የቀድሞው የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት በአብዮተኛው ሳንካራ ግድያ ሊከሰሱ ነው

ቶማስ ሳንካራ

የፎቶው ባለመብት, Alain MINGAM

የቀድሞው የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ብሌይዝ ኮምፓዎሬ በብዙዎች ዘንድ ቀጥተኛ አብዮተኛ ተብሎ በሚጠራው ቶማስ ሳንካራ ግድያ ሊከሰሱ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1987 ከስልጣን የተወገደውና የተገደለው ቶማስ ሳንካራ ግድያ እንደሚጠየቁ ያስታወቀው ወታደራዊው ፍርድ ቤት ነው።

ቡርኪናፋሶን ለአመታት ያስተዳደሩት ኮምፓዎሬ የስልጣናቸውን ዘመናቸውን ለማስረዘም ያደረጉትን ሙከራ ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2014 ለግዞት ተዳርገዋል።

በቀጣዩ አመትም የእስር ትዕዛዝ ወጣባቸው።

ወታደራዊው ፍርድ ቤት በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እንዳስታወቀው የቀድሞው ፕሬዚዳንት "በመንግሥታዊ ደህንነት ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ ግድያን በማቀነባበርና አስከሬን በመደበቅ ወንጀል" ክስ ይጠየቃሉ ብሏል።

ከቀድሞው ፕሬዚዳንት በተጨማሪ ሌሎች 13 ሰዎችም በቶማስ ሳንካራ ግድያ እንደሚጠየቁ ተዘግቧል።

የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸውና በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ለማምጣት ማክሰኞ እለት ትዕዛዝ እንደተላለፈ ከተከሳሾቹ መካከል የአንደኛው ጠበቃ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ለአራት አመታት ያህል ብቻ በስልጣን ላይ የቆዩት አብዮተኛው ሳንካራ የአፍሪካ "ቼ ጉቬራ" ተብለው ይጠራሉ።

አብዮተኛው መሪ ሳንካራ ጭቆናን አጥብቀው የሚጠየፉ፣ ለድሆች፣ ሴቶችን ጨምሮ መዋቅራዊ ጭቆና አለባቸው ብለው ለሚያምኗቸው ህዝቦች እኩልነትን የሚያቀነቅኑ፣ ቅኝ ገዥዎችንና ኢምፔሪያሊዝምን የሚቃወሙ፣ ህዝብ ለመብቱ እንዲነሳ ታግለው ያታገሉ እንደነበሩ ታሪክ ይዘክራቸዋል።

ይኼም ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያን በብድር ስም አፍሪካውያንን ይበዘብዛሉ በማለት የአለም ባንክና የአለም ገንዘብ ድርጅትን አጥብቀው በመተቸታቸው በምዕራባውያኑ ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።