ኦባማ፣ ቡሽና ክሊንተን በቲቪ መስኮት እየታዩ ሊከተቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንቶች ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ እና ቢል ክሊንተን በቴሌቪዥን መስኮት እየታዩ የኮቪድ-19 ክትባት ለመወጋት ቃል ገብተዋል።
ሶስቱ የቀድሞ መራሄ መንግሥታት ክትባቱ በአሜሪካ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ ካገኘ በኋላ ክንዳችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ሁለቱ ዴሞክራቶች ኦባማና ክሊንተን እንደሁም ሪፐብሊካኑ ቡሽ በጤና ሙያ ጥርሳቸውን የነቀሉ ሰዎችን ይሁንታ ካገኙ በኋላ ነው የሚከተቡት።
የቀድሞዎቹ መሪዎች ይህን ለማድረግ የቆረጡት ሕዝቡ በክትባት ላይ ያለው እምነት እንዲፀና በማሰብ ነው።
ከዚህ ቀደም የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያመክቱት አሜሪካዊካዊያን በክትባት ጉዳይ ልግምታም ናቸው።
ብዙዎቹ ክትባት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤ ሲቀጥል ምን እንደሚሰጠን በምን እናውቃለን የሚል ጥርጣሬ አላቸው።
ለምሳሌ ባለፈው ጥቅምት የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እንደሚጠቁመው ከ10 አሜሪካውያን ስድስቱ ክትባት ለመውሰድ ፈቃደኛ ናቸው።
ይህ አስተያየት የተሰበሰበው ፋይዘርና ሞደርና የተባሉት ክትባት አምራቾች የሙከራ ውጤታቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ነው።
አሜሪካ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ክትባት ለገበያ እንዲውል አልፈቀደችም።
ነገር ግን በሚቀጥሉት ሳምንታት ሞደርና እንዲሁም ፋይዘር የተባሉትን ክትባቶች መርምራ ውሳኔ ታሳልፋለች ተብሎ ይጠበቃል።
"ቃል እገባላችኃለሁ፤ ክትባቱ ለእንደኔ ዓይነት ሰዎች ሲሰራ እከተባለሁ" ብለዋል ባራክ ከአንድ ራድዮ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
"በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቤ ነው ደግሞ የምከተበው። ሰዎች ሳይንስ እንደማምን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ። ከተከተብኩ ደግሞ ኮቪድ-19 አይዘኝም ብዬ አምናለሁ።"
የቡሽና ክሊንተን ተወካዮች ሲኤንኤን ለተሰኘው ጣቢያ እንደተናገሩት ሁለቱ ፕሬዝደንቶች ክትባቱ ለሕዝብ ይፋ ሲሆን ለመከተብ ዝግጁ ናቸው።
ሕዝቡም እንዲከተብ አሳስበዋል ሲሉ ተናግረዋል የፕሬዝደንቶቹ ወኪሎች።
የሕብረተሰብ ጤና ሙያተኞች በርካታ ሰዎች ከተከተቡ ሕዝቡ ቫይረሱን ሊላመደው ይችላል ብለው ያምናሉ።
ይህ ደግሞ በሙያው 'ኸርድ ኢሚዩኒቲ' ይባላል። ወረርሽኙን ለመግታት ወሳኙ ምዕራፍ ተደርጎም ይቆጠራል።
የአሜሪካ መድኃኒት ቁጥጥር ሰዎች ቫይረሱ ጥቅም ላይ እንዲውል ካፀደቁ በኋላ ሰፊ ማስታወቂያ ይሰራል ተብሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም ፋይዘር የተሰኘውን ክትባት ለመጠቀም ወስናለች።
የቦሪስ ጆንሰን ፕሬስ ዋና ፀሐፊ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቲቪ እየታዩ ይወጉ ይሆናል የሚል ፍንጭ ሰጥተዋል።












