ከሕንድ የሚመለሱ አውስትራሊያውያን እስር ወይም የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሕንድ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ አውስትራሊያውያን እስከ አምስት ዓመት እስራት እና የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የአውስትራሊያ መንግስት ገለጸ።
የአገሪቱ መንግሥት ከሕንድ ወደ አውስትራሊያ የሚደረግ ጉዞ ሕገ-ወጥ ነው ብሏል።
የአውስትራሊያ የጤና ሚንስትር መንግሥት ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው በሕንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጨመርን ተከትሎ ነው ብለዋል።
አውስትራሊያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከሕንድ የሚመጡ በረራዎችን በሙሉ አግዳለች።
9,000 የሚደርሱ አውስትራሊያዊያን በሕንድ ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 600 የሚሆኑት ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ተብለው ተለይተዋል።
አውስትራሊያውያን ወደ አገራቸው በመመለሳቸው በወንጀል ሲከሰሱ ይህ የመጀመሪያው እንደሚሆን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
አንድ አውስትራሊያዊ የሕክምና ዶክተር የመንግሥት ውሳኔ ከሕንድ የሚመለሱ ሰዎች ከሚያደርሱት ስጋት ጋር የማይመጣጠን ነው ብለዋል።
"ቤተሰቦቻችን ሕንድ ውስጥ እየሞቱ ነው ... እነሱን ለማውጣት ምንም መንገድ አልተመቻቸም። ይህ ምንም ድጋፍ ሳይደረግላቸው መተው ነው" ሲሉ የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ቪዮም ሻርመር ገልጸዋል።
ማንኛውም ዜጋ አውስትራሊያ ለመግባት ካቀደበት ቀን በፊት ባሉት 14 ቀናት ውስጥ በሕንድ ከነበረ ወደ አውስትራሊያ መግባት አይችልም።
ውሳኔውን አለመተግበር ለአምስት ዓመት እስራት ወይም ለ 37,000 ፓውንድ ቅጣት ወይም በሁለቱም ያስቀጣል።
ውሳኔው ግንቦት 15 ቀን እንደሚገመገም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ሚኒስትሩ ግሬግ ሃንት በመግለጫቸው "መንግሥት እነዚህን ውሳኔዎች በቀላል አልወሰነም" ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ቬንትሌተሮችን እና የመከላከያ አልባሳትን ጨምሮ አስቸኳይ የህክምና አቅርቦቶችን ለመላክ ከሕንድ ጋር መስማማቱን ገልጿል።
መግለጫው አክሎ "ለሕንድ ህዝብ እና ለሕንድ-አውስትራሊያዊ ህብረተሰባችን ሃዘናችንን እንገልጻለን" ብሏል።
በሕንድ የቫይረሱ ስርጭት ወደ 19 ሚሊዮን ከፍ ሲል የሟቾቹ ቁጥር 200 ሺህ ደርሷል። ባለፈው ሳምንት በየቀኑ ከ 300 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ነበር።












