ምርጫ 2013፡ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያልተስማማቸው ሕብረቱ ሉዓላዊነትን የሚጻረር ጥያቄ በማቅረቡ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ ምርጫ ለመታዘብ ካቀደው የአውሮፓ ሕብረት ጋር ያልተስማማቸው ሕብረቱ ሉዓላዊነትን የሚጻረር ጥያቄን በማቅረቡ ነው ሲሉ የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከስምምነት መድረስ ባለመቻሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ አስቦ የነበረውን የምርጫ ታዛቢ እንዲቀር መወሰኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሕብረቱ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ለመላክ ከፍተኛ ጥረት ቢያደረግም ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚሰማራበት ቁልፍ መለኪያዎች /ፓራሜትርስ/ ላይ ከስምምነት መድረስ አልተቻለም ብሏል።
ሕብረቱ ያልተሟሉ መስፈርቶች ያላቸው የምርጫ ታዛቢው ልዑክ ገለልተኝነት ማረጋገጥ አለመቻሉ እና ልዑኩ የራሱን መገናኛ ስርዓቶች ወደ አገር ማስገባት አለመቻሉ ናቸው።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ማክሰኞ ረፋድ ላይ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑኩን ላለመላክ የወሰነው በሁለት ምክንያት ነው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ሕብረቱ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይስማሙ የቀሩበት ጉዳዮች፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረሩ እና የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ከሕብረቱ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ መቅረቱን አብራርተዋል።
የቴሌኮሚኒኬሽን ስርዓት
አምባሳደር ዲና የመጀመሪያ፤ ሕብረቱ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የጠየቀው የግንኙነት ስርዓት የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው ብለዋል።
ሕብረቱ 'ቪሳት' የሚባል ኢትዮጵያ የሌላት የቴሌኮሚኒኬሽን ስርዓት ወደ አገር ውስጥ ለመስገባት ጫና ማድረጉን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች፤ የውጪ ታዛቢዎች ወደ አገር ሲገቡ መሰል የግንኙነት መሳሪያዎችን ለመጠቀም ጥያቄ ቀርቦ እንደማያውቅ አስታውሰዋል።
"ታዛቢዎችም ሊጓዙባቸው የሚችሉባቸው ቦታዎች የአገሪቱ የቴሌኮሚኒኬሽን ስርዓት የተዘረጋባቸው ናቸው። እሱን መጠቀም ይችላሉ፤ ከዚህ ውጪ አገሪቱ የሌላትን የቴሌኮሚኒኬሽን ስርዓት ይዘን እንገባለን ማለት እኛ እናስተዳደራችሁ ማለት ነው" ብለዋል።
'የምርጫ ውጤት ይፋ ምናደርገው እኛ ነን'
መንግሥት ከሕብረቱ ጋር ያልተስማማበት ሁለተኛው ነጥብ ሕብረቱ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀድሞ የምርጫውን ውጤት ይፋ የማደርገው እኔ ነኝ ማለቱ መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
"ይህ በየትኛው አገር የማይታሰብ ነው" ያሉት አምባሰደር ዲና፤ የምርጫ ውጤትን መግለጽ ያለበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው ብለዋል።
"በቅድሚያ ምርጫው የሚያረጋግጥልን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ከዚያ ቀጥሎ የምርጫ ቦርድ ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 2013 ዓ.ም. ለማካሄድ ላቀደችው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን መራጮችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ጥላቸውን ከጣሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚቀሰቀሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች ናቸው።

በሌላ በኩል አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች ኢትዮጵያ የምታካሂደው ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም ማለታቸው ይታወሳል።
ሴናተሮቹ ይህን ያሉት በቅርቡ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለተሾሙት አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ ነው።
ሴናተሮቹ ከሳምንታት በኋላ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም ብለዋል።
ሴናተሮቹ ምርጫውን በተመለከተ ይህን ማለታቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይሁን መንግሥት ቀጣዩ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።












