"የባይደን መምጣት ትራምፕ ግድቡን በተመለከተ ይሰጡት የነበረውን ባዶ ተስፋ ይቀንሳል"

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ከሳምንታት በፊት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አወዛጋቢ የተባለውን ግብፅ "ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች" ብለው መናገራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማብራሪያ ጠይቃለች።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ ለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንግግሩን በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል፤ በበርካታ ኢትዮጵያውያንም ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። ከሳምንት በፊት በተካሄደው የአሜሪካ ምርጫ የዴሞክራት እጩው ጆ ባይደን ማሸነፋቸው ይፋ ተደርጓል። የጆ ባይደን ማሸነፍ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሦስትዮሽ ውይይት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖር ይሆን? የምሥራቅ ናይል ቴክኒካዊ አህጉራዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ቢቢሲ፡ የጆ ባይደን ማሸነፍ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሦስትዮሽ ውይይት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ?

አቶ ፈቅአሕመድ፡ የአገር ፖሊሲ ስለሆነ የፖሊሲ ለውጥ አይኖርም። አሜሪካ ከግብፅም ከኢትዮጵያ ጋርም አጋርነት ስላላት ማስቀየም አትፈልገም። ማስቀየም ካለባት ግን ግብፅን ማስቀየም አትፈልግም። ትራምፕ እንደሚሉት ግድቡን ማፍረስ ወይም ማውደም በተበላሸ ዲዛይን የተገነባ ሪልስቴት እንደማፍረስ ነው። ግድቡን ማፍረስ ተከትሎ የሚመጣውን ብጥብጥ፣ ረብሻ እና እልቂትን አላሰቡም። ባይደን ሲመጡ ይህንን ንግግር ተከትሎ የሚመጣው ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። ባይደን ከ40 ዓመት በላይ በፖለቲካው ቆይተዋል። ከኦባማ ጋር ሰርተዋል። አፍሪካን መረዳታቸውና ከግል ባህሪያቸው አንጻር ንግግሩ የሚያመጣው ተጽዕኖ ይቀረፋል። በአገራቶቹ መካከል ያለውን ልዩነት ስንመለከት በተለይ የአሜሪካ መሪዎች ግድቡን በተመለከ መፍትሔ ያመጡልናል የሚል እምነት ስላለ። በተለይ [ግብፆች] ፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ ትልቅ እምነት ነበራቸው። ስለዚህ ወደ ስምምነት የመቅረብ ፍላጎት አያሳዩም ነበር። ባይደን መምጣታቸው ትራምፕ ይሰጣቸው የነበሩ ባዶ ተስፋና ድጋፍን ይቀንሳል። ስለዚህም አገራቱ በተሻለ ሁኔታ የመነጋገርና ፍላጎቱ ካላቸው ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲመጡ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ።

ቢቢሲ፡ የትራምፕ ንግግር ግብፅ ግድቡ ላይ ጥቃት እንድትሰነዝር በማደፋፈር፣ በድርድሩ ያላትን አቋም በመቀየር ወይም በሌላ መንገድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

አቶ ፈቅአሕመድ፡ የግብፅ መሪዎች ግድቡን በተመለከተ መፍትሔ እናገኛለን ብለው የሚያስቡት ከምዕራባውያን አገራትና መሪዎች ነው። በተለይ ትራምፕ መፍትሔ ይሰጣል የሚል እምነት አላቸው። የትራምፕ ንግግር ግብፆችን ልባቸውን ከማሞቅ ድርድሩ ላይ በፊት የነበራቸውን ያለመስማማት ፍላጎት ከማጠናከር ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም። ያው ግብፆች ግን ንግግሩን በመስማት አሜሪካ ከጎናችን ነች በማለት በፊት ከነበራቸው አቋም ትንሽ ጠንከር ያለ አቋም ይዞ የመምጣት ሁኔታ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። በፊት ከጠየቁት የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝላቸው አቋም ይዘው የመምጣት ሁኔታ ይኖራል። የትራምፕ አለመኖር እነሱ እንደ ድጋፍ የሚወስዱትን ባዶ ተስፋ ያስቀራል የሚል እምነት አለኝ። ከዛ ውጪ በግድቡም ሆነ በድርድሩ ሂደት ላይ ምንም ተጽዕኖ አይኖረውም።

