አምስት ሴናተሮች ቀጣዩ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ 'ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም' አሉ

የፎቶው ባለመብት, @rosenfornevada,@SenatorKaine, @Corybooker
አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች ኢትዮጵያ ከአምስት ሳምንታት በኋላ የምታካሂደው ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም አሉ።
ሴናተሮቹ ይህን ያሉት በቅርቡ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለተሾሙት አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ ነው።
ሴናተሮቹ ቤንጃሚን ኤል ካርዲን፣ ቲም ኬይን፣ ጃኪ ሮስን፣ ኮርይ ኤ ቡከር እና ኤድዋርድ ጄ ማርኬይ ስለመጪው አገራዊ ምርጫ፣ ስለትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ስፍራዎች ስላሉ ግጭቶች ለተሿሚው ልዩ መልዕክተኛ መልዕከታቸውን አጋርተዋል።
"ምርጫው ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም"
ሴናተሮቹ ከሳምንታት በኋላ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም ብለዋል።
በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ተዓማኒነት ባለው መልኩ ሊካሄድ አይችልም በሚል ምክንያት ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ሴናተሮቹ በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል።
በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች እና አመራሮች መታሰር በምርጫው እምነት ለማጣታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሴናተሮቹ ምርጫውን በተመለከተ ይህን ማለታቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲዎች አባላቶቻችን እና አመራሮችን ለእስር እየተዳረጉ ነው፣ ቢሮዎቻችን እየተዘጉ ስለሆነ በምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችል ሁኔታ የለምበሚል ምክንያት በምርጫው እንደማይሳተፉ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይሁን መንግሥት ቀጣዩ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ሴናተሮቹ፤ "የኢትዮጵያን ሕዝብ እምነት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ማሻሽያዎች ሳይደረጉ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ዘርን እና ፖለቲካን መሠረት ያደረገው ውጥረት በመላው አገሪቱ ነግሶ ወደ ከፋ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት አለን" ብለዋል።
የትግራይ ቀውስ
ሴናተሮቹ በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው፣ 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅሎ እንደሚገኝ እና ወደ 62ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አገር ጥለው መሰደዳቸውን በደብዳቤያቸው አትተዋል።
ሴናተሮቹ ለልዩ መልዕክተኛው በጻፉት ደብዳቤ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲረጋገጥ፣ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ፣ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ እና ጥፋተኞች ለሕግ እንዲያቀርቡ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን እንዲጠቀሙ እናበረታታዎታለን ብለዋል።
የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ያለፉት የደህንነት ስጋት ስላለባቸው መሆኑን በመግለጽ ከኢትዮጵያ እንደሚወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መናገራቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ መንግሥትም ጦሩን ከኢትዮጵያ እንደሚያስወጣ ገልጿል።
ብሔር ተኮር ግጭቶች
አራቱ ሴናተሮች በኢትዮጵያ ያለው ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ያሳስበናል ብለዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የደረሱ ጥቃቶችን አስታውሰው፤ ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ሰላም፣ እርቅ እና መቻቻልን እንዲኖር እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፌልትማን ማን ናቸው?
አሜሪካ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ ባሉ አገራት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች በቅርበት እንዲከታተሉላት አምባሳደር ጆፈሪ ፌልትማንን መሾሟን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።
ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።












