አሜሪካ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ለማስውጣት ተጨማሪ ጦር ልካለች

የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ለሚወጡት የአሜሪካ እና ለጥምር ጦሩ ሽፋን የሚሰጥ ወታደራዊ ኃይል አሰማራች።

ወታደሮችን እና ሲቪል ሠራተኞችን ለመጠበቅ ቦምብ ጣይ እና ተዋጊ አውሮፕላኖች ተመድበዋል።

አሜሪካ እና ኔቶ በአፍጋኒስታን ለ 20 ዓመታት ያህል ቆይተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የመስከረም 11 ጥቃት 20ኛ ዓመት መታሰቢያ ዕለት የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ እንደሚለቅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የጦሩ የመውጣት ዜና ከተሰማ ጀምሮ በየአቅጣጫው ጥቃቶች የበረከቱ ሲሆን የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች የበቀል እርምጃ ይኖራል በሚል በተጠንቀቅ ቆመዋል።

ታሊባን ዓለም አቀፍ ወታደሮችን ዒላማ እንዳያደርግ የተደረሰበት ስምምነት እንደማይገዛው አስጠንቅቋል።

ታጣቂዎቹ እና ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባለፈው ዓመት በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት ታሊባን ዓለም አቀፍ ወታደሮችን የማያጠቃ ሲሆን የውጭ ኃይሎች ደግሞ እስከ ግንቦት 1 ቀን መልቀቅ ነበረባቸው።

አሜሪካ ምን አሰማራች?

2500 የአሜሪካ የጦር አባላት እና ለ 16,000 ሲቪል ተቀጣሪዎችን ሽፋን እየሰጡ ለማስወጣት ስድስት ቢ-52 ቦምብ ጣይ እና 12 ኤፍ-18 ተዋጊ ጄቶች መሰማራታቸዉን የጥምር ጦሩ ኤታማዦር ሹም ሊቀመንበር ማርክ ማይሊ ገልጸዋል።

ጄኔራል ማይሊ አክለውም የታሊባን ታጣቂዎች በየቀኑ ከ 80 እስከ 120 ጥቃቶችን በአፍጋኒስታን መንግሥት ላይ ቢፈጽሙም ጦሩ መውጣት ከጀመረበት ከግንቦት 1 ጀምሮ በአሜሪካ እና በጥምር ኃይሉ ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳልነበረ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ጦር ለምን በአፍጋኒስታን ተገኘ?

እአአ መስከረም 11/2001 በአሜሪካ በተፈጸመ ጥቃት ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የአልቃይዳ መሪ የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ከጥቃቱ ጀርባ መሆኑ ታወቀ።

አክራሪዎቹ ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ሲያተዳድሩ የነበረ ሲሆን ቢንላደንን አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ከመስከረሙ 9/11 ጥቃት ከአንድ ወር በኋላ አሜሪካ በአፍጋኒስታን የአየር ድብደባ ጀመረች።

ሌሎች ሀገራትም ጦርነቱን የተቀላቀሉ ሲሆን ታሊባንም በፍጥነት ከስልጣን ተወግዷል። ከስልጣን ቢወርዱም ጠፍተው አልጠፉም እንዲያውም ተጽዕኗቸው እያደገ ነው።

በኋላም አሜሪካ እና አጋሮቿ የአፍጋኒስታንን መንግሥት ከመፍረስ ለማስቆም እና በታሊባን የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ሲጥሩ ቆይተዋል።

አፍጋኒስታን አሁን ምን ትመስላለች?

የአሜሪካ ጦር መውጣት መጀመሩን ተከትሎ የሠላም ስምምነት ባለመኖሩ ታሊባን እና የመንግስት ኃይሎች መካከል ከባድ ፍጥጫ ተፈጥሯል።

ባለፈው ሳምንት በሎጋሪ አውራጃ በፑል-ኤ-አላም በተፈጸመ ጥቃት 30 ሰዎች ሲገደሉ 110 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ከእነዚህ ውስጥ በአብዛኛዎቹ ተማሪዎች ናቸው።

ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ ጦር መውጣት አፍጋኒስታን የውጭ ጂሃዳውያን የጥቃት መነሻ በመሆን ለምዕራባውያን ስጋት እንደማትሆን ስላረጋገጥን ውሳኔው ተገቢ ነው ብለዋል።

የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ የመንግሥት ጦር አመጸኞችን ለመቆጣጠር ሙሉ ብቃት አላቸው ብለዋል።

የጦሩ መውጣት በሁሉም ዘንድ በበጎ ጎኑ አልታየም ምክንያቱ ደግሞ ሀገሪቱን ወደ የታሊባን የጨለማ ዘመን ሊመልሳት ይችላል በሚል ነው።