የ20 አመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ግድያን ተከትሎ የፖሊስ ኃላፊው ከስራቸው ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Katie Wright
ዳውንቴ ራይት የተባለ የ20 አመት ወጣት በሚኒያፖሊስ ከተማ ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ተከትሎ የከተማዋ የፖሊስ ኃላፊ ከስራቸው ለቀዋል።
ከኃላፊው በተጨማሪ የተኮሰችበት ፖሊስም እንደለቀቀች ተዘግቧል።
የፖሊስ ኃላፊ ቲም ጋኖንና የተኮሰችበት ፖሊስ ኪም ፖተር ከብሩክሊን ሴንተር ኃይል ስራቸው የለቀቁት ዳውንቴ መገደሉን ተከትሎ ለሁለት ቀናት ያህል ከፍተኛ አለመረጋጋትና ሁከት በመነሳቱ ነው።
ፖሊሷ ዳውንቴን ጥይት የተኮሰችበት በስህተት እንደሆነና ዋነኛ አላማዋ ማደንዘዣ መተኮስ እንደነበር ተናግራለች።
ግድያው የተፈፀመው ከሚኒያፖሊስ ወጣ ብላ በምትገኝ አካባቢ ሲሆን በባለፈው አመት ጆርጅ ፍሎይድ አንገቱን መሬት አጣብቆ የገደለው ፖሊስ የፍርድ ሂደትም የሚታይበት አካባቢ ነው።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የብሩክሊን ማዕከል ከንቲባ ማይክ ኤሊየት ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት ስራቸውን በለቀቁት የፖሊስ ኃላፊ ቦታ ለ19 አመት በሰራዊቱ ያገለገሉትን ቶኒ ግሩይንግን መሾማቸውን ነው።
በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ከስራቸው የለቀቁት የፖሊስ ኃላፊ ጋኖን ፖሊሷ ዳውንቴን የተኮሰችበት "በስህተት እንደሆነና" ሽጉጧንና የማደንዘዣ መሳሪያዋን በማሳሷቷ እንደሆነ ተናግረው ነበር።
"ኃላፊው ከስራቸው መልቀቃቸው መልካም ነገር ነው" ያሉት ከንቲባው ዳውንቴ ላይ የተኮሰችበት ፖሊስ እንዲሁ ከስራ መልቀቋ በተወሰነ መልኩ "በማህበረሰቡ መረጋጋትን እንደሚያመጣ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
ዳውንቴ ላይ የተኮሰችበት ፖሊስ እንዲሁም የፖሊስ ኃላፊው ከስራቸው መልቀቃቸውን ዜና በሚኒያፖሊስ ሳልቬሽን አርሚ የምግብ ማመላለሻ አስተባባሪ ሆና ለምትሰራው አምበር ያንግ የተቀላቀለ ስሜትን ፈጥሮባታል።
ምንም እንኳን ዜናው ቢያስደስታትም ከዚህ ፈጠን ብሎ ሊደረግ በተገባ ነበር ብላ ታምናለች።
ብሩክሊን ሴንተር ፖሊስ ቢሮ ውጭ ቆማ በፖሊሶቹ ድርጊት ምን ያህል እንደተንገበገበችና እንደተቆጨች ትናገራለች።
"ከስራዋ መባረር ነበረባት። ተኩሳ የገደለችው ፖሊስ እስከምትለቅ ሊጠበቅ አይገባም ነበር" ትላለች።
የፖሊስ ኃላፊውን አስመልክቶም "ለማህበረሰቡ ምንም ግድ የሚሰጠው ሰው አልነበረም። እንኳን ተሰናበተ" በማለት ታስረዳለች።
ዝናብና በረዶ እየደበደባቸው ተቃውሟቸውን ለማሰማት ከመጡት ውስጥ አንዷ ነች አምበር።












