ትራምፕ ኢራቅ አይታ የማታወቀው ማዕቀብ ይጠብቃታል ሲሉ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ የኢራቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሜሪካ ወታደሮች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ የሚወስን ከሆነ ከባድ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስጠነቀቁ።
" እጅግ ውድና ግዙፍ የሆነ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር [በኢራቅ] አለን። ለመገንባት ቢሊየን ዶላሮች አፍስሰንበታል። እስካልከፈሉን ድረስ ለቅቀን አንወጣም" