ፍትሕ፡ ኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ሕጓን ማሻሻሏ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

የፍርድ ቤት ውሳኔ ማሳለፊያ መዶሻ

የፎቶው ባለመብት, MARK METCALFE

የግልግል ዳኝነት እና የእርቅ ሥርዓት አሰራር አዋጅ ባሳለፍነው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።

በኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሕግ ማዕቀፍ ያገኘው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነበር።

ይህ አዋጅ ተሻሽሎ የፀደቀው ከ65 ዓመታት በኋላ ነው።

ኢትዮጵያ እአአ በ1958 የወጣውን ዓለም አቀፉን የግልግል ዳኝነት ሕግ፣ ኒው ዮርክ ኮንቬንሽንን ከዓለም 162ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 33ኛ አገር በመሆን የፈረመችውም ባለፈው ዓመት ነበር። ።

የግልግል ዳኝነት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የመሳሰሉ አለመግባባቶችን የተከራካሪ ወገኖችን ሕጋዊ መብትና ጥቅም በጠበቀ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል አማራጭ የዳኝነት ሥርዓት ነው።

የግልግል ዳኝነት ከፍርድ ቤት አሰራር በምን ይለያል? አዋጁ መሻሻሉስ ምን ፋይዳ አለው? ኩባንያዎች የግልግል ዳኝነትን ለምን ተመራጭ ያደርጋሉ?

አቶ ሚካኤል ተሾመ አዋጁን በማርቀቁ ሂደት ምክክር ሲጀመር በመነሻ ረቂቅ ደረጃ (Zero Draft) ከተሳተፉ የሕግ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። "የግልግል ዳኝነት በኢትዮጵያ ሕግ" የሚል መጽሐፍም አቶ ሲራክ አካሉ ከተባሉ ሌላ የሕግ አዋቂ ጋር በመሆን ጥናት ሠርተው አሳትመዋል።

የኢትዮጵያ የማስማማትና የግልግል ዳኝነት ማዕከል ዳሬክተርም ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት የግልግል ዳኝነት አለመግባባትን መፍቻ ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታውም የጎላ ነው።

የግልግል ዳኝነት ከሌላው የፍርድ ቤት ክርክር በምን ይለያል?

የግልግል ዳኝነት ተከራካሪዎቹ ዳኞችን የመምረጥ፣ ውሳኔ የሚሰጥበትን ጊዜና ቦታ እንዲሁም የሚመራበትን ሕግ የመምረጥ፣ እንዲሁም ተቋማዊ ወይም ተቋም የሌለው እንዲሆን መወሰን የሚያስችል እንደሆነ አቶ ሚካኤል ይናገራሉ።

አቶ ሚካኤል እንደሚሉት በግልግል ዳኝነት የክርክሩን ሂደት የመወሰንና የመምራት መብትም የተከራካሪዎቹ ነው። ይህ ለተከራካሪዎቹ ነጻነት የሚሰጥ በመሆኑ ከፍርድ ቤት ይልቅ የግልግል ዳኝነትን ተመራጭ ያደርገዋል።

የግልግል ዳኝነት በሚቋቋምበት መንገድም ከፍርድ ቤት ይለያል።

ፍርድ ቤት የሚቋቋመው በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሲሆን የግልግሉ አሠራር የሚረቀቀው ግን በውል ነው። ተከራካሪዎቹ ወይም ባለጉዳዮቹ በአንድ አገር የግልግል ዳኝነት ሕግ ለመዳኘት ፈቅደው በተስማሙበት ውል ማለት ነው።

የይግባኝ አጠያየቅ ጉዳይም የፍርድ ቤትና የግልግል ዳኝነት የሚለዩበት ሌላኛው ነጥብ መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ።

በፍርድ ቤት ሥርዓት ማንኛውም ተከራካሪ የፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ይግባኝ የመጠየቅ መብት ያለው ሲሆን የግልግል ዳኝነት ላይ ግን ይህ ምርጫ ነው። ተከራካሪዎቹ ይግባኝ ማለት ከፈለጉ ይጠይቃሉ። ካልፈለጉም ይግባኝ አለማለት ይችላሉ።

ኩባንያዎች ከፍርድ ቤት ይልቅ የግልግል ዳኝነትን ለምን ይመርጣሉ?

በዓለማችን ትልልቅ የንግድ ተቋማትና ኩባንያዎች፣ ባለሃብቶች እና ዝነኞች የሚገጥማቸውን አለመግባባቶች ለመፍታት የግልግል ዳኝነትን ተመራጭ ሲያደርጉ ይስተዋላል።

ይህ ለምን እንደሆነ የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ሚካኤል፤ "ሚስጥራቸው የተጠበቀ እንዲሆን ስለሚያስችላቸው ብዙዎች የግልግል ዳኝነት ተመራጭ ያደርጉታል" ይላሉ።

ባለሙያው እንደሚሉት በዚህ ሥርዓት ከሚመለከታቸው ሰዎች ውጪ ሦስተኛ ወገን ገብቶ ዳኝነቱን መከታተል አይችሉም።

በፍርድ ቤት ሕግ ግን 'ልዩ' ከሆኑ ጉዳዮች ውጪ ማንኛውም ሰው ገብቶ ችሎቱን መከታተል ይችላል።

በመሆኑም የግልግል ዳኝነት ነጻነት የሚሰጥ በመሆኑ የውጪ አገር ባለሃብቶች አንድ አገር ሄደው መዋዕለ ንዋያቸውን ሲያፈሱ የሚገጥማቸውን ችግር ከፍርድ ቤት ይልቅ የግልግል ዳኝነት ይፈታልናል የሚል እምነት አላቸው ይላሉ- አቶ ሚካኤል።

በዚህ ሥርዓት ተከራካሪዎቹ ዳኞችን፣ የሚዳኙበትን ሕግ ፣ ውሳኔ የሚሰጥበትን መንገድ እና ተቋማዊ መሆን አለመሆኑን የመምረጥ ነጻነት አላቸው።

በሌላም በኩል የግልግል ዳኝነት ወጪ ቆጣቢ ነው ይባላል። ምንም እንኳን ይህ ብዙ አከራካሪ ሃሳብ ቢሆንም።

የፍርድ ቤት ሂደት የተራዘመ ጊዜ በመውሰዱ የተነሳ ለበዛ ወጪ ይዳርጋል የሚል እሳቤ አለ። በተቃራኒው የግልግል ዳኝነት መጀመሪያ ላይ ለዳኞቹና ሌሎች አስተዳዳራዊ ክፍያዎች የሚከፈለው ገንዘብ ከፍ ስለሚል ውድ ተደርጎ የሚታይበትም አግባብ አለ።

ቢሆንም ግን የግልግል ዳኝነት ሌሎች ጠቀሜታዎች ስላሉት በርካቶች ተመራጭ እንደሚያደርጉት አቶ ሚካኤል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በውጭ አገር የተሰጡ የግልግል ዳኝነት ማስፈጸም የሚረዳውንና እአአ በ1958 የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት (የኒው ዮርክ ኮንቬንሽን) ፈርማለች። ይህም በእንግሊዝኛው (Convention on the Recognition and Enforcement of Foreign Arbitral Awards) የሚባለው ነው።

በመሆኑም ሌላ አገር የተሰጠን የግልግል ዳኝነት ውሳኔ አገር ውስጥ በቀላሉ ማስፈፀም ይቻላል።

ሌላ አገር የተሰጠን የፍርድ ቤት ውሳኔ ግን ኢትዮጵያ መጥቶ ማስፈፀም አደጋች ነው።

"የፍትሃ ብሔር ሥነ ሥርዓትና ሕግ ጉዳይ፤ የሌላን አገር ውሳኔ እንዳይፈፀም የሚያደርግበት/የማያደርግበት የኢትዮጵያ ሕግ ሊኖር ይችላል" ይላሉ ባለሙያው።

የግልግል ዳኝነት ግን አፈጻጸሙ የሚገዛው በ1958 በወጣው የኒው ዮርክ ስምምነት በመሆኑ የትኛውም አገር ጉዳይን ማስፈፀም የሚያስችል ነው ይላሉ።

የኒው ዮርክ ስምምነት ሌላ አገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ፤ ባሉበት አገር ውስጥ እንዴት ይፈፀማል የሚለውን የሚያስረዳ አለም አቀፍ ስምምነት ነው።

ይህ ስምምነት በአፈፃፀም ደረጃ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው።

በአዲሱ ሕግ ምን ተካቷል?

ኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነትን በሕግ ማዕቀፍ ያስገባችው በ1952 ዓ.ም ሲሆን የተሻሻለው ከአስርት ዓመታት በኋላ ነው።

አቶ ሚካኤል ይህ ሕግ ከረዥም ጊዜ በኋላ ቢሻሻልም መሰረታዊ ነጥቦችን አካቷል ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት አዲሱ ሕግ ተቋም እንዲቋቋም ይፈቅዳል። በመሆኑም በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት የግልግል ዳኝነት ተቋም ማቋቋም ያስችላል።

ይህም ለተከራካሪዎች የበለጠ ነጻነት ይሰጣቸዋል ይላሉ -አቶ ሚካኤል። 'ተቋም መቋቋሙ ብቻ አይደለም ለተከራካሪዎች ነጻነትን የሚያጎናጽፈው። ለተከራካሪዎች ነጻነት የሚሰጠው በሕጉ ውስጥ የተካተቱት አንቀጾችና ድንጋጌዎች ናቸው።'

የግልግል ዳኝነት ሰፊና ውስብስብ ቢሆንም በሕግ ደረጃ የተደነገገው በጣም ቁንፅል ሃሳብ ነበር የሚሉት ባለሙያው፤ አሁን በተቋም ደረጃ መታሰቡ ጠንካራ ያደርገዋል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሌላ አካል ጣልቃ ገብነትን ማስቀረት እንደሚያስችል ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም በነበረው ሕግ ፍርድ ቤቶች በተለያየ መልኩ እየገቡ ዳኝነቱ እንዲቆም ፣ ዳኞች የሚመረጡበትን መንገድ የመወሰን ሥልጣን እንደነበራቸው የሚያስታውሱት ባለሙያው፤ የተሻሻለው ሕግ ግን ከፍርድ ቤቶች ይልቅ ለተከራካሪዎች የበለጠ ሥልጣን እንደሰጣቸው አስረድተዋል።

የግልግል ዳኝነቱ ዝርዝር ሃሳቦችን የያዘ ዘመናዊ ሕግ ሆኖ ነው የወጣው ሲሉም ያክላሉ።

ከዚህም ባሻገር በፊት ያልነበረና የንብረት እግድ እንዴት ሊፈፀም እንደሚችል፤ እንዲሁም ሦስተኛ ወገን መግባት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን በተመለከተም መልስ የሰጠ ሕግ እንደሆነ ተናግረዋል።

የግልግል ዳኝነት ፋይዳ ምንድን ነው?

ባለሃብቶች ወደ አንድ አገር ሄደው መስራትን ሲያስቡ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገባሉ። ሌጣ መሬት ስለተገኘ አሊያም ገንዘብ ስላለ ብቻ ገንዘባቸውን አያፈሱም። ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ የግብር ሕግ፣ የንግድ ሕግ ፣ የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ፣ የብሔራዊ ባንክ ሕግ እና ሌሎችን ሕጎች ያጤናሉ። ያሰራኛል ወይ ብለው ይጠይቃሉ።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የግልግል ዳኝነት ሕግ ነው። በሥራቸው አለመግባባት ቢገጥማቸው ባሉበት አገር ሆነው የሚዳኙበት ሥርዓት።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የኒው ዮርኩ ስምምነት አካል መሆኗ ለኢንቨስተሮች [ባለሃብቶች] በር ይከፍታል።

"ባለሃብቶች 'ከኢትዮጵያዊ ነጋዴ ጋር ተከራክረን ውሳኔ ቢወሰንልን እንኳን፤ በምን አግባብ? እንዴት አድርገን እናስፈፅማለን?' የሚለውን ነገር አያሰጋቸውም። " ይላሉ አቶ ሚካኤል።

ይሁን እንጅ በጥንቃቄ ካልተሰራበት የሚያስከፍለው ዋጋ እንዳለም ባለሙያው ይናገራሉ።

አቶ ሚካኤል እንደሚሉት ይህ የሚያጋጥመው በቸልተኝነት ውል ሲፈፀም ነው።

በመሆኑም ስምምነትን የሚያረቁ፣ የሚፈርሙ፣ በጉዳዩ ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች በሙሉ እያንዳንዱን ነገር ትኩረት ሰጥተው በጥንቃቄ ማየት አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።

"በየትኛውም አገር የኢትዮጵያን ኩባንያዎችን የሚወክሉ ባለሙያዎች ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው። ኮንትራቶችን በቸልተኝነት የሚፈረሙ ከሆነ፤ ዋጋ መክፈል አይቀርልንም" ብለዋል።