በላቲን አሜሪካ የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በላቲን አሜሪካ አገሮች የኮቪድ-19 ክትባትን ለመጀመርያ ጊዜ በዘመቻ መስጠት ተጀምሯል። በተለይ ሜክሲኮ በዚህ ረገድ ቀዳሚ ሆናለች።
ሜክሲኳዊቷ ነርስ የፋይዘር ባዮንቴክ ክትባትን ለመወጋት የመጀመርያዋ የላቲን አሜሪካ ዜጋ ሆናለች።
ይህ ዘመቻ የተጀመረው ትናንት ሐሙስ ሲሆን ሜክሲኮ 3ሺህ ብልቃጥ ክትባት ወደ አገሯ እንደገባ ነው ዘመቻውን የጀመረችው።
ሜክሲኮ ተህዋሲው በርካታ ዜጎችን ከገደለባቸው የዓለም አገራት ተርታ ትመደባለች።
በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተህዋሲው ያለቀባቸው አገራት በቅደም ተከተል አሜሪካ፣ ብራዚል ሕንድና ሜክሲኮ ናቸው።
ሜክሲኮን ተከትሎ ቺሌ እና ኮስታሪካ የጀርመን/አሜሪካ ሰራሹን ፋይዘር ባዮንቴክ ክትባትን ለዜጎቻቸው መስጠት ጀምረዋል።
አርጀንቲናም በተመሳሳይ ከቀናት በኋላ ክትባት መስጠት ልትጀምር እንደሆነ ይፋ አድርጋለች።
ሆኖም አርጀንቲና የመረጠችው የክትባት ዓይነት ራሺያ ሰራሹን ሰፑንትኒክቪ ሲሆን 300ሺህ ብልቃጥ ቦነስ አይረስ መድረሱ ተሰምቷል።
ከደቡብ አሜሪካ አገሮች ከፍተኛ ሕዝብ በተህዋሲው የሞተባት ብራዚል ግን እስከ አዲሱ የፈረንጆች ዓመት የካቲትድረስ ክትባቱን መስጠት እንደማትጀምር ተዘግቧል።
አወዛጋቢው ፕሬዝዳንቷ ቦልሴናሮ ክትባቱን እንደማይወስዱ ተናግረዋል። ምክንያቱም እኔ በቫይረሱ ተይዤ ስለነበረ የመከላከል አቅም አዳብሪያለሁ ብለዋል።
ረቡዕ ሜክሲኮ የደረሱበት 3ሺህ ብልቃጥ ክትባቶች የተመረቱት ቤልጂየም ውስጥ ነው።
የመጀመርያዋ ተከታቢ ነርስ ክትባቱን ስትወስድ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሎፔዝ ኦፕራዶር በተገኙበት ለሕዝብ በቀጥታ ተላልፏል።
የሜክሲኮ መንግሥት በቀጣይ ሁሉንም የጤና ባለሙያዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ክትባቱን ለማዳረስ እንደሚሞክር ቃል ገብቷል።
ሜክሲኮ 1 ሚሊዮን 300ሺህ ዜጎቿ በተህዋሲው ተይዘው 120ሺህ የሚሆኑት ሞተውባታል።
ቺሊ 600ሺህ ሰዎች ተይዘውባት 16ሺ የሚሆኑት ሞተውባታል። አርጀንቲና 1 ሚሊዮን 600ሺ ሰዎች ተይዘው 42ሺ የሚሆኑት ሞተዋል።
የቺሌው ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ፓኔራ የክትባቱ መጀመር የአዲስ ተስፋ ዘመን መምጣትን ያመላክታል ሲሉ ለሕዝባቸው ንግግር አድርገዋል።












