የኢትዮጵያን ባሕል እያስተዋወቀች የምትገኘው ‘ኩኩሉ’

የፎቶው ባለመብት, Qene Games
ልክ እንደፋሲካ ባለ አንድ የበዓል ማለዳ የገዟት ዶሮ ከቁጥጥር ውጪ ብትሆንብዎትስ? ነገሩን ከዶሮዋ አንጻር አስበውት ያውቃሉ? እርሰዎ ለበዓሉ ድምቀት ዶሮዋ ተስፈልጎታለች- ስለዚህ ያሳድዷታል። ዶሮዋ ደግሞ ነፍሷን ለማትረፍ እግሬ አውጪኝ ትላለች።
ቅኔ ጌምስ በተባለ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ የበለጸገው 'ኩኩሉ' የተሰኘው የሞባይል ጨዋታ ወይም ጌም ግን እርስዎን [የጌሙን ተጫዋች] የዶሮዋን ገጸ ባህሪ ያላብስዎታል። የሚገጥሞትን መሰናክል እያለፉ ከሚያሳድዎ ባለቤት ራስዎን አትርፈው ምን ያህል ተጓዙ የሚል ነው እንግዲህ በኩኩሉ ጨዋታ ስኬታማ የሚያደርገዎ።
ኢትዮጵያዊ መቼት
በኩኩሉ የሞባይል ጨዋታ ዶሮዋና ባለቤቷ በሚሯሯጡበት አካባቢ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቋቸው የኑሮ መልኮች አልፎም ባህልና ቅርሶች አይታጡም። የቅኔ ጌምስ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ እንዲሁም ጌም አበልጻጊው ዳዊት አብርሃም በእያንዳንዱ ጌሙን የማበልጸግ ሂደት ወስጥ ኢትዮጵያዊ ብሎም አፍሪካዊ ሀሳቦች ተካተውበታል ይላል።
በጨዋታው መካከለ ጎጆ ቤቶች፣ ታጥበው የተሰጡ ነጠላዎች፣ ጀበና እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅርሶች እንደሚታይ የሚገልጸው ዳዊት የኢትዮጵያ አልባሳትና ሙዚቃ እንደተካተበትም ይናገራል። "ጌሙን ብዙ አይነት የኢትዮጵያን ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበብን ለመላው ዓለም ለማሳየትም የሰራነው ነው" ይላል።
በተጨማሪም በጨዋታው የተዘረዘሩ ደረጃዎችን የሚያልፍ ተጫዎች በሚሰበስበው ነጥብ [ቆሎ] መሰረት ኩኩሉን የተለያዩ ብሄረሰቦችን አልባሳት ማልበስ ይችላል። በሌላ በኩል ሙዚቃው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ባለሙያዎች ለጨዋታው የተዘጋጀ ሲሆን ጌሙ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግረኛና በእንግሊዘኛ ለመጠቀም የሚያስችሉ አማራጮችም አሉት።
ኩኩሉ ጌም በአውሮፓውያኑ 2018 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደ 'አፕስ አፍሪካ' በተሰኘና የሞባይል መተግበሪያዎች ላይ በሚያተኩር ውድድር በምርጥ የመዝናኛ የሞባይል መተግበሪያ [Best African Entertainment Apps] ዘርፍ አሸናፊ ነበር። ይህ ስኬት ለዳዊት ያልተገመተ ነበር። "ከኛ ጋር ትላልቅ ኩባንያዎች ነበሩ። አናሸንፍም ብለን ርግጠኛ ነበርን። ሆኖም አሸንፈናል" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Kene Games
ገበጣ: ሌላ ኢትዮጵያዊ ጌም
ዳዊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 'በኤሌክትሪካል ኤንድ ኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ' የተመረቀ ሲሆን የኩኩሉ ጌም ከሀሳብ ወደ ተግባር የተቀየረው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለ ነበር።
የኩኩሉን የመነሻ ውጤትን ይዞ ከሌላ ጓደኛው ጋር በመሆን ያቋቋመው ኩባንያ አሁን አራት ዓመታት አስቆጠሯል። ኩባንያው በአንድ ባለሃብት አማካኝነት የ8.6 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ማግኘቱንም ይናገራል - ዳዊት።
እናም በኩኩሉ የተጀመረው ሀሳብ ገበጣ ወደ ተባለ ሌላ የኢትዮጵያን ባህል ወደ ሚያስተዋውቅ ጌም ተሸጋግሯል።
የገበጣ ጌም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚዘወተረውን የገበጣ ጨዋታን መሰረት የሚያደርግ ነው።
"ዋናውን የጨዋታውን ሃሳብ ወስደን በዚህ ዘመን ያሉ ጌም ተጫዋቾች ሊጠቀሙበት በሚችሉት መልኩ ቀይረነዋል።
አዳዲስ ህጎችና የጌም ግብአቶችን ጨምረንበታል።" የሚለው ዳዊት ይህ ጌም ከጅምሩ ስኬታማ እንዳደረገው ይገልጻል።
"ይህንኑ ስኬት አይተው የተለያዩ ጌምን የሚያወጡ ድርጀቶች [Game Publishers] አብረን እንድንሰራ ጥያቄዎች ሲያቀርቡልን ነበር። ደቡብ አፍሪካው ውስጥ 'ኬሪፈርስት' ከተባለ ድርጅት ጋር ተፈራርመናል። ጌሙን ወስዶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳተም ሽያጩንና ማስተወቂያውን ለመስራት ነው የተስማማነው" ሲል አስረድቷል።
የደቡብ አፍሪካው የጌም አሳታሚ 'ኬሪፈርስት' ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮርዴል ሮቢን ኮከር "ገበጣ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ እንደሚሆን እምነት አለኝ" ማለታቸውንን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቦ ነበር።
በተጫማሪም ኩባንያው ቀለል ባለ አቀራረብና በኢትዮጵያ ባህልና ምግቦች ላይ የሚያተኩር 'ፈታ' የተሰኘ የእንቆቅልሽ ጨዋታ [Puzzle] ቅኔ ጌምስ አብልጽጓል።

የፎቶው ባለመብት, Dawit
የሞባይል ጨዋታ፣ ባህልና የስራ ዕድል
ጌም ዘመናዊ ጥበብ ነው የሚለው ዳዊት ማንነትን የመግለጫ መንግድ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳል።
"ህጻናት በቋንቋቸው እየተናገሩ በቋንቋቸው ደስ የሚል ነገር እየተመለከቱ ታሪካቸውን እየተመለከቱ ሲያድጉ ለራሳቸው ያላቸው ክብር ይጨምራል።" ሲል ይገልጻል።
በሌላ በኩል የ'ጌም' ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስበት እንደሆነ የሚያነሳው ጌም አበልጻጊው ዳዊት ይህ የስራ ፈጠራ አንድ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የውጪ ምንዛሬን ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳል።
"የጌም ዘርፉ ላይ ጠንክረን ብንሰራ ያለምንም ጥርጥር ኤክስፖርት ከምናረጋቸው ነገሮች ባልተናነሰ ጌም ኤክስፖርት የማድረግ አቅማችን ከፍተኛ ነው ብዬ አስባለሁ። ይሄን ነገር ለማሳካት የሚያስፈልገው ኮምፒውተር፣ኢንተርኔትና የፈጠራ ብቃት ብቻ ነው" ብሏል።
ቅኔ ጌምስ በአፍሪካ ከፍ ብሎም በዓለም ዙሪያ ተወዳዳሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ጨዋታዎች የማበልጸግና ባህሏቿን በማራኪ መንገድ የማቅረብ አላማዎች አሉት። ሆኖም በኢትዮጵያ የሞባይል መተግበሪያዎች በማበልጸግ የሚፈጸም ክፍያን ለማግኘት የሚያስችል ስርዓት አለመኖሩ ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ገልጾል።
ወደ ኩኩሉ ጌም ስንመለስ! በፋሲካ በዓል አውድ ኩኩሉን ሲጫወቱ እርስዎ 'ፎርሸው' ዶሮዋ ብትይዛ ጌሙም ህይወቷም ያበቃል። የባለቤቷ በዓል ደግሞ ይደምቃል። የደመቀ በዓል ይሁንላችሁ!















