አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያሉ ወታደሮቿ በመጪው መስከረም ይወጣሉ

የአሜሪካ ወታደሮች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወታደሮቻቸው በመጪው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አፍጋኒስታንን ለቅቀው እንደሚወጡ ለማስታወቅ መዘጋጀታቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሀን ገለጹ።

ባሳለፍነው ዓመት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከታሊባን መሪዎች ጋር ግንቦት ወር ላይ ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም አዲሱ ፕሬዝዳንት ግን ወደ መስከረም ገፍተውታል።

በአዲሱ ቀነ ገደብ መሰረት ወታደሮቹ አፍጋኒስታኒንን ለቅቀው የሚወጡ ከሆን ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በዓለም የንግድ ማዕከል ላይ ከደረሰው የሽብር ጥቃት 20ኛ ዓመት ጋር ሊገጣጠም እንደሚችል ተገምቷል።

ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግንቦት ወር ላይ ወታደሮቹን ከአፍጋኒስታን ማስወጣት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

የአሜሪካ እና የኔቶ ኃላፊዎች እንዳሉት ታሊባን በተስማሙት መሰረት በአካባቢው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መቀነስ አልቻለም።

ታሊባን አሜሪካ ወታደሮቿን በምታስወጣበት ጊዜ ላይ ጥቃት የሚፈጽም ከሆነ ከባድ የሀነ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚጠብቀው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩት ከፍተኛ ኀላፊ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተቻኩሎ ወታደሮቹን ለማስወጣት መሞከር ወታደሮቹን አደጋ ላይ ሊጥላቸው እንደሚችል በማሰብ ይህንን እንደወሰኑ ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱም ዛሬ ስለወታደሮች መመለስ በይፋ እንደሚናገሩ ይጠበቃል።

ጥቂት የአፍጋኒስታን ኃላፊዎች የአዲሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አዲስ የሆነ የሰላም መስመር እንደሚከተል ተስፋ እንደሚያደርጉ የገለጹ ሲሆን ወታደሮቹን የማስወጣት ሂደቱን ወደ መስከረም መግፋታቸው ግን አንዳንዶችን አሳስቧል።

በአፍጋኒስታን መንግስትና በታሊባን መካከል የመንግሥት ሰልጣንን እንዴት መካፈል ይቻል በሚለው ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር በጣም አዝጋሚ መሆኑን ተከትሎ የአሜሪካ ወታደሮች ከመውጣታቸው በፊት ስምምነት ላይ ላይደርሱ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ምናልባት ከስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ ታሊባን ለዓመታት ሲናፍቀው የቆየው ዓለማቀፍ ተቀባይነት ሊረጋገጥ ይችላል። ነገር ግን በርካቶች ደግሞ የአሜሪካ ወታደሮች መውጣታቸውን ተከትሎ ታሊባን በኃይል ነገሮችን ለመቆጣጠር ሊሞክር እንደሚችል እየተናገሩ ነው። ምክንያቱም የአፍጋኒስታን መንግሥት አሁንም ቢሆነ የአሜሪካ ወታደሮች የሚያደርጉለት ድጋፍ ከፍተኛ ነው።

ታሊባን በበኩሉ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በሚቀጥለው ወር ቱርክ ውስጥ የአፍጋኒስታን መጻኢ ተስፋ ላይ በሚደረገው ውይይት ላይ እንደማይሳተፍ ያስተወቀ ሲሆን ''ምክንያቴ ደግሞ የውጭ አገር ወታደሮች እስካሁን ከአፍጋኒስታን ስላልወጡ ነው'' ብሏል።

''ሁሉም የውጭ አገራት ኃይሎች ሙሉ በሙሉ አገራችንን ለቅቀው እስካልወጡ ድረስ በቱርክ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ አንሳተፍም'' ብለዋል መቀመጫውን ኳታር ያደረጉት የታሊባን ቃል አቀባዩ ሞሀመድ ናኢም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን እና የአሜሪካ መከላከያ ኃላፊ ሎይድ ኦስቲን ዛሬ የኔቶ አጋሮቻቸውን ከአፍጋኒስታን ወታደሮችን ማስወጣት በተመለከተ ማብራሪያ እንደሚሰጧቸው ይጠበቃል።

አሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት በአፍጋኒስታን ብቻ በርካታ ሚሊየን ዶላሮችን ፈሰስ ያደረገች ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ ከ2 ሺ በላይ ወታደሮቿ ተገድለውባታል።