ኮሮናቫይረስ፡ቤታቸው እስር ቤት የሆነባቸው ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች

ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች እርዳታን የሚሰጡ ስልኮች ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, PATRICK BAZ

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያስረዳው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ መወሰኑን ተከትሎ የቤት ውስጥ ጥቃት ጨምሯል።

የበርካታ የአፍሪካ አገራት መንግሥታት፣ፖሊስና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደገለጹት ከቤት ያለመውጣት ሕግን ተከትሎ በርካቶች በፍቅር አጋራቸው አልያም በቤተሰብ አባላቸው ጥቃት ይደርስባቸዋል።

ጥቃት ከሚደርስባቸው ሰዎች መካከል ደግሞ አብዛኛዎቹ ሴቶችና ህጻናት ናቸው።

በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እራሳችሁን ብታገኙት ምን ታደርጋላችሁ? የዘርፉ ባለሙያዎችንና የቤት ውስጥ ጥቃትን ማምለጥ የቻሉ አነጋግረን ተከታዩን አዘጋጅተናል።

‘’ ጥቃት የሚፈጸመምበት አይነት ግንኙነት ውስጥ ካላችሁ ምን እየሆነ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል’’ ትላለች ለብዙ ዓመታት በባለቤቷ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት የደረሰባት ኤስተር።

‘’ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሁሌም አስቸጋሪ ነበሩ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ወደየቤቱ ይሰበሰባል። በቤት ውስጥ ሲውል ምንም የሚሰራው ነገር ስለሌለው ይደብረዋል። ሰብብ እየፈለገ እኔን ለማበሳጨትና የሆነ ነገር እንድናገር ወይም እንዳደርግ ይገፋፋኛል።‘’

"አዎ ሁሌም መጨረሻው የቃላት ውርጅብኝና አንዳንዴም ዱላ ነበር። ልክ የታሰርኩ ያክል ነበር የሚሰማኝ።‘’

በሁለት ቀን ውስጥ የሰው ልጅ ያክል ይህንን ያህል ከደበረው ለወራት ቤት ውስጥ ሲቀመጥ ደግሞ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም ትላለች ኤስተር።

ጭንቀት ጥቃት አድራሾችን የበለጠ ጠብ ጫሪ ያደርጋቸዋል፤ ለሴቶቹ ደግሞ ማንም እንደማይደርስላቸው ሲያውቁ ደግሞ የበለጠ ጨካኝነት ያጠቃቸዋል።

‘’በኢኮኖሚ በኩል ጥገኛ ስለነበርኩኝና ልጆች ስላሉኝ እንዴት ዝም ብዬ እሄዳለው የሚለው ሀሳብ ሁሌም ወደኋላ ይጎትተኝ ነበር።‘’

የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት በዚህ ወቅት ደግሞ ሴቶች አጋሮቻቸውን ጥለው እንዳይሄዱ እንኳን ሕግ ጣሳችሁ ተብለው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይውላሉ።

እሱን ቢያመልጡ እንኳን ወደፈለጉበት የሚሄዱበት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የለም።

በርካታ አገራት ይህንን ውስጥ በማስገባት በቤት ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው አገልግሎት የሚሰጥ ነጻ የስልክ መስመር አዘጋጅተዋል። መስመሩ ሁሌም ቢሆን እንደሚጨናነቅ ነው የሚነገረው።

በደቡብ አፍሪካ በመጀመሪያዎቹ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለባቸው ሳምንታት ብቻ ፖሊስ 2320 ጾታዊ ጥቃቶች እንደመዘገበ ገልጿል። ይህ ደግሞ ከሌላ ጊዜው 37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በዚምባብዌ ደግሞ የጥቃቶች ቁጥር በሶስት እጥፍ የጨመረ ሲሆን በናይጄሪያም ቢሆን ከሌላጊዜው ከፍ ያለ ጥቃት ተመዝግቧል።

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሴቶችን በዚህ ወቅት ለመርዳት በማሰብ የተለያዩ አማራጮችን እየወሰዱ ነው። ለምሳሌ ቱኒዚያ በዚህ ጊዜ ጥቃት የሚደርባቸው ሴቶችና ህጻናት ማረፊያ የሚሆኑ ስምንት መጠለያዎችን አዘጋጅታለች

በሌሎች አገራት ደግሞ ተመሳሳይ መጠለያዎች ተዘጋጅተው በጎፈቃደኞችም ጭምር እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዚምባብዌ የሚገኘው መጠለያ በአሁኑ ሰአት 21 አዋቂ ሴቶችና ሰባት ህጻናትን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል። የማዕከሉ ዳይሬክተር ቢየትሪስ ሳቫድዬ እንደሚሉት ሴቶቹና ህጻናቱ አንዳንዶቹ ከቤታቸው ጠፍተው የመጡና በፖሊስ ጥቆማም የተገኙ ናቸው።

በኬንያ የምትገኛዋ የማህበበራዊ አገልግሎት ሰራተኛ ዳያና ካማንዴ እንደምትለው ደግሞ እሷ የምትሰራበት ድርጅት 17 ሴቶችን ተቀብሎ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በናይጄሪያ ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ሴቶች ከቤታቸው ለማስወጣት በጎ ፈቃደኞችም ጭምር በመሳተፍ ትብብር እያደረጉ ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሴቶቹን ከአጋሮቻቸው ለማስመለጥ ቤተ ዘመድም ጭምር ይሳተፋል ተብል።

በጋና ያለው መጠለያ ደግሞ ከዚህ በኋላ ጥቃት የሚደርስባቸውን ሴቶች ለመቀበል እየተቸገርኩ ነው ብሏል። ምክንያቱም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና የለይቶ ማቆያዎች በመሙላታቸው ነው።

ኤስተር በዚህ ማዕከል ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሰዎች በተቋቋመው የጥር መስመር ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች።

‘’ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ለማግኘት ጥረት አድርጉ፤ደውሉላቸውና ያላችሁበትን ሁኔታ አስረዷቸው። ሊረዳችሁ የሚችል ማንኛው ሰው ጋር ከመደወል ወደኋላ አትበሉ’’ በማለት ምክሯን ለግሳለች።

ኮሮና