አሜሪካ ወታደሮቿን ከኢራቅ ታስወጣለች የተባለው 'ስህተት ነው' አለች

በኢራቅ ከ5000 በላይ አሜሪካውያን ወታሮች ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በኢራቅ ከ5000 በላይ አሜሪካውያን ወታሮች ይገኛሉ።

የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ማርክ እስፔር አሜሪካ ወታደሮቿን ከኢራቅ ታስወጣለች መባሉ ሐሰት ነው አሉ።

መከላከያ ሚንስትሩ ይህን ያሉት በኢራቅ የአሜሪካ ወታደሮች አመራር የሆኑት የጦር ጀነራል፤ ለኢራቅ መከላከያ ሚንስትር አሜሪካ በኢራቅ የሚገኙ ወታደሯቿን ታስወጣለች የሚል ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ ነው።

መከላከያ ሚንስትሩ ማርክ ስፔንሰር "በምንም ዓይነት ሁኔታ ኢራቅን ለቅቆ የመውጣት ውሳኔ የለም" ብለዋል።

አሜሪካ ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒን በኢራቅ ከገደለች በኋላ የኢራቅ ፓርላማ በአገራቸው የሚገኙ የውጪ ሃገራት ወታደሮች እንዲወጡ በአብላጫ ድምጽ ወስኖ ነበር።

የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛ ምስራቅ አሜሪካ ጠል እንቀስቃሴዎች እና ዛቻዎች ተበራክተዋል።

አሜሪካም በቀጠናው የሚገኙ ዲፕሎማቶቿን እና የአጋሮቿን ደህንነት ለማጠናከር ተጨማሪ 3000 ወታደሮች እንደምትልክ ማስታወቋ ይታወሳል።

የደብዳቤው ይዘት ምን ነበር?

ደብዳቤው የተላከው ለአብዱል አሚር፤ በኢራቅ የጥምር ጦር ኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ሲሆን፣ በኢራቅ የአሜሪካ ጦር አዛዥ የሆኑት የብርጋዴር ጀነራል ዊሊያም ኤች ሴለይ ስም አርፎበታል።

ደብዳቤው አሜሪካ የኢራቅ የሕዝብ እንደራሴዎች ውሳኔን እና የኢራቅ ጠቅላይ ሚንስትር ጥሪን ተከትሎ፤ ጦሯን በሚመጡት ጥቂት ቀናት ውስጥ ማንቀሳቀስ እንደምትጀምር አሳውቀዋል።

ብ/ጀነራሉ ጦራቸውን ሲያንቀሳቅሱ የባግዳድ ከተማን ነዋሪዎችን ላለመረበሽ እንቅስቃሴያቸውበምሽት እንደሚሆኑ ጨምሮ ዝርዝር መረጃዎችን በደብዳቤያቸው ላይ አስፈረዋል።

ዋሽንግተን የሚገኙት የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትሩ ግን፤ "ኢራቅን ለቅቆ ለመውጣት ምንም አይነት ውሳኔ የለም። ስለተባለው ደብዳቤ የማውቀው ነገር የለም . . . ይህ ደብዳቤ ከየት እንደመጣና ለምን እንዳስፈለገ እያጣራን ነው" ብለዋል።

የመከላከያ ሚንስትሩ ይህን ካሉ በኋላ ሌላው የጦሩ ከፍተኛ አዛዥ ማርክ ማይሊ ለጋዜጠኞች ደብዳቤው 'ስህተት ነው' ብለውታል።

ይህ የጦር አዛዥ "ደብዳቤው ገና በረቂቅ ላይ የነበረና በአሳሳች ቃላት የተሞላ ነው። ወጪ መደረግ አልነበረበትም። ቁልፍ የሆኑ የኢራቅ ጦር አባላት አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ነበር ወጪ የተደረገው" ብለዋል።

ማርክ ማይሊ፤ "በስፍራው በከፍተኛ ወጪ የገነባነው የተራቀቀ የጦር ካምፕ አለን። በብሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ ተደርጎበታል። ይህን መልሰው ካልከፍሉን ጥለን አንወጣም" ሲሉም ተደምጠዋል።

Presentational grey line

በአሁኑ ሰዓት በኢራቅ አይኤስን ለመዋጋት ወደ ኢራቅ የተሰማሩ ከ5000 በላይ የአሜሪካ ወታደሮች ይገኛሉ። ከአሜሪካውያኑ በተጨማሪ የሌሎች የምዕራባውያን ሃገራት ወታደሮች በኢራቅ ይገኛሉ።

ይህ የጥምር ኃይል አይኤስ ላይ ድል ከተቀናጀ በኋላ የምዕራባውያኑ ጦር ዋና ዓላማ ለኢራቅ ጦር ስልጠና እና የቁስ ድጋፍ ማድረግ ነበር።