ምርጫ 2013፡ "በራሱ መሬት ላይ እንግዳ የሆነ ሕዝብ ቢኖር የአፋር ሕዝብ ነው"

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አቶ ሙሳ አደም

የፎቶው ባለመብት, Musa Adem

በአሸባሪነት ተፈርጇል። እንደ ግንቦት 7 እና ኦብነግ ነፍጥ አንስቶ በኤርትራ በረሃ ኳትኗል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ በኋላ ወደ አገር ቤት ገብቷል።

አሁን በአፋር ከፍተኛ ተሰሚነት ካላቸው ፓርቲዎች አንዱ ነው። "የአፋር ሕዝብ ፓርቲ" ወይም በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ ኤፒፒ (APP) ተብሎ ይጠራል።

ከፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም ጋር በቁልፍ የአፋር ሕዝብ ጉዳዮች ዙርያ ዘለግ ያለ ቆይታ አድርገናል።

ፓርቲ ስለበዛ እስኪ የእርስዎን ፓርቲ በአጭሩ ያስተዋውቁን?

በፈረንጆች 2010 ላይ ነው የተመሠረትነው። ከዚያ በኋላ ግን ሕጋዊነት አልነበረውም። እዚህ የነበረው ነገር ፈረሰና ከዚያ ፓርቲው በአሸባሪነት ተፈረጀ። አባላቱ ተበተኑ። ህቡዕ ገባን። ተሰደድን።

ምን ያህል ወታደሮች ነበሯችሁ?

ወደ 3ሺህ ታጣቂ ወታደሮች ነበሩን። ኤርትራ ነው የነበሩት።

ወታደሮቻችሁ አሁን የት ነው ያሉት?

ከለውጡ በኋላ በምዕራፍ፣ በምዕራፍ አስገብተናቸዋል። አጠቃላይ ወታደሮቻችን መልሰው ተቋቁመዋል። የወታደራዊ ክንፋችን ዜሮ ፐርሰንት ነው፤ በዚህ ሰዓት።

ምን ያህል አባላት አሏችሁ?

በቋሚነት ወርሃዊ ክፍያ የሚከፍሉ አባላት 250ሺህ ሰዎች ይሆናሉ።

ለምንድነው "የአፋር ግንቦት 7" የሚሏችሁ?

ዛሬም አንድ ጋዜጠኛ ይህንኑ ሲጠይቀኝ ነበር። 'ከግንቦት 7 ጋር ግንኘነት አላችሁ ይባላል' አለኝ።

'ግንቦት 7 አለ እንዴ?' አልኩት።

ምናልባት መንፈሱን ኢዜማ ወርሶት ከሆነ ብለን በዚያ እንያዘውና ጥያቄውን እንቀጥል። ለምን ይህ ቅጽል መጣ? የግንቦት 7 ተላላኪዎችም' የሚሏችሁ አሉ።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሲፈጠርም አግላይ አስተሳሰብ የለውም። ጽንፈኛም አይደለም። አማካይ (Moderate) የፖለቲካ አካሄድን ነው የሚመርጠው።

ግንቦት 7 በትግል ወቅት አብረን የተባረርን የትግል አጋር ፓርቲ ነበር። ኤርትራም ሳለን ሰፊ ግንኙነት ነበረን፣ ውጭ እያለንም 'ኢትዮጵያን ናሽናል ሞቭመንት' የሚባል እንቅስቃሴ ነበረን። እዚያ ውስጥ እነ ሌንጮ ባቲ የነበሩበት ድርጅት፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄና እኛም፣ ግንቦት 7ም ነበረ።

አሁን ግንቦት 7ም ፈርሶ እኛም እንደ አዲስ ተደራጅተን ነው ያለነው።

አሁን ኢዜማ አለ። ኢዜማና ፓርቲያችን ጥሩ ግንኙነት ነው ያለን። ይሄ ምንም የሚሸፋፈን ነገር የለውም።

በፖለቲካ አስተሳሰብ ደረጃ ግን አንድ ነን ማለት አይደለም።

መሠረታዊው ልዩነታችሁ ምንድነው?

ለምሳሌ በመንግሥት አወቃቀር ላይ እኛ አሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር መቀጠል አለበት፣ ችግር የለበትም ነው የምንለው።

ቋንቋ ላይ መሠረት ያደረግ ዘውጌ የፌዴራል አወቃቀር ትክክለኛ ነው ብላችሁ ነው የምታምኑት?