ቢቢሲ፡ አሜሪካ እንዲሁም የዓለም ባንክ በሦስትዮሽ ድርድሩ ጣልቃ መግባታቸው ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አሉ። እርስዎ ደግሞ የባይደን መኖር አገራቱ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲመጡ ሁኔታዎች ሊያመቻች ይችላል ያሉትን ነጥብ ያብራሩልን።

አቶ ፈቅአሕመድ፡ በወሰን ተሻጋሪ ውሃ (በተለይ በናይል ውስጥ) የሦስተኛ አካል ተሳትፎ አይደገፍም። ሦስተኛ አካል ወደ ድርድሩ ሲመጣ የራሱን ጥቅም ለማስከበር ነው። የራሱ ፍላጎት አለው። ያ የሱ ፍላጎት ደግሞ ከአገራቱ ፍላጎት ጋር እንደማይጣጣም የታወቀ ነው። አገራቱ ልዩነት ቢኖራቸውም ልዩነታቸውን አጥብበው መስማማት ይችላሉ። ምክንያቱም የራሳቸው ፍላጎት፣ ስጋትና ፍርሀት አላቸው። በወንዙ ተሳስረዋል። ተለያይተው መኖር አይችሉም። ስለዚህ ልዩነታቸውን መፍታት አለባቸው። ሦስተኛው አካል ግን ፍላጎቱ በፍጹም ከነዚህ አገራት ጋር አይጣጣምም። የሶስተኛውን ፍላጎት ለመሳካት በሚያደርገው ጥረት በአገራቱ መካከል አንዳንዴ አላስፈላጊ ግጭት መፍጠር ይችላል። ስለዚህ ሦስተኛ አካል ባይገባና አገራቱ ራሳቸው ልዩነታቸውን አጥብበው ወደ ስምምነት ቢመጡ ይመረጣል።

የባይደን መመረጥ በአገራቶቹ መካከል መስማማት ሊያፋጥን ይችላል ያልኩት በሂደቱ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ሳይሆን ጣልቃ ባለመግባት ነው። ባይደን ጣልቃ አይገቡም የሚል እምነት አለኝ። ጣልቃ ቢገቡም ትራምፕ እንዳደረጉት ገፍተው ሄደው፣ የአንድን አገር ሉዓላዊ መብት ጨፍልቀው ወይም በአገራቱ መካከል መጨረሻ የሌለው ግጭት እንዲነሳ የሚያበረታታ ንግግር አያደርጉም። አንድን አገር ለይተው ድጋፍ ካልሰጡ አገራቱ የሚደራደሩት በተስተካከለ ሜዳ ላይ፣ ሁሉም ተመሳሳይ አቋም ይዘው ይሆናል። ስለዚህም በቀላሉ ልዩነታቸውን ሊፈቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ባይደን በዚ ሁደት ቢሳተፉ የአገሪቷ ፖሊሲ ስላለ ማድላታቸው ስለማይቀር ያው ተመልሶ ልዩነቱ እየሰፋ ነው የሚሄደው። ስለዚህ እሳቸው ስምምነቱን የሚያፋጥኑት ጣልቃ ባለመግባት ነው።

ቢቢሲ፡ አሜሪካ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገችው ሱዳንን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር የማውጣት እቅድ አለ። ይህ ደግሞ በምጣኔ ሀብቷ ላይ ልዩነት ሊፈጥር ይችላል። ባለፈው ትራምፕ ከተናገሩት በመሳት ደግሞ በአሜሪካ በኩል፤ ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታሳድር የመግፋት ነገር ሊኖር እንደሚችል መረዳት ይቻላል። ይህ አዝማሚያ በባይደን አስተዳደርም የሚቀጥል ነው?

