰብ ማድረግ ነው፡፡

መስክ እንሚያስበው የሰው ልጅ ወደፊት የሚጠፋው በሰው ሰራሽ ክህሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) መወሳሰብ ነው፡፡

ይህንን መቋቋም የሚቻለው ደግሞ ልዕለ-ሰብ በመፍጠር ነው፡፡ ልዕለ-ሰብ የሚፈጠረው ደግሞ በኮምፒውተር በሚታገዝ አእምሮ ብቻ ነው፡፡

ግርቱሩድ የተሰኘቸው አሳማ ሳንቲም መጠን ያለው ኮምፒውተር ፍላሽ ከተገጠመላት በኋላ በካሜራ ክትትል ተደርጎላታል፡፡

መጀመርያ ትንሽ የመወዛገብ ነገር ቢታይባትም በኋላ ግን ሕይወቷን ቀጥላለች፡፡ ገለባ አሽትታ ስትቀምስ የነርቭ እንቅስቃሴዋና ስሜቷ በተገጠመላት ኮምፒውተር አማካኝነት ክትትል ሲደረግለት ነበር፡፡

አሳማዋ ምግብ ስትሻ በጭንቅላቷ የተገጠመላት ማሽን ቀድሞ ምልክቶችን ማሳየት ችሏል፡፡

ይህ ኒውትራሊንክ የሚባለው ቅንጣት እጅግ ደቂቅ የሆኖ ክሮች እንዲኖርት ተደርጎ ነው የተመረተው፡፡ ከፀጉር ውስጥ ቢሰካ መለየት አይችልም፡፡ ከጸጉርም የቀጠኑ ክሮችን ነው የተደረጉለት፡፡

ይህ ቅንጣት 3ሺህ ኤሌክትሮድሰን የያዘ ሲሆን ከሰው ጸጉር የቀጠኑ ተጣጣፊ ክሮች አንድ ሺህ የአእምሮ ኒውሮንስን መቆጣጠር ይችላሉ ተብሏል፡፡

ባለሙያዎች የሰው ልጅ አእምሮ መጀመርያ እንዴት ይሠራል የሚለውን ጠንቅቀን ሳናውቅ አእምሮ ላይ ቅንጣት መግጠም ያለውን ፋይዳ በጥርጣሬ ይመለከቱታል፡፡

አሳማዋ የኮምፒውተር ቅንጣት ተገጥሞላት ሳለ ከሌሎች አሳማዎች በተለየ ምንም የሆነችው ነገር ባለመኖሩ አንድ የሳይንስ እርምጃ ተደርጎ ታይቷል፡፡

ይህም ምናልባት ወደፊት የሰው ልጆች አንጎል ተከፍቶ ሳንቲም የምታክል ቅንጣት ቢጨመርበት አደጋ አይፈጥር ይሆናል የሚል ተስፋን አሳድሯል፡፡

የሰው ጭንቅላት ውስጥ ኒውሮሲግናሎችን ማንበብ የሚችል ቅንጣት ተገጠመ ማለት ሰዎች ቴሌቪዥን ቻናል ለመቀየር፣ እጅ የሌላቸው ሰዎች ማሸን የተገጠመላቸውን ማሽን ለማዘዝ፣ ወይም በኮምፒውተር ለመተየብ ጣቶች አያስፈልጉ ይሆናል፡፡ ፍላጎቱን ማሰብ ብቻ በቂ ነው፡፡