ኮሮናቫይረስ፡ በኒው ደልሂ አጣብቂኝ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ታካሚዎች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, PRAKASH SINGH
የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ተከትሎ ህንድ ባሳለፈችው የእንቅስቃሴ ገደብ ለሳምንታት በኒው ደልሂ ለመቆየት ተገደው የነበሩ 100 የሚሆኑ ኢትዮጵውያን ታካሚዎች ከሰሞኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ለህክምና ወደ ህንድ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው መመለስ ሲኖርባቸው ባልጠበቁት ሁኔታ እንዲቆዩ መደረጋቸው ለኢኮኖሚያዊና ለተለያዩ ችግሮች መጋፈጣቸውን በባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ይህንንመ ተከትሎ በኒው ደልሂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመተባበር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ 14/2012 ዓ.ም ወደ አገራቸው እንደመለሷቸው ታካሚዎቹ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ታፍነን ነበርን"
ከኒው ደልሂ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ እድል ካገኙት መካከል አንዱ አቶ ሃብቶም በህክምና ምክንያት ከወንድሙ ጋር ለሁለት ወራት በህንድ ቆይቷል።
"በአንደኛው ወር ህክምናዬን ብጨርስም የህንድ መንግሥት እንቅስቃሴ እንዳይኖር መመሪያ በማውጣቱ ለተጨማሪ አንድ ወር በከባድ ችግር ነው ያሳለፍነው። ቅዳሜ እለት ግን የኤምባሲ እና የአየር መንገዱ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመልሱን ነገሩን። ብዙ መከራ ብናሳልፍም አሁን ግን ደስተኞች ነን" ይላል።
የ68 ዓመት አዛውንቱ አቶ ገብረመስቀል ገብሩም ለኩላሊት ንቅለ-ተከላ ሦስት ሁነው ነበር ወደ ኒውደልሂ የሄዱት።
ከባለቤታቸው እና ኩላሊት ከሚለግስላቸው ሰው ጋር የሄዱት እኚህ የእድሜ ባለፀጋ በህንዷ መዲና ለሦስት ወራት እንዲቆዩ ተገደው ነበር።
"እዚህ ታፍነን ነበር፤ ከማንም ጋር መነጋገር አይቻልም። በችግር ውስጥ ነው የነበርነው" በማለት አሁን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ በመደረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌላ ስጋት…..
በህንድ ሁለቴ በታወጀው ረዥም የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ላልተፈለገ ወጪ ተጋልጠው የቆዩት እነዚህ ታካሚዎች አሁን ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም በመዲናዋ ለሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ ያሳልፋሉ።
"የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆቴሎች ዝርዝር ልኮልናል፤ ዝቅተኛው ዋጋ በቀን 30 ዶላር ነው። በህንድ የኢኮኖሚ ችግር ስለደረሰብን ይህ ለመክፈል አቅማችን አይፈቅድም። በውድ ሆቴሎች ገብተን ምንድን ነው የምንሆነው?" ሲል አቶ ሃብቶም ይናገራል።
በአዲስ አበባ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ሆቴሎች የነበሩና ጉዟቸውን ወደ ትግራይ የሚቀጥሉ ተጓዦችም የክልሉ መንግሥት በጣለው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ምክንያት ለሁለተኛ ግዜ በክልሉ ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል አሊያም ሆቴሎች መግባታቸው ግድ ነው።
አቶ ገብረመስቀል በውድ ሆቴሎች ለዚያውም ሁለት ግዜ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባት የሚለውን ውሳኔ አይቀበሉትም።
"ከሆስፒታል እንደወጣሁኝ ኩላሊት ለለገሰልኝ ሰው እና ለእኛ ሁለት ማረፍያ ነበር የያዝኩት። በጣም ውድ ነው፤ በዚያ ላይ ለሦስት ወር መቆየት በጣም ከባድ ነው። የገንዘብ ቀውስ ደርሶብናል" ይላሉ አቶ ገብረመስቀል።
"በአዲስአበባ ለ14 ቀናት፤ በመቀለም ለ14 ቀናት ባጠቃላይ ለአንድ ወር በለይቶ ማቆያ መቆየት ጥሩ አይደለም። ወደ መቀለ የሚሄደውን እዚያ ተለይቶ መቆየት አለበት። በአዲስ አበባ አንዴ ተለይተን ከቆየን ይበቃል። ሰው በተጓዘበት ሁሉ መታሰር ግን ትክክል አይደለም" ብለው ያምናሉ።
የሌሎቹ እጣፈንታስ?
