ንግድ፡ በኢትዮጵያ አንድ ግለሰብ ብቻውን ኩባንያ እንዲያቋቁም ተፈቀደ፤ አዲሱ የንግድ ሕግ ምን ይዟል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 16/2013 ዓ.ም ላለፉት 62 ዓመታት ሲያገለግል የቆየውን የአገሪቱን የንግድ ሕግ በመሻር በአዲስ እንዲተካ በሙሉ ድመጽ ወስኗል።
ይህን አዲሱ የንግድ ሕግ ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር በርካታ ለውጦች የተደረጉበት እንደሆነ ይነገራል። ለማዘጋጀትም ረጅም ጊዜ የወሰደና በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር።
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸውና አዋጁን በማርቀቅ ሂደት የተሳተፉት ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር) የሕጉ መውጣት የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴን በአወንታዊ መንገድ ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ይናገራሉ።
ባለሙያው የሕጉን መውጣት አስፈላጊነት ሲያስረዱ የሚጠቅሱት ላለፉት 62 ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ሕጉ ከወቅታዊው የዓለም ሁኔታ ጋር አለመሄዱን ነው።
"የንግድ ሕጉ በወጣበት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የኢንቨስትመንት፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አውድ የ1952ቷ እና የ2013ቷ ኢትዮጵያ በጣም የተለያዩ ናቸው" የሚሉት ታደሰ (ዶ/ር) ይህ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያ ለንግድ ከሚመቹ አገራት ዝርዝር ውስጥ በዝቅተኛ ደርጃ ላይ እንድትቀመጥ እንድርጓታል ሲሉ ገልጸዋል።
የዚህ ውጤት ደግሞ አገሪቱን በተለያየ መልክ ዋጋ አስከፍሏታል።
"ኢንቨስተሮች ይሄ አገር እንዴት ቀላል ነው? እንዴት ለንግድ አመቺ ነው? የሚሉትን ነገር ሰለሚያዩ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ኢንቨስመንት ይቀንሳል ማለት ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያለውን ካፒታል የመሳብ አቅሟንም በጣም አሳንሶታል" በማለት የሚያስርዱት ባለሙያው፤ ይህም የሥራ ፈጠራንና የውጭ ንግድን እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ዕድገቷን የሚገታ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በ1952 ዓ.ም የወጣውን ይህን ሕግ ለመቀየር ከ30 ዓመት በፊት ጀምሮ ጥረት ሲደረግ እንደቆየ ተገልጻል። 825 አንቀጾች ያሉት አዲሱ አዋጅ በርካታ ማሻሻያዎችን የያዘ ነው። ከእነዚህ ጥቂቶቹን እንመልከት።
አንድ ግለሰብ ለብቻው ኩባንያ መክፈት እንዲችል ተፈቅዷል
በቀድሞው የንግድ ሕግ መሠረት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ለማቋቋም ቢያንስ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ።
"ለምሳሌ የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርጉ አንድ ሌላ ሰው ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው። ይህ ብዙ ወጪ ነው የሚያስወጣቸው። ከፍተኛ ጥርጣሬም ይፈጥራል" ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
ከዚህም በላይ አብሮ ኩባንያውን የመሰረተውን ሰው ባለመስማማት ወይም በሞት ምክንያት ለመቀየር ሲፈለግ ያለውን ሒደት "አበሳ ነው" ሲሉ ከባድነቱን ይገልጹታል።
ይህም የኩባንያውን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና አላስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች የሚዳርግ ነው ሲሉም አክለዋል።
እንደ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በአገር ውስጥ ያሉ በርካታ ኃላፊነታቸው የተወሰኑ የግል ኩባንያዎች በተግባር የአንድ ሰው ሆነው ሳለ፤ ለሕጉ ሲባል ግን ተጨማሪ ሰው በባለቤትነት ይመዘግባሉ።
አዲሱ የንግድ ሕግ ይህን ግዴታ አንስቶ አንድ ግለሰብ ብቻውን ኩባንያን እንዲከፍት ፈቅዷል። ይህም ሰዎች በቀላሉ ወደ ሥራ እንዲገቡና ባለቤትነትን በተመለከተ ስጋት እንዳይኖራቸው ያግዛቸዋል ብለዋል።
የንግድ ትርጓሜን መቀየር
በተሻረው ሕግ የተዘረዘሩት የንግድ አይነቶች 21 ብቻ ናቸው። ከነዚህ ውጪ ያሉት ንግድ አይደሉም ተብለው እንደሚገመቱ ባለሙያው ያስረዳሉ።
አሁን ግን ሕጉ የንግድ አይነቶችን ወደ 38 አሳደጓቸዋል።
"ያም ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ሕግ የንግድ ትርጉም ክፍት ነው። በግልፅ ካልተከለከለ በስተቀር ማንኛውም ሰው ከፀሐይ በታች ባለን ሥራ ንግድ ነው፤ ያተርፋል ብሎ እንደሙያ የያዘውን ሥራ አስመዝገቦ መቀጠል ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ አዳዲስ የንግድ አይነቶችንና የፈጠራ ሐሳቦችን እንደሚያበርታታ አክለዋል።
ኃላፊነታቸው የተወሰኑ የሙያ ሽርክና ማኅበራት መፈቀድ
ከቀደመው ሕግ በተቃራኒው አዲስ የጸደቀው አዋጅ ግለሰቦች በሙያቸው ተደራጅተው እንዲሠሩ በግልጽ ድንጋጌ አስቀምጧል።
አዋጁን በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉት ከፍተኛ የሕግ አማካሪው፤ እያንዳንዱ ሙያ የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ይዘው ደንበኞቻቸውን የሚያስተናግዱ የሽርክና የሙያ ማኅበራት እንዲስፋፉ ያስችላል ብለዋል።
በሌላው ዓለም በስፋት የሚሠራበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሕግ በግልጽ ባለመፍቀዱ ዘርፉን አዳክሞታል።
በሌላ በኩል የቀድሞው ሕግ የአክስዮን ማኅበራት የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት ሁሉም የአክሲዮን ባለድርሻ እንዲሆኑ ግዴታ የጣለ ነበር።
ነገር ግን በአዲሱ ሕግ ባለድርሻ መሆን ሳይጠበቅባቸው፤ ባለ ድርሻ ያልሆኑ ሰዎች በሙያቸው እስከ አንድ ሦስተኛ ድረስ የሚሆነውን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ቦታን እንዲይዙ ይፈቃዳል።
በተጨማሪም ከተሻረው ሕግ በተቃራኒ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የሚከስሩ የንግድ ሰዎች ነጻ የሚሆኑበትን መንገድ እንዳመቻቸም ገልጸዋል።
የሕግ ባለሙያው ታደሰ (ዶ/ር) እነዚህን ጨምሮ ለንግድ እንቅስቃሴው የማይመቹ ሕጎችን ያሻሻለው የአዲሱ አዋጅ መውጣት "በአገር ውስጥ ያለውን እንቅሰቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል" ብለዋል።
በአዲሱ አዋጅ ያልተካተቱት የባንክ፣ የኢንሹራንስና፣ የማጓጓዣ ዘርፎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በቀድሞው አሠራር መሠረት የሚቀጥሉ ሲሆን፤ በቀጣይ ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲሱ የንግድ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ገብቶ የቀድሞውን ሕግ ይተካል ተብሎ ይጠበቃል።















