ኮሮናቫይረስ ፡ 'ለ25 ዓመታት የተሰራበትን የሴቶች እኩልነት ኮቪድ-19 እየናደው ነው'' ተመድ

አንዲት ሴት ምግብ እያበሰለች የሚያሳይ ስዕል

ላለፉት 25 ዓመታት በጾታ እኩልነት ዙሪያ ሲሰራ የነበረውን ሥራ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋው እንደሚችል አንድ በቅርቡ የተሰራ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት አመለከተ።

በወረርሽኙ ምክንያት ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሰሩና ቤተሰብ ያላቸው ደግሞ ልጆቻቸውን እነሱ ብቻ እንዲንከባከቡ ተገድደዋል ይላል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ተቋም ያወጣው መረጃ።

"ላለፉት 25 ዓመታት ስንሰራበት የቆየነው የጾታ እኩልነት በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ክፍኛ ሊደናቀፍ ይችላል" ብለዋል የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ቀቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አኒታ ብሃሺያ።

እኩል የሥራ እድል እና የትምህርት አጋጣሚዎች ሊጠፉ ይችላሉ፤ በዚህም ምክንያት ሴቶች ከባድ የሆነ ሥነ አእምሯዊ እና አካላዊ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ተብሏል።

ሴቶች በቤት ውስጥ ሲውሉ በአብዛኛው ልጆችን የመንከባከብና ቤትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚጣልባቸው ሲሆን ከኮሮናቫይረስ በኋላ ደግሞ ሥራቸውንም ሊያጡ የሚችሉ ብዙዎች ናቸው።

ልክ ኮሮናቫይረስ በመላው ዓለም መሰራጨት ሲጀምርና ተቋማት ሠራተኞቻቸው ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን አንዲያከናውኑ ማድረግ ሲጀምሩ፤ ብዙዎች ምናልባት የቤት ውስጥ ሥራዎች እኩል በሆነ ሁኔታ ሊከወኑ ነው የሚል ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር። 'ባሌ ፀጉሬን ይዞ ከግድግዳ ጋር ያጋጨኛል . . . '

ነገር ግን በበርካታ አገራት በተሰሩ ጥናቶች መሰረት እውነታው የተገላቢጦሽ ነበር። በርካታ ሴቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ልጆቻቸውን የመንከባከብና ምግብ የማብሰል ኃላፊነት ተጭኖባቸዋል።

በአሜሪካ ቦስተን ተመራማሪዎች በሦስት ሺህ ሰዎች ላይ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት በቤት ውስጥ ከሚውሉ ሰዎች ውስጥ ሴቶቹ ከወንዶች በበለጠ ሁኔታ በሳምንት ተጨማሪ 15 ሰዓታትን በቤት ውስጥ ሥራና ልጆችን በመንከባከብ ያሳልፋሉ።

ምንም እንኳን በበርካታ አገራት በተለይም በአውሮፓ የእንቅስቃሴ ገደቦቹ እየላሉ ቢሆንም ኮረሮናቫይረስ ያስከተለው ጫና በቀላሉ የሚጠፋ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።

ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት እንኳን በዓለማችን በእያንዳንዱ ቀን ያለ ምንም ክፍያ በሥራ ከሚያልፉ 16 ሚሊዮን ሰዓታት መካከል ሦስት አራተኛውን ሥራ የሚሰሩት ሴቶች ናቸው።

በሌላ አገላጽ ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በእያንዳንዱ ያለክፍያ ወንዶች በሚሰሩት አንድ ሰዓት ሴቶች ደግሞ ሦስት ሰዓት ይሰራሉ ማለት ነው።

ምንም እንኳን የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በዓለም ዙሪያ የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተለው ተቋም (UN Women) ያካሄዳቸው 38 የዳሰሳ ጥናቶች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ላይ ያተኮረ ቢሆንም ባደጉት አገራትም ጭምር ያለው መረጃ ግን ተመሳሳይ ነገር ያሳያል።

Mop image

ስዊድናዊቷ አና ዣቪዬር የሁለት ልጆች እናት ስትሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የስምንት ወር ነፍሰጡር ነች። ምንም እንኳን ባለፉት ወራት ከቤተሰቦቿ ቤት በመውጣት የራሷን ቤት በማፈላለግ ላይ የነበረች ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነገሮችን እንዳመሰቃቀለባት ትናገራለች።

ከወረርሽኙ በፊትም ለብዙ ዓመታት የሰራችበትን የውበት መጠበቂያዎች አምራች ኩባንያ በመልቀቅ ስቶክሆልም ውስጥ የራሷን የህጻናት መገልገያዎች ማምረቻ ድርጅት ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነበረች።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ እሷና ባለቤቷ ከቤት መስራት የጀመሩ ሲሆን፤ በቤት ውስጥ ያለው የሥራ ክፍፍል ግን የሥራ ሰዓቷን ጭምር እንደሚሻማባት ትናገራለች።

ምንም እንኳን በቤት ውስጥ ለሚያስፈልጉ ነገሮች በየወሩ እኩል የሆነ ገንዘብ አዋጥተው የሚኖ ቢሆንም፤ እሷ ከባለቤቷ በበለጠ መልኩ ልጆችን የመንከባከብ፣ ምግብ ማብሰልና ቤት የማጽዳት ኃላፊነት አለባት።

"በውይይታችን ወቅት ባለቤቴ የህክምና መሳሪያዎችን ለሚያመርት ድርጅት ስለሚሰራና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደገው ጥረት መንግሥትን ስለሚረዳ ሙሉ ጊዜውን መሰዋት እንዳለበት ተስማማን።"

ነገር ግን ሥራውን ከጨረሰ በኋላ ያሉበትን ቀላል የሚባሉ ኃላፊነቶች እንኳን አሁንም ቢሆን ለመወጣት ፍላጎት አልነበረውም ትላለች አና።

ነፍሰጡርነት፣ የወረርሽኝ ስጋትና የቤት ውስጥ ሥራ ተደማምረው ሕይወትን ከባድ እንዳደረጉባት የምትናገረው አና፤ ልጇን ከመውለዷ በፊት ለመጨረስ አስባቸው የነበሩ በርካታ ነገሮች እስካሁን እንዳልተጀመሩ ትገልጻለች።

"ነገሮችን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርጋቸው ደግሞ ሴቶቹ ከወረርሽኙ በኋላ እንኳን ተመልሰው ሥራ መጀመር መቻላቸው አለመረጋገጡ ነው" ይላሉ አኒታ ብሃሺያ።

አክለውም "በመስከረም ወር ብቻ አሜሪካ ውስጥ እስከ 850 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች ከሥራቸው የተቀነሱ ሲሆን በተመሳሳይ ከሥራቸው የተቀነሱ ወንዶች ቁጥር ግን 200 ሺህ ብቻ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ጃፓን ውስጥ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ሴቶች ተጨማሪ አምስት ሰዓታትን ያለክፍያ ሥራ እየሰሩ እንደሚያሳልፉ አንድ ጥናት ያመለክታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት አብዛኛውን ሰዓታቸውን በሥራቸው ምክንያት ውጪ ያሳልፉ የነበሩ አባቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በአግባቡ መስራት የጀመሩበትና ልጆቻቸውን መንከባከብ እያዘወተሩ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን አሁንም ቢሆንም ሴቶች ከቤት ውስጥ ሥራ የአንበሳውን ድርሻ ቢወስዱም ከነጭራሹ ምንም ነገር ሰርተው የማያውቁ አባቶች ወደ ኩሽናዎች ሲገቡ መታየታቸው እንደ ትልቅ የለውጥ ጉዞ መቆጠር አለበት የሚሉም አልጠፉም።

አንድ ካናዳ ውስጥ በተሰራ ጥናት መሰረት ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑ አባቶች ከዚህ በፊት ከሚያደርጉት በተሻለ ምግብ እያበሰሉና ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ልብስ ማጠብና ቤት ማጽዳት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም መሪዎችና ትልልቅ ኩባንያዎች በርካቶች ያለክፍያ ሥራ እንደሚሰሩ እንዲረዱና በተለይ ደግሞ ሴቶች በዚህ ተጎጂ መሆናቸውን አውቀው ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።