አዎ! ፌዴራል አወቃቀር ችግር አለበት ብለን አናምንም። የፌዴራሊዝሙ አፈጻጸም፣ የተተገበረበት መንገድና 'ማኒፑሌት' የተደረገበት መንገድ (የተጠመዘዘበት ሁኔታ) ግን መርዘኛ ነው ብለን እናምናለን።

መርዘኛ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦች ማንነታቸውን ይዘው አብረው እንዳይኖሩ የሚያደርግ መጥፎ አተገባበር ነበረ ብለን ነው የምናስበው።

ኢዜማ ደግሞ መልከአምድራዊ (Geographic) ፌዴራሊዝም ነው መኖር ያለበት ይላል። ከእኛ ጋር በጣም ይራራቃል።

የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ ዓርማ

የፎቶው ባለመብት, APP

የአፋር ሕዝብ መንፈሳዊ አባት ከነበሩት ሡልጣን ሐንፍሬይ አሊሚራህ ጋር የናንተ ፓርቲ የተለየ ግንኙነት ነበረው ልበል? ስትገቡም አብራችሁ ነው የገባችሁት።

ሡልጣን አሊሚራህ በጣም ቅርብ ወዳጃችንም መካሪችንም ነበሩ። በወንድማቸው የሚመራ የአፋር ነጻ አውጪ ፓርቲ አለ። እኩል ነበር የሚያዩን። በተለይ ከእኛ ፓርቲ መሪ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ጋር ልባዊ ግንኙነት ነበራቸው። የተሰደዱ ጊዜ ከፍተኛ አቀባበል አድርገንላቸዋል።

በብዙ ነገር ይደግፉን ነበር። ከሚጠበቅባቸው አባታዊ ድጋፍም በላይ መካሪያችን ነበሩ።

ይሄን ጥያቄ ያለምክንያት አላነሳሁም፣ አቶ ሙሳ። ሡልጣኑ ከናንነተ ጋር መወገን የጨዋታውን ሕግ ስለሚቀይር ነው። እርሳቸው በአፋር ክልል "አያቶላህ" ማለት ናቸው። በፖለቲካ ባረኳችሁ (Endorse ) ማለት ትልቅ የፖለቲካ ድል ነው። የድጋፍ መሠረታችሁንም ያደላድላል።

ልክ ነህ። ይሄ እንግዲህ እንደ ሰው ዕይታ ነው የሚወሰነው። እኛ በፕሮግራም ደረጃ ለአገር ሽማግሌዎች፣ ለነባር ታጋዮች እና ለመንፈሳዊ አባቶች ፕሮግራም ቀርጸን ነው የምንቀሳቀሰው። ለአገር ሽማግሌዎች የተለየ ስፍራ አለን። ራሱን የቻለ ፓርላማ (ቼምበር) አዘጋጅተናል...።

እሱን ወደኋላ እንመለስበታለን። ሌላ ጥያቄ ላንሳ። ፓርቲያችሁ ስለሴቶች ግድ ይለዋል? ለምሳሌ ስንት አባላት በአመራር ደረጃ አሏችሁ?

እኛ የሴቶችን ተሳትፎ በዋዛ አንመለከተውም። ሴቶች ያለገደብ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ነው የምንታገለው።

የአፋር ሴት እንደሌሎች አካባቢዎች ሁኔታዎች የተመቻቹላት ሴት አይደለችም። የአፋር ሴቶችን ወደ ፖለቲካ ሜዳ ማምጣት በራሱ ቀላል ሥራ አይምሰልህ።

ያም ሆኖ በጣም ብዙ ሴት አባልና ደጋፊዎች አሉን። ወጣት ሴቶች በስፋት ገብተው ፖለቲካ እንዲሠሩ እናደርጋለን።

በአሐዝ አስደግፈው ይገሩኝ፤ ስንት አባላት በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ አሉ?

ከአሥራ አንድ ሥራ አስፈጻሚ መሀል አራቱ ሴቶች ናቸው። ቁልፍ ኃላፊነቶችን የያዙም ናቸው።

በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ 45 አባላት አሉ። 15ቱ ሴቶች ናቸው። ትንሽ ቁጥር ነው፤ እናውቃለን። ግን በስፋት እየሠራንበት ነው።

በነገርህ ላይ፣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከብዙዎቹ እኛ በሴቶች አሳታፊነት የላቅን ነን። ምርጫ ቦርድ በዚህ ረገድ ያወጣው ጥናት አለ።

እኛ ጋ በአባላት ደረጃ 34 ከመቶ ሴቶች ናቸው። ይሄ ትንሽ ቁጥር ቢመስልም በአገር ደረጃ ትልቁ 38 ከመቶ ነው።

እውነት ለመናገር እኛ ሴቶችን ወደፊት ለማምጣት ቁርጠኛ ነን፤ ግን ሥራው ቀላል አይደለም።

የአፋር ሴት ሌሊት ወጥታ ማታ ነው የምትገባው። እንጨት ለቅማ፥ እረኝነቱ፤ ውሃ መቅዳት በሴቷ ጫንቃ ላይ ነው ያለው። የአፋር ሴት ፖለቲካን ለመሥራት ምን የተመቻቸላት ነገር አለ?

ይቺ አሐዝ ላይ የደረስነውም በከፍተኛ ትኩረት ስለሠራንበት ነው።

አቶ ሙሳ አደም

የፎቶው ባለመብት, APP

ከተመረጣችሁ የአፋር ፓርላማን ባለ ሁለት ቼምበር ለማድረግ አስባችኋል። የባሕላዊ ሽማግሌዎች የሚወከሉበት ሸንጎ ይኖረዋል። ይሄ ለምን አስፈለገ? ከጀርባው ያለው ፖለቲካዊ አመክንዮ ምንድነው?

ጥሩ! በክልልም በአገርም ደረጃ እያወዛገበን ያለ ነገር አለ። ወይ ዘመናዊ አልሆንም ወይም በራሳችን ባሕል ውስጥ ዘመናዊ ፖለቲካን አልፈጠርንም። በመሀል እየዋለለን ያለን ሕዝቦች ነን። ተጭበርብረናል።

አመክንዮው ወደራስ መመለስ ነው። እኛ በምክር ቤት ደረጃ ሁለቱ ምክር ቤቶች (ቼምበርስ) ይኖሩናል። ሦስተኛ ደግሞ አማካሪ ምክር ቤት ይባላል።

የመጀመርያው ምክር ቤት በሕዝብ በሚመረጡ እንደራሴዎች የሚሞላ ነው።

ሁለተኛው ከተለያዩ ባሕላዊ ተቋማት በተለይም ሃይማኖታዊና ባሕላዊ አባቶች፣ ነባር ታጋዮች የሚወከሉበት ነው።

የአፋር ሽማግሌዎች በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታግለው ይምጡ፣ ለሕዝባችን ለአገራችን ዋጋ ከፍለዋል፣ ወድቀው ተነስተዋል፤ ብዙ አይተዋል።

እነዚህ ሽማግሌዎች ወደድንም ጠላንም የካበተና የደረጀ ዕውቀት አላቸው። ለዚህ ተገቢውን ቦታ መስጠት አለብን።

መንግሥት "ፈንክሽን" ሲያደርግ ባሕላዊውንም ዘመናዊውምን አስተዳደር አጣምሮና አስታርቆ መሄድ አለበት ብለን እናምናለን።

ሁለቱ ቼምበር ያስፈለገው ለዚህ ነው። በመሀል የአማካሪ ምክር ቤት አለ።

አማካሪ ምክር ቤቱ ደግሞ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ የአፋር ተወላጆች የሆኑ ምሁራንን ያቀፈ ነው የሚሆነው። ይህ አማካሪ ምክር ቤት የባሕላዊ ሸንጎውንና የላይኛውን የክልል ምክር ቤት እንደ ድልድይ ያገናኛል።

የአፋር ሕዝብ በማይናወጽ ብሔራዊ ስሜቱ ይነሳል። መንፈሳዊ መሪው "እንኳን እኛ ግመሎቻችን ባንዲራውን ያውቋታል" ብለዋል ይባላል። በታሪክም ውስጥ በግዛት አንድነት ጉዳይ ላይ ከቱርክ፣ ከግብጽ፣ ከፖርቹጋል የመጡ ወራሪዎችን በመመከት ይነሳል። የአፋር ሕዝብ ለዚህ ተግባሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ተገቢው ቦታ ተሰጥቶታል ብለው ያምናሉ? ወይስ ተገድፏል?

የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ ሉዓላዊነትና አገራዊ አንድነት ላይ ሰፊ ገድል የፈጸመ ሕዝብ ነው። እንደ አገር ያልተዋጋናቸው፣ እንደ ሕዝብ ብቻ የመለስናቸው ትልልቅ ውጊያዎች አሉ።

አፋር ብትመጣ ዕውቅ የጦርነት አውድማዎች አሉ። የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይዘምት አፋሮች ብቻ የመከቷቸው ብዙ ጦርነቶች አሉ። አልተጻፉም እንጂ።

የተለያዩ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ በመጡበት ጊዜ ትላልቅ ውጊያ አፋሮች አድርገው ውጊያ በተጀመረበት መሬት እንዲያልቅ አድርገዋል።

በታሪክ ደረጃ አፋር ተወርቶለታል ወይ ላልከኝ የሚያውቀው ያውቀዋል። ነገር ግን ሌላው እንደሚንቆለጳጰሰው አልተንቆለጳጰሰም። ሕዝቡም ያን የሚፈልግ አይደለም። በአገሩ ጉዳይ ከማንም ምስጋና እንዲቸረው አይፈልግም።

በነገርህ ላይ ጣሊያንን የወጉ አርበኛ አባቶች ዛሬም አፋር አሉ። ሜዳሊያ ያጠለቀላቸው ግን የለም። ባንዲራ ያለበሳቸው የለም። ታሪካችሁን እንጻፍ ያላቸው ግን የለም። የፖለቲካ ታሪክ (Political History)ን የሚጽፉ ሰዎች አፋር ቢመጡ ቱባ ታሪክ ያገኛሉ።

አፋሮች ሌላውን "ይሄ ክልልህ አይደለም፣ ውጣ" ሲሉ አይሰማም። በሌላ አካባቢ ይህ ነገር ትልቅ ቀውስ ፈጥሯል። ምንድነው እናንተ ጋር ያለው ነገር?

