ኮሮናቫይረስ፡ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሴቶች ከለላ የሚሰጠው ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Rtbf
ብራሰልስ የሚገኝ የአውሮፓ ምክር ቤት ህንጻ ለ100 ሴቶች መጠለያ ሆኗል። ከሴቶቹ አብዛኞቹ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ናቸው። ቤልጄም ዜጎቿ ከቤት እንዳይጡ ማወጇን ተከትሎ የቤት ውስጥ ጥቃት ተበራክቷል።
በመጠለያው ቤት አልባ ሴቶችም ይገኙበታል።
ሄልሙት ኮሁል የተባለው ህንጻ ለሴቶች ማቆያ የሆነው ባለፈው እሮብ ነበር። በህንጻው ያሉ ቢሮዎች ወደ መኝታ ክፍልነት ተለውጠዋል። ምግብና የህክምና አገልግሎትም ይሰጣል።
ሳሙሶሻል የተባለ የተራድኦ ድርጅት እንደሚለው፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ መወሰኑን ተከትሎ የቤት ውስጥ ጥቃት ጨምሯል። በቤልጄም መዲና ብራሰልስ የሚገኘው ምክር ቤት ከሳሙሶሻል ጋር ተጣምሮ ነው ለሴቶች ከለላ የሚሰጠው።
የተራድኦ ድርጅቱ ኃላፊ ሰባስሽን ሮይ፤ “የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለ ወዲህ በቤት ውስጥ ጥቃት ሳቢያ ብዙ ሴቶች ጎዳና ወጥተው አግኝተናል” ብለዋል። የብራሰልስ ባለሥልጣኖች የጎዳና ተዳዳሪዎች በሆቴሎች እንዲጠለሉ አድርገዋል።
በአሁን ወቅት አብዛኞቹን የአውሮፓ ምክር ቤቶች የሚጠቀምባቸው የለም። በምክር ቤቶቹ ጥቂት የሕዝብ እንደራሴዎች ለስብሰባ ሲገኙ፤ አብዛኞቹ ግን ስብሰባውን የሚከታተሉት በቪድዮ ነው። የምክር ቤቱ ፕሬዘዳንት ዴቪድ ሳሎሶ፤ ብራሰልስ ከመቼውም በላይ ችግር ውስጥ መውደቋን ገልጸው፤ “ችግሩ ሁላችንንም ይነካል” ብለዋል።
“አሁን ያለንበት ውጥንቅጥ ሁላችንም በጎ ነገር እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል” ሲሉም አክለዋል። ምክር ቤቱ ቤት አልባ ሰዎችን ለሚረዱ ድርጅቶች በየቀኑ 1,000 ምግብ ያከፋፍላል።
የሳሙሻል ኃላፊ ሮይ እንደሚሉት፤ የእንቅስቀሴ ገደቡ ከተነሳ በኋላ ቤት አልባ የሆኑት ሴቶች እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አጠያያቂ ነው። ኮሮናቫይረስ ያስከተለው ቀውስ፤ ለአደጋ እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰቡ አካላት ከለላ የሚሰጥበት መሆኑንም አክለዋል።
በመጠለያው ካሉ ሴቶች አንዷ አድሊን፤ “በእንደዚህ አይነት ወቅት ቤት አልባ ሰዎችን የሚያስታውስ የለም” ትላለች። ማቆያው እፎይታ እንደሰጣትም ትናገራለች። የእንቅስቃሴ ገደብ ሲጣል እሷና ባለቤቷ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ተገደው ነበር።
“ወደ 15 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘናል። አንድ ቦታ ስናርፍ ፖሊሶች ተነሱ ይሉን ነበር። በስተመጨረሻ አቅማችን ተሟጠጠ” ትላለች። በሌሎች ማቆያዎች በአንድ ክፍል እስከ ስድስት ሴቶች እንደሚኖሩ በመጥቀስ፤ ምክር ቤቱ ውስጥ በአንድ ክፍል ሁለት ሴቶች ብቻ እንዲቆዩ መደረጉ ምቹ መሆኑንም ታስረዳለች።
እሷ መጠለያ ብታገኝም ባለቤቷ እንደአብዛኞቹ ቤት አልባ ወንዶች አሁንም ጎዳና ላይ በመገኘቱ ግን ታዝናለች።