አሁን በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደው እርምጃ በኒውደልሂ የነበሩ ታካሚዎች ብቻ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ አሁንም በተለያዩ የህንድ ግዛቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ታካሚዎች አሉ።
በሀገሪቱ በወረርሽኙ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በመከልከሉ ከኒውደልሂ ውጪ ያሉ ታካሚዎች ወደ መዲናዋ መምጣት አልቻሉም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከኒውደልሂ ውጪ ወደ ሌሎች አካባቢዎች አለመብረሩ ደግሞ ይህንን እድል ለማግኘት እንዳልቻሉ ነው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን የሚገልፁት።
አሁን ወደ አገር ቤት የተመለሱት 100 እንደማይሞሉ እና ቁጥሩ በተለያዩ የህንድ ግዛቶች የሚገኙትን ታካሚዎች ከዚህ በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ከአዲስ አበባ እናቱን ለማሳከም ወደ ኖይዳ ከተማ የሄደው አቶ ዳናይ ግደይም በህንድ ካሰቡት በላይ እንዲቆዩ እና ለገንዘብ ችግር ከተጋለጡት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው።
"እናቴ ዕጢ ስለነበራት እሱን ለማስወገድ በመጋቢት 13 ነው ወደ ጄፒ ሆስፒል የሄድኩት። አስፈላጊውን ቀዶ ህክምና ብንጨርስም ለማደሪያ በቀን 1800 ሩፒ በመክፈል ነው እየኖርን ያለነው። ይህንን የምግብና የመድኃኒት ክፍያን አይጨምርም" ይላል ዳናይ።
በእጁ የነበረውን ብር እየጨረሰ መሆኑ እና ከቤተሰብ በዌስተርን ዩኒየን እንዳያስልክም የአገሪቱ ባንኮች ዝግ በመሆናቸው መንቀሳቀስ እንዳልቻለ ገልፆልናል።
በህንድ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ መጨመር ለእናቱ ጤና ስጋት እንደሆነበት የሚናገረው አቶ ዳናይ ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ቢደውልም ኤምባሲው በአገሪቱ በተጣለው አዋጅ ዝግ መሆኑ እንደተነገረው ይገልፃል።
"የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአየር መንገዱ ጋር በመተባበር ኒውደልሂ የሚገኙትን እየወሰደ እንደሆነ ገና ዛሬ ነው የሰማነው። የምናውቀው ነገር አልበረም። እንደሰማን እኛም ወደ ሀገራችን መመለስ እንፈልጋለን እባካችሁ ድረሱልን ብለናቸዋል" ቢሆንም የቪዛ ቁጥራቸውን ከመመዝገብ ባሻገር መፍትሄ እንዳላገኙ ነው የሚናገረው።
"አገራት ዜጎቻቸውን በቻርተር አውሮፕላን እያስወጡ ነው"
ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ ለማግኘት ኒውደልሂ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተደጋጋሚ ቢደውልም ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት አልቻለም።
በሰሜናዊ ህንድ የሚኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ክሩቤል ሽታሁን ግን ይህን ጉዳይ እንደሚያውቁት፤ አየር መንገዱ መንገደኞች ለማጓጓዝ ፈቃድ እንዳልተሰጠው እና በረራዎች መንግሥታት እንደሚያስተባብሩት ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
"ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከህንድ መንግሥት መንገደኞች ለማጓጓዝ ፈቃድ ስላልተሰጠን ምንም ማድረግ አልቻልንም። አንዳንድ አገራት ዜጎቻቸውን በቻርተር አውሮፕላን እያስወጡ እንደሆነ እናውቃለን" ማለታቸው ይታወሳል።
በዚህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መልስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።