የኛ የባሕላዊ ፍልስፍና መነሻ አንድነት ነው። አንድ ብለህ ነው ሁለት የምትለው። ሁለት ከአንድ በኋላ ነው የሚመጣው።

ይቺን አገር አንድ ሆና ስትቆይ ትከበራለች። ደግሞም ተከብረን ቆይተናል። በአንድነታችን ተከብረንበታል።

የተከፋፈሉ ሕዝቦች በቅኝ ግዢ ወድቀው ነው የሚገኙት። የተከፋፈሉ ሕዝቦች የባሪያ ቀንበርን ተሸክመው ዛሬም ድረስ ከዚያ ዳፋ አልተላቀቁም። ባሕላቸውም ማንነታቸውን እምነታቸውን አጥተዋል።

አንድነታችን ነው ከዚህ ያዳነን። ማንነታችን እንዳናጣ ያደረገን እሱ ነው።አፋር ይህን አሳምሮ ስለሚያውቅ ይመስለኛል።

የመገፋቱ፣ የመገለሉ ነገር እንዳለ ነግረውኛል። ያም ሆኖ ነው ስለ አገር አንድነት የጸና አቋም አለን የሚሉኝ?

ይሄ እኛን የመግፋቱ፣ የማግለሉ ነገር አስተዳደራዊ ጉዳይ ነው። ወደፊት ታግለህ የምታስቀይራቸው ነገሮች ናቸው። በአገርህ የሚያደራድሩህ ነገሮች አይደሉም።

በፌዴራል ደረጃ አፋር ያለውን ውክልና እንዴት ይገመግሙታል?

በፌዴራል ደረጃ ያለን ውክልና ዜሮ ሊባል የሚችል ነው። አንዲት ሚኒስትር ናት ያለችው። ከዚያ ባለፈ ሃያ የሚኒስቴር ኤጀንሲና ተቋማት ውስጥ በዳይሬክተርነት ደረጃ እንኳን አፋሮች የሉም።

ለምን ይመስልዎታል?

ድሮ የተማረ የሰው ኃይል የላችሁም ይሉን ነበር። ካልተማርክ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ልትሆን አትችልም፤ ልክ ነበሩ።

አሁንስ?

አሁን በጤና፣ በምህንድስና፣ በሳይንስ፣ በአስተዳደር የአፋር ሕዝብ በዚህ ሰዓት ከማንም አያንስም። ነገሩ መዋቅራዊ ግፉእነት (Structural marginalization) ነው በአፋር ሕዝብ ላይ ላለፉት 50 ዓመታት የተደረገው።

የኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት "ዘላን ርስት የለውም" ይለን ነበር። ደርግም ከመጣ በኋላ፣ ወያኔም በአፋር ሕዝብ ብዝበዛና ጭፍጨፋ ነው ያካሄዱት።

የአፋር ሕዝብ በአገሩ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ሥርዓቶቹ ዕድል ሰጥተውት አያውቁም።

"ገዢ መደቦች የተፈጥሮ ሃብቱን እንጂ የአፋርን ሕዝብን አይፈልጉትም፤ ጉዳያቸው ኾኖም አያውቅም" ትላላችሁ በማኒፌስቷችሁ ላይ። ምን ማለታችሁ ነው?

ይሄኮ በተጨባጭ ያየነው ነው። የኖርነው ነው።

ሩቅ ሳንሄድ ወያኔ ምንድነው ያደረገው። ሰፊውን የጨው መሬት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በእጁ አስገባ። አንድ በል።

አፋሮችን ያኔ ምን ያሠራቸው እንደነበር ታውቃለህ? መጥረቢያ ይዘው፤ ጨው መቅረጽ (እንደ ብሎኬት ቅርጽ ማውጣት) ነበር የሚሠሩት።

አፋሮች "የቀን ጆርናታ" ነበር የሚከፈላቸው። በዚያ በረሃ፣ ቁምጣ ለብሰው የጨው ቅርጽ ማውጣት ነበር ሥራቸው።

የመሬት ባለቤትነት መብት የላቸውም፤ የአምራችነት መብት የላቸውም። የነበራቸው ተሳትፎ የጉልበት ሠራተኝነት ብቻ ነው። በዚያ በበረሃ። አፍዴራ ብትሄድ ይህን ታያለህ።

እንቀጥል፤ አብአላ ሂድ። ከፍተኛ የወርቅ ክምችት አለ። ብሔራዊ ባንክ ቅርንጫፍ ከከፈተባቸው ቦታዎች አንዱ እዚያ ነው። ፖታሽ አለ። ከፍተኛ ምዝበራ ነበር የሚደረገው። አፋር ግን ተጠቃሚ ሆኖ አያውቅም።

በራሱ መሬት ላይ እንግዳ የሆነ ሕዝብ ቢኖር የአፋር ሕዝብ ነው።

በተጠቃሚነት ደረጃ ተገለን ቆይተናል ነው የሚሉኝ? ግን'ኮ ያው ሁሉም ክልል ይህንን ነው የሚለው ...

ምን መሰለህ!

እኛ ቅድሚያ የምንሰጠው የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነትን ነው። በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ አንደራደርም፤ በፍጹም።

ይሁንና እንደ አፋር በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ መከበርንም፣ መክበርም እንፈልጋለን። ሀብት ማፍራት ማደግ እንፈልጋለን። መልማት እንፈልጋለን።

የኛ ሴቶች ምጥ ሲመጣባቸው ሌላ ክልል እንዲሄዱ አንፈልግም። ሌላው "እኔ አውቅልሃለው" እንዲለን አንፈልግም። ራሳችንን ችለን መቆም እንፈልጋለን።

ኤርታሌ ቱሪስት የሚያስደነግጥ ቦታ ነው። አፋር የቱሪስት ገነት ሆና ለምንድነው "ቱሪስት አንድ ቀን የማያድርባት ከተማ የተባለችው? ብትመረጡ በዚህ ረገድ ምን አስባችኋል?

ዳሎል የዓለማችን ዝቅተኛ ቦታ ነው። ኤርታሌ የዓለማችን ሞቃታማው ቦታ ነው። ሉሲ አዳኣር ላይ ነው የተገኘችው።

ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ሉሲ የተገኘችበት ቦታ ላይ ትልቅ ሙዝየም በመገንባት እዚህ አፋር እንድትመጣና እንድትጎበኝ እንፈልጋለን።

የአገር ውስጥ ቱሪስቱም የውጭ ቱሪስቱም እኛ ጋር መጥቶ እንዲጎበኛት ነው ፍላጎታችን።

የደኅንነት የምቾት የትራንሰፖርትና የሆቴል አገልግሎቶችን ማዘመን አስበናል። ቱሪስቶች ተመችቷቸው ሄደው ስለኛ መልካም ትዝታቸውን እንዲያጋሩ ማድረግ አለብን።

የአርብቶ አደር የግጦሽ መሬት ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥ እንሠራለን ትላላችሁ። አልተረጋገጠም እንዴ?

አልተረጋገጠም። የግጭቶች መነሻም ከዚህ የተነሳ ነው።

አሁን ትላልቅ ፋብሪካዎች ይከፈታሉ። ተንዳሆ፣ የከሰም ስኳር ፋብሪካ እርሻ ልማቶችም አሉ።

ማኀበረሱ በአንድ ቦታ ረግቶ የማይኖር፣ ተንቀሳቃሽ ስለሆነ ብቻ ባዶ መሬት ሲያዩ ተንሰፍስፈው ይወስዱታል። ይሄ መሬት ባለቤት እንዳለው ይረሳሉ።

አርብቶ አደሩ ተንቀሳቃሽ ነው ማለት የመሬት ይዞታው አይረጋገጥለት ማለት አይደለም።

የአርብቶ አደሩን ጉዳይ እንመለስበታለን። በአፋር ከተሞች ውስጥ ነጋዴዎች በሙሰኛ ባለሥልጣናት ፍዳቸውን ነው የሚበሉት ይባላል።

የአፋር ሕዝብ ጉዳት ተናግረናል፤ በክልላችን ያሉ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችን ጉዳትም መናገር አለብን።

በትውልድ አፋር ያልሆኑ ሰዎች የሚሠሯዋቸው ሥራዎች አሉ። በብዛት ነጋዴዎች ናቸው። ነጻ ሆነው እንዳይሠሩ ሥርዓት የለም። በግብር ያሠቃይዋቸዋል።

ማንኛውም የክልሉ ባለሥልጣን ብር ባስፈለገው ሰዓት ብር አምጣ ይልሃል። ሾፌሩን ነው የሚልክብህ።

የሚገርም ነገር ልንገርህ፤ በአፋር ሾፌሮች ዕቁብ አላቸው።

ዕቁብ የገቡት በየሳምንቱ ለደንብና ሥርዓት አስከባሪዎች ለመስጠት ነው። የሚያሳዝን ነው።

በብዛት አፋር ተወልደው አፋር ያደጉ ነጋዴዎችን ነው የሚያሰቃዩት። የመለወጥ መብታቸውን ነው የነፈጉት። ወንድሞቻችን እዛ መኖራቸው አልቀረ፣ ለፍቶ ማደራቸው አልቀረ፣ በዚያ በረሃ ላባቸውን ጠብ አድርገው መኖራቸው አልቀረ።

አንድ ባለሥልጣን መጥቶ ሀብትህን ይቀማዋል። የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት የሚጻረር ነው።

ዱብቲን ብታያት የምትገርም ከተማ ናት። ትልቅ የገበያ ቦታ ናት። ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ ያለባት ከተማ ናት።

አንድ ደህና ቤት የለም። ገብተህ ምግብ በልተህ ረክተህ አትወጣም። እንዳሉ የቆርቆሮ ቤቶች ናቸው። የጦር ካምፕ ነው የሚመስሉት።

እዛ ውስጥ እየሠሩ ያሉት ለምንድን ነው ዘመናዊ ሱቅ የማይከፍቱት ስትል ያለተተመነና መጠኑ የማይታወቅ ግብር ይዘውብን ይመጣሉ ይሉሃል። ይሄ ያሳፍራል።

ባለሥልጣኖቹ ሾፌራቸውን እየላኩ ነጋዴን "ብር ላክ" እያሉ ማሰቃየት ማቆም ይኖርባቸዋል።

በክልላችሁ ከለውጡ በኋላ ለውጥ አለ?

