ኢትዮጵያ በቀንና በዓመት ምን ያህል የነዳጅ ምርት ትጠቀማለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት ጥቂት ቀናት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ምክንያት፣ በነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የመኪናዎች ወረፋ ታይቷል።
አሽከርካሪዎችም ነዳጅ ለመቅዳት በረጃጅም ሰልፎች ላይ ሆነው ሰዓታትን ለመጠበቅ በመገደዳቸው በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ ሰንብቷል።
ለወትሮ እንዲህ አይነት ነዳጅ ለማግኘት ሰልፎች ይታዩ የነበረው በወራት ማብቂያ ላይ፣ የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ከሚደረግባቸው ቀናት ቀደም ብሎ የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ ግን ከዚያ የተለየ ነበር።
ባለፉት ቀናት የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት በተመለከተ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመንግሥት በኩል ግልጽ ምክንያት ባይሰጥም በአቅርቦት ሥርዓቱ ውስጥ ባጋጠመ ችግር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ኢትዮጵያ ከዓመታዊ በጀቷ ውስጥ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ መድባ በምታስገባው ነዳጅ ላይ እጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ፣ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የራሱ የሆነ ጫና ያሳድራል።
የኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች ፍላጎት ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንደሚሄድ የተነገረ ሲሆን፣ የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው የዛሬ 10 ዓመት፣ ማለትም በ2003 ዓ.ም፣ አገሪቱ ለነዳጅ ምርቶች አውጥታው የነበረው ገንዘብ በወቅቱ በነበረው የምንዛሪ ዋጋ መሠረት 22.8 ቢሊዮን ብር ነበር።
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የተሽከርካሪዎች ቁጥርና ነዳጅን የሚጠቀሙ ተቋማትና ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ የተነሳ፣ ለነዳጅ ምርቶች የወጣው ገንዘብ ሁለት ዕጥፍ ያህል ከፍ ብሎ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ 62.05 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ኢትዮጵያ ነዳጅ ከየት ታገኛለች?
ኢትዮጵያ ለፍጆታዋ የሚውለውን ነዳጅ ከተለያዩ ነዳጅ አምራች አገራት የምታስገባ ሲሆን፣ በዋናነት ከመካከለኛው ምሥራቅና የባሕረ ሰላጤው አገራት ታገኛለች።
በዚህም መሠረት በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የነዳጅ ዘይት ከሳዑዲ አረቢያ እና ከኩዌት በማስመጣት ላይ እንደምትገኝ የነዳጅ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንደሚለው በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገባበት ብቸኛው መንገድ በጂቡቲ ወደብ በኩል ባለው መስመር ነው።
ስለዚህም በየወሩ እስከ አምስት በሚደርሱ ግዙፍ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች አማካኝነት፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ነዳጅ ወደ ጂቡቲ ወደብ እንደሚጓጓዝ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከጎረቤት አገር ሱዳን፣ ለሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከሚያስፈልገው አቅርቦት ውስጥ የተወሰነውን ስታስገባ የቆየች ሲሆን ከኮሮናቫይረስ መከሰት በኋላ ባለፈው ዓመት አቅርቦቱ ተቋርጧል።

የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ?
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ኃይለማርያም፣ ለአገሪቱ 2.5 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እና 8 ሚሊየን ሊትር ናፍጣ በቀን እንደሚቀርብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንንም ለማሟላት በየዓመቱ ለአገሪቱ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የነዳጅ መጠን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን፣ ድርጅታቸው ለአገሪቱ በዓመት ምን ያህል ነዳጅ ያስፈልጋል የሚለውን ያቅዳል።
ኢትዮጵያ ወደ አገር ቤት የምታስገባቸው ነዳጆች አምስት ዓይነት ናቸው። እነዚህም ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅና ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ሁለት ዓይነት ናፋጣዎች ናቸው።
በዚህም መሠረት ቤንዚን በዓመት እስከ 700 ሺህ ሜትሪክ ቶን፣ 2.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ናፍጣ፣ 600 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅና እስከ 70 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተለያየ አይነት የኢንዱስትሪ ናፍጣ በየዓመቱ እንደሚገባ የድርጅቱ ኃላፊ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በበጋዎቹ ከታኅሣሥ እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ውስጥ ከሌለው ጊዜ በበለጠ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ምርት ጥቅም ይውላል።
"ምክንያቱ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በስፋት የሚከናወኑበት ወቅት በመሆኑ ነው። ነገር ግን በክረምት ወራት ፍጆታው ይቀንሳል" ይላሉ አቶ ታደሰ።
አገሪቱ በዓመት ውስጥ ያስፈልገኛል ብላ ካቀደችው የነዳጅ ፍጆታ ውስጥ አፈጻጸሙ ሲታይ ብዙም ልዩነት እንደሌለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ልዩነት የሚመጣ ከሆነም ከሚያስፈልገው "በ10 በመቶ ይጨምራል ወይም ከፍ ይላል እንጂ ብዙ ልዩነት አይመጣም" በማለት ይናገራሉ። በምሳሌነት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴው በመቀዛቀዙ የአውሮፕላን ነዳጅ አምና ከታቀደው ፍላጎት በ50 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
በተጨማሪም ናፍጣ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ካቀደው ጋር ሲነፃፀር ፍላጎቱ በ4 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፤ የቤንዚን ፍላጎት ግን በ13 በመቶ መጨመሩን ይናገራሉ።

ችግር ቢፈጠር ምን አማራጭ አለ?
በየዕለቱ በርካታ የነዳጅ ዘይት ማመላለሻ ግዙፍ ቦቴዎች በመላው አገሪቱ የሚያስፈልገው የነዳጅ አቅርቦት እንዳይጓደል ከጂቡቲ ምርቶችን ያጓጉዛሉ። በዚህም ከወደብ እስከ መድረሻቸው በመቶዎቹ ሲልም ሺህ ኪሎ ሜትሮች እየተጓዙ ነዳጅ ያቀርባሉ።
አቶ ታደሰ እንደሚሉት ነዳጅ ወደብ መድረሱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ነገር ወደ ሚፈለግበት ቦታ ደርሶ ጥቅም ላይ መዋሉ ነው። በዚህ የአቅርቦት ሥርዓት ውስጥ ብዙ ባለድርሻዎች ያሉ ሲሆን የተለያዩ እንቅፋቶችም ሊያጋጥሙ ይችላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ የአቅርቦት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ መሰናክሎች የነዳጅ እጥረት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህና ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተፈጥረው የነዳጅ አቅርቦት መስመሩ የመስተጓጎል ሁኔታ ቢፈጠር በሚል ድርጅቱ ሌላ አማራጭን ማዘጋጀቱን ይናጋራሉ።
ለዚህም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ችግር በሚያጋጥም ጊዜ የሚያስፈልገውን የነዳጅ አቅርቦት ለማሟላት ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች ውስጥ ያለውን መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።
ይህ የመጠባበቂያ ነዳጅ አቅርቦት ለሳምንታት የሚሆን አቅርቦትን የያዘ ሲሆን፤ ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆን የነዳጅ ክምችት ስላለ በአንድ ምክንያት ከወደብ አገር ውስጥ ነዳጅ በማይገባባቸው ቀናት ውስጥ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ይቻላል ብለዋል።
የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓቱ
የነዳጅ ምርቶች ከወደብ ተነስተው ተጠቃሚው ጋር እስኪደርሱ ድረስ ያለው ሂደት ውስብስብ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ታደሰ፤ ይህም በየጊዜው ለሚያጋጥመው የአቅርቦት ችግር አንዱ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
የነዳጅ ምርቶችን "በጣም ረዥም ርቀትን በከባድ የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች ነው የሚጓጓዙት። አንዳንዴ እስከ ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትሮች ድረስ ነው ነዳጅ ተጓጉዞ ለተጠቃሚው የሚደርሰው" ይህ ሂደት ለውጥ ያስፈልገዋል ይላሉ።
የመጓጓዣ ወጪውና የሚፈጀው የጉዞ ቀናት በአቅርቦቱ ላይ የራሱ ተጽእኖ ይኖረዋል። ከዚህ ውጪ ሌሎች አገራት ነዳጅን ለማጓጓዝ ረከስ ያሉና ፈጣን አማራጮችን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል።
አቶ ታደሰም ነዳጅ ከወደብ አስከ መሃል አገር ወይም አስከ ማከማቻ ዴፖዎች ርካሽ በሆኑት ቱቦዎች አሊያም በባቡር ሊጓጓዝ እንደሚገባ ይመክራሉ።
በተጨማሪም የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ መረጃ በቀላሉ ለማግኘትና አቅርቦቱን ለማፋጠን በቴክኖሎጂ ቢታገዝ የተሻለ ቅልጥፍና ሊኖር ይችላል።
"ለምሳሌ ነዳጅ የያዘ መኪና የት እንዳለ ማንም አያውቅም። በስልክ ተደውሎ ነው የት ደርሳችኋል? የሚባለው። ነገር ግን እንደ ጂፒኤስ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቢቻል" ይላሉ።
ይህም በአቅርቦት መስመሮች ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ቀድሞ ለመለየትና አስፈላጊውን ማስተካከያና የአቅርቦት አማራጭ ለማመቻቸት እንደሚረዳ ይታመናል።















