በአፍጋኒስታን በደረሰ የቦምብ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, KILLED GROUP
በአፍጋኒስታን የእንግዳ ማረፊያ ቤት አቅራቢያ መኪና ላይ ተጠምዶ የነበረ ቦምብ ፈንድቶ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
ከተገደሉት መካከል የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደሚገኙበት የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የቦምቡ ፍንዳታ የደረሰው በምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው ሎጋር ግዛት ሲሆን ተማሪዎቹ ያረፉበት የእንግዳ ማረፊያ አቅራቢያ ነው ተብሏል።
በጥቃቱ ከሞቱት በተጨማሪ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል። ጣራዎች መደርመሳቸውን እና ተጎጂዎች በፍርስራሽ ስር መያዛቸውን እማኞች ገልፀዋል። ወደ 90 የሚጠጉ ሰዎች ቆስለዋል ያሉት ደግሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ታሪቅ አሪያን ናቸው።
የረመዳን ጾም ማፍጠሪያ ሰዓት አካባቢ ለደረሰው ፍንዳታ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን የለም።
የእንግዳ ማረፊያ ቤቱን ጨምሮ በርካታ ሕንፃዎች በፍንዳታው ተጎድተዋል።
ፍንዳታው ሆስፒታሎችን እና መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በአካባቢው ሰፊ ጉዳት ማድረሱን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
"የቤቶች ጣራ ፈርሶ ሰዎች በክምሩ ስር ተይዘዋል" ብለዋል።
የፀጥታ ኃይሎች እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ህይወት የማዳን ጥረት እያካሄዱ ነው ተብሏል።
በበይነ መረብ በተዘዋወሩ ምስሎች ተጎጂዎችን ከፍርስራሹ ስር ሲወጡ ያሳያሉ።
በካቡል የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ጥቃቱን ያወገዘ ሲሆን "ይህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ትርጉም የለሽ ጥቃት መቆም አለበት" ብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ጦር እስከ መስከረም 11 ቀን ድረስ ሃገሪቱን እንደሚለቅ ከገለጹ ወዲህ አፍጋኒስታን ሁከትና ብጥብጥ ተመላልሶ ጎብኝቷታል።
ፍንዳታው የደረሰው የአሜሪካ ጦር ቀሪ የመጀመሪያ ዙር ወታደሮቹን ከአፍጋኒስታን በይፋ ማስወጣት ከመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት ነው።
ሀገሪቱ ከቅርብ ወራቶች ወዲህ በሠላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ጨምሮ የሽምቅ ተዋጊዎች አመጽ እየጨመረ መጥቷል።