እውነት ለመናገር በክልል ደረጃ ያለው አመራር በጣም የሚደነቅ ነው። ትልቅ አክብሮትም አለን፤ ለሰዎቹ። በደፈናው መጨፍለቅ አካሄዳችን አይደለም።

የክልሉ ፕሬዝዳንትም ሌሎቹም ከፓርቲያችን ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያላቸው። በብዙ ነገሮች ላይ አብሮ መሥራቱ አለ። ሌሎች ክልሎች ጋር ባልተለመደ ሁኔታ አብሮ የመሥራቱ ነገር እኛ ጋር አለ።

ነገሩ የሚበላሸው ወደታች ሲወርድ ነው። ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ነግርያቸዋለሁ። ከአዲስ አበባ ወጥተህ ክልል ስትሄድና ወደታች ስትወርድ የብልጽግና ለውጥ እየጠፋ ይሄዳል። የታችኛው መዋቅር ለውጡን አያውቀውም ብያቸዋለሁ።

ለምሳሌ ዕጩዎቻችንን ከሥራ ያባርሩብናል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ዘመቻ ስናደርግ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ ሲወጣ ወረዳ ላይ ያሉ ካድሬዎች ይደነግጣሉ። በኛ ክልል እንዲህ ዓይነት ቅስቀሳ ኖሮ አያውቅም። ያስደነግጣቸዋል።

በቃ እነዚህ ሰዎች ሊያጠፉን ነው ብለው ስለሚሰጉ ወከባ ይፈጥሩብናል።

አንዳንድ ቦታ ደግሞ አዳራሽ መጥተው መክፈቻ ንግግር አድርገው አይዟችሁ፣ አገራችሁ ነው ብለው አበረታተውን የሚሄዱ ካድሬዎች አሉን።

"ይህን ትግል እናንተ ናችሁ ያመጣችሁት። በምርጫና በምርጫ ብቻ እንሸናነፋለን፤ አብሽሩ" ብለው የሚያሰናብቱንም አሉ።

ነገሮች የማይስተካከሉ ከሆነ ከምርጫው እንዳንወጣ ስጋት አለን።

አርብ አደር የምንወክል ፓርቲ ነን ትላላችሁ። አርብቶ አደሩ ማኅበራዊ ፍትሕን ይናፍቃል። የአርብቶ አደሩን አጀንዳ ብሔራዊ አጀንዳ የምታደርጉት እንዴት ነው?

በኢትዮጵያ ደረጃ የሚወጡ ማናቸውም ፖሊሲዎች አርብቶ አደሩን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ታግለናል። ትግላችን ይቀጥላል። ለምሳሌ የምርጫ ሕጉ ሲወጣ ፓርላማ ላይ 6 አንቀጾች እንዲስተካከሉ ያደረግነው እኛው ነን።

የምርጫ ሕጉ አንድ ሰው መራጭ ለመሆን ሁለት ዓመት መኖር አለበት የሚል ነበር። ይሄ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ያላገናዘበ ነው በሚል አንስተን ተስተካክሏል። ሌሎችም ብዙ አሉ።

የቤት ቁጥር የግድ ነው ይላል መራጭ ለመሆን። የኛ ሕዝብ የቤት ቁጥር የለውም። ተንቀሳቃሽ ነው። ይህን አስተካክለናል።

የአርብቶ አደር ፖሊስ እንዲቀረጽ ከፍተኛ ጫና ያደረገው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ነው።

አሁን በሚኒስተሮች ምክር ቤት ፖሊሲው ጸድቆ ወደ ትግበራ ሊገባ ደርሷል።

እንግዲህ አስበው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የእንሰሳት ሃብት ደረጃ በአንደኝነት ተቀምጣ እስከዛሬ ድረስ የአርብቶ አደር ፖሊሲ የሚባል ነገር አልነበራትም።

አርብቶ አደሩ ከሕዝቡ በመቶኛ ምን ያህል ነው?

በቁጥር ደረጃ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ይሆናል። በመሬት ስፋት የአገሪቱን 62 ከመቶ ይሸፍናል። በውጭ ምንዛሬ ረገድ ከቡና ቀጥሎ በ2ኛ ደረጃ ነው የሚጠቀሰው፤ የእንሰሳት ተዋጽኦ።

የእርሻ ጠቅላላ አገራዊ ጥቅል ምርት (GDP) አርብቶ አደሩ 43 በመቶ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ ዘርፍ በፖሊሲ ካልተደገፈ እንዴት ነው አገር ወደፊት የምትሄደው?