አቶ ፈቅአሕመድ፡ አሜሪካ ሱዳንን ሽብርተኛን የምትደግፍ በሚል ማዕቀብ በመጣል የአገሪቷን ኢኮኖሚ ስታሽመደምድ እና አገሪቷንም ከፍተኛ ብጥብጥ ውስጥ ስትከት ነበር። ያ እንደ አገር የሚከተሉት ፖሊሲ ነው። ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ሱዳንን ከዚህ ዝርዝር ውስጥ እናወጣሻለን፣ ማዕቀቡንም እናነሳለን፣ የኢኮኖሚ ግንኙነትም እናጠናክራለን፤ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ፍጠሪ የሚለው ግን ፕሬዘዳንት ትራምፕ የጨመሩበት አቅጣጫ ነው። የአገር ፖሊሲ አይደለም። ስለዚህ በጣም ዝርዝር ጉዳይ ስለሆነ የፖሊሲ ጉዳይም አይሆንም። ትራምፕና መንግሥታቸው ግብፅን ለመጥቀም አልፎም በሱዳን እና እስራኤል መካከል ስምምነት ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ያለ ነው። በተለይም ትራምፕ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም መካከል ሰላም ለማውረድ ያዘጋጁት ስምምነት ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርጉት ጥረትም አካል ነው። አሁን በሱዳን ላይ እያሳደሩ ያሉት ጫና ግብፅን ለመጥቀም ሲባል ፕሬዘዳንት ትራምፕና መንግሥታቸው የተከተሉት አቅጣጫ ነው እንጂ የአሜሪካ መንግሥት ፖሊሲ ነው የሚል እምነት የለኝም።

ቢቢሲ፡ ግብፅ ከምትተችባቸው ነገሮች አንዱ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ፖለቲካ የግድቡ ግንባታ ወይም ድርድሩ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መጠቀሟ ነው። አሁን ደግሞ የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በግድቡ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

አቶ ፈቅአሕመድ፡ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በናይል ተፋሰስ አገራት ላይ ከምትከተላቸው በርካታ ስልቶች ውስጥ አንደኛው የተፋሰሱን አገራት ደካማ፣ ተጋላጭና ያልተረጋጉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በተለይ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ አንድም አገራቶቹ ልማት ላይ ያላቸውን ትኩረት ይቀንሳሉ፤ የጀመሩትን ያቆማሉ የሚል እምነት አላቸው። ስለዚህ ያንን አለመረጋጋት ለማበረታታት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ስለዚህ በዚያ በኩል የራሳቸውን እንቅስቃሴ ያደርጋሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ። ይሁን እንጂ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚመጣ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አይኖርም። ምክንያቱም የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለየ ሁኔታ የሚታይ ስለሆነ። ከዚያ ውጭ ድርድሩ ይቀጥላል። ከድርድሩ ጋር ይህም ቢሆን ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም። በእነሱ እምነት ይህ ሁኔታ ለነሱ ትልቅ ዕድል እንደሚሰጣቸው አድርገው ነው የሚወስዱት። መሬት ላይ ስንወርድ ግን እምብዛም ተፅዕኖ ያለው አይመስለኝም።

ቢቢሲ፡ ድርድሩ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ በድጋሚ መጀመሩ ይታወሳል። አሁን ድርድሩ ምን ላይ ይገኛል?

አቶ ፈቅአሕመድ፡ ባለኝ መረጃ አሁን እየተናገጋገሩ ያሉት አደራዳሪ ወይንም አሸማጋይ በሆነው የአፍሪካ ሕብረት ሚና ላይ ነው። የአፍሪካ ሕብረት ሚና ምን ይሁን? የሚለው ላይ ሦስቱ አገራት ተነጋግረው መስማማት አልቻሉም። በተለይ ኢትዮጵያና ሱዳን በድርድሩ ውስጥ ሕብረቱ የተሻለ ሚና እንዲኖረው ይፈልጋሉ። ግብፅ ግን የአፍሪካ ሕብረት የተሻለ ሚና ይቅርና አደራዳሪ እንዲሆንም አትፈልግም። ምክንያቱም የአፍሪካ ሕብረት እንደ አሜሪካ መንግሥት ወይም እንደ ትራምፕ መንግሥት ለነሱ አድልቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚነካ፣ የወደፊት በውሃው የመጠቀም ተስፋ የሚያጨልም ስምምነት እንድትፈርም ያስገድዳታል የሚል እምነት የላቸውም። ስለዚህ ግብፆች የአፍሪካ ሕብረት ባይሳተፍ ይመርጣሉ። አልተስማሙም እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ነው እየተነጋገሩ ያሉት።