ኬንያ የነዳጅ ድፍድፍ ወደ ውጭ መላክ ጀመረች

ትናንት ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ለኬንያ ታሪካዊ ቀን ሆኖ አልፏል።
ኬንያ የመጀመሪያውን የነዳጅ ድፍድፍ ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በተገኙበትም የነዳጅ ድፍድፍ የጫነችው መርከብ ከሞምባሳ ወደብ ተሸኝታለች። ዕለቱም ለምስራቅ አፍሪካ የነዳጅ ልማት ዘርፍ ትልቅ እርምጃ ነው ተብሏል።
የነዳጅ ድፍድፍ መላኩን የሙከራ ወቅት የተባለ ሲሆን የተጣሩ የነዳጅ ምርቶችን ከአምስት አመታት በኋላ ወደ ውጭ የመላክ እቅድን ይዛለች።
ተቀማጭነቱን እንግሊዝ አገር ያደረገው የቻይና ኩባንያ 'ኬምቻይና ዩ ኬ ሊሚትድ' የመጀመሪያውን 240 ሺህ በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ለመግዛት ጨረታውን አሸንፏል።

የእስያና የአውሮፓ ድርጅቶች በጨረታው ላይ የተሳተፉ ሲሆን በቱሎው ኦይል የሚመራው የነዳጅ አምራች ጥምረት ኮንትራቱን ለኬም ቻይና ካምፓኒ ሰጥቶታል።
ለጊዜው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የሌላት ኬንያ፤ ድፍድፍ ነዳጁ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ቱርካና ከሚገኘው የነዳጅ ማውጫ ቦታ 850 ኪሎሜትር በተሽከርካሪ ተጉዞ ነበር ሞምባሳ የደረሰው።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦውን ለመዘርጋት ከኡጋንዳ ጋር ይዛው የነበረው እቅድ፤ ኡጋንዳ ከታንዛኒያ ጋር ውል በመጀመሯ ሳይሳካላት ቀርቷል።
ኬንያ በመጭው ሁለት ዓመታት ከነዳጅ ከ84 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች ተብሎም ይጠበቃል።
እንደ ቱሎው ካምፓኒ ከሆነ በኬንያ ቱርካና በሚገኘው የነዳጅ ማውጫ ቦታ 560 ሚሊየን በርሜል የነዳጅ ክምችት የሚገኝ ሲሆን ከአውሮፓዊያኑ 2022 ጀምሮ በየቀኑ 100 ሺህ በርሜል ነዳጅ ያመርታል ተብሎ ይገመታል።