እኛ በፖሊሲ ደረጃ ነው የምንታገለው። በእስክሪብቶ ነው የምንዋጋው፤ በፌዴራል ደረጃ ጀምረናል ለውጡን እናስቀጥላለን።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም እና ሌሎች አመራሮች

የፎቶው ባለመብት, APP

በአፋርና በሶማሌ አዋሳኝ ቦታዎች በቅርቡ ግጭት ነበር። አቶ ሙስጠፌና አቶ አወል ተገናኝተው እንፈተዋለን ሲሉ ነበር። በእርግጥ እንፈተዋለን ስላሉ የሚፈታ ነው? የአፋርና የኢሳ ግጭት ድሮም የነበረ ነው። ለምን አልተፈታም?

በአጭሩ ልመልስልህ። የመንግሥት ክፍተት ነው የችግሩ ምንጭ። ምን ማለቴ መሰለህ?

አቶ ሙስጠፌና አቶ አወል ተገናኝተው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር ተወያይተው ውሎ ሳያድር በነገታው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፋጅተዋል።

ስለዚህ በወሬ ችግሩ አይፈታም። ትክክለኛ የመፍትሄ ፍላጎትና ፍለጋ አልነበረም።

የሦስቱ ቀበሌዎች ጉዳይ ብዙም ውስብስብ አይደለም። የአፋር ክልል አስፈላጊውን ሁሉ ለእነዚህ ቀበሌ ነዋሪዎች በማድረግ የሚፈታ ነው።

አፋር ክልል ትምህርት ጤና መሰረተ ልማት ሊያቀርብላቸው ግዴታ አለበት።

ነዋሪዎቹ ሶማሌዎች ናቸው አይደል፤ በሦስቱ አወዛጋቢ ቀበሌዎች?

እና ሶማሌ ቢሆኑስ መሠረት ልማት መነፈግ አለባቸው?

እንደዛ ማለቴ ሳይሆን ጥያቄያቸው የቦታ ይገባኛል ሳይሆን የልማት ነው ወይ ማለቴ ነው?

አዎ በአፋር ክልል የሚገኙ ልዩ ቀበሌዎች ናቸው። ሶማሌዎች ናቸው የሚኖሩበት።

በዚያ በኩል ደግሞ ይሄን እንወስዳለን ይህን እንመልሳለን ማለት ሳይሆን፤ ሕግና ሥርዓትን መከተል አለበት። በመንግሥት ደረጃ ድንበር ማካለል መሠራት አለበት። "ያ የኔ ነው፤ ይሄ የኔ ነው" መባባል ሳይሆን እንደ ዘመናዊ ሰው ተነጋግሮ መፍታት ያስፈልጋል። ወሰን ማበጀት ያስፈልጋል።

ሁለቱ ሕዝቦች ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያቀራርባቸው ነገር ይበዛል። እንዴት ነው ወደ ግጭት የሚገቡት?

ሁለቱ ሕዝቦች ተፈጥሮ ያጎራበተቻቸው አንድ ዓይነት የጉስቁልና ሕይወት የሚመሩ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው።

በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ገሸሽ የተደረጉ ግፉኣን ናቸው። በዚህ ችግር ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ አያስፈልግም።

እኛ መንግሥት ስንሆን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ይህ ነው።

አፋር የኢትዮጵያ ጉሮሮ ነው የምትባለው። አፋር ሰላም ከሌለ የመሐል አገር ሰው ጋር በነገታው ነው ሕመሙ የሚደርሰው። ይህ በቅርቡ በነዳጅም እጥረትም ታይቷል። የክልላችሁን በአስተማማኝ ሰላም ለማስጠበቅ የትኛውን መንገድ ትከተላላችሁ? የልዩ ኃይል ማደራጀትን ታምኑበታላችሁ?

ልዩ ኃይልን በተመለከተ አንድ ወጥ አገራዊ አቅጣጫ መቀመጥ አለበት ብለን ነው የምናምነው።

መደበኛ ፖሊስ አለ፣ ፌዴራል ፖሊስ አለ፣ መከላከያ አለ። ወደ ታች ስትወርድ ሚሊሻ አለ። እነዚህ በቂ ናቸው ብለን እናምናለን።

ዘመናዊ ዓላማ ያለው የሰለጠነ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል። ምን እያደረጉ እንደሆኑ የሚያውቁ። ለዜጎች ከለላ መስጠት እንጂ ደኅንነት መንሳት ሥራቸው እንዳልሆነ የሚያወቁ የጸጥታ ኃይሎች ያስፈልጋሉ።

የክልሎች የልዩ ኃይል ፉክክር ያሳስበናል። ከሁለቱ አንዱ መሆን አለበት። ወይ በአገር ደረጃ ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች መበተን አለባቸው። ወይ ደግሞ ሥርዓት ያለው ፊትና ኋላው የሚታወቅ የተለየ ተልእኮ ያለው ኃይል መገንባት አለበት።

ምን ማለቴ ነው? ለምሳሌ በፊት ፊናንስ የሚባሉ ነበሩ። ከኮንትሮባንድ ጋር የተያያዙ ቁጥጥሮችን የሚከታተሉ።

የጸረ ሽብር ግብረ ኃይል አለ። ተልዕኮው ተለይቶ የተቀመጠለት። እንደዚህ ለተለየ ተልዕኮ ጸጥታ መዋቅር ሊያስፈልግ ይችላል እንጂ ልዩ ኃይል መልካም ነገር ይዞ ይመጣል ብለን አናስብም። ይሄ የመንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ ነው የሚሆነው።

ከጂቡቲ ጋር በተያያዘ ስለ ጂቡቲ ከአፋር የተሻለ ሊናገር የሚችል የለም። ቤተሰብ ሕዝብ ነው። አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ...። እንደው በረዥም ዘመን ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ኅብረት ፈጥራ ሉአላዊነቷ እንደተጠበቀም ቢኾን ለኢትዮጵያ ነጻ የንግድና እንቅስቃሴ ቀጠና ሆና በአንድ አገራዊ ስሜት ከኢትዮጵያ ጋር የምትቀርብ ይመስልዎታል?

በቅድሚያ የእነርሱን ሉዓላዊነት መንካት አልፈልግም። ከጠየቅከኝ አይቀር አንድ ነገር ልንገርህ።

የጂቡቲ ጉዳይ የኛ ጥንካሬ ላይ የሚመሠረት ጉዳይ ነው፡፡ ጂቡቲና ኢትዮጵያ ፈቅደው አንድ ለመሆን የሚቸገሩ አገሮች አይደሉም። የሩቅ ነገርም አይደለም። ይገባኛል! እንዴት ፖለቲከኛ እንዲህ ይላል ልትለኝ ትችላለህ።

በአጭሩ ላስረዳህ። ጂቡቲ ላይ ያሉት ኢሳና አፋሮች ናቸው። የነሱ ትልቁ የቤተሰብ ግንድ ያለው እዚህ አፋር ኢትዮጵያ ነው። ከዚህ ጂቡቲ የሄደ እንጂ ከጂቡቲ እዚህ የሰፈረ ሕዝብ የለም።

አፋር እኮ እዚያ አጎት፤ እዚህ አክስት አለው። አባት እዛ ነው ልጅ እዚህ ነው። እናት እዛ ልጂቱ እዚህ። በቃ ምን ልበልህ ቤተሰብ ነው። ኢሳውም በተመሳሳይ ማለቴ ነው።

ስለዚህ እኛ ከጠነከርን በተለይ አንድ የኢኮኖሚ አገር ከጂቡቲ ጋር ለመፍጠር የሩቅ ዕቅድ ኾኖም አይደለም የሚታየን።

ለምሳሌ ሱዳንን በቤኒሻንጉል እንጎራበታለን። ወደ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመምጣት ግን አስቸጋሪ ነው። ትልቅ አገር ነው። ብዙ ብሔር ያለበት አገር ነው፤ ሱዳን።

ጂቡቲ ግን ኢሳና አፋር ነው። የኔ ወንድምና እህቶች ናቸው። ቤተሰብ ነን።

ስለዚህ እንደ ቤተሰብ ልንይዛቸው ነው የሚገባው። ውሃ ማቅረብ። ኤሌክትሪክ ማቅረብ፣ መሠረተ ልማት ማቅረብ፤ ንግዱን ማሰባጠር ነው። ቀስ በቀስ በምጣኔ ሀብት "ኢንተግሬትድ" መሆን ቀላል ነው።

ይህ በተለይም በሶማሌ ክልልና በአፋር ክልል በኩል መሆን የሚችል ነገር ነው። ይህ በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ አንድነትና ጥንካሬ መሳካት የሚችል ነገር ነው።

ጂቡቲን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ለእኛ ለአፋሮች ከባድ ሥራ አይደለም።

በአፋር በኩል መሳለጥ የሚችል ነገር ነው።

እኔ አሁንም ቢሆን የጂቡቲን ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት አይደለም። በመፈቃቀድ ግን አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት የሩቅ ነገር ተደርጎ መታሰብ የለበትም።

ጎጠኝነትን እየተውን ከመጣን ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ አይደለም።

ኢስማኤል ኡማር ጊሌ ባለፈው አዋሽ ወንዝን መጠቀማችንን እናረጋግጣለን የሚል ይዘት ያለው ትዊት አድርገው ነበር። አይተኸዋል?

አዎ አይቼዋለሁ።

እሳቸው ራሱ የኛ ስለሆኑ ነው አዋሽን 'የኛ ነው' የሚሉት ብለን ነው የወሰድነው። ለዚያ ነው ያልተገረምነው። ያልተናደድነው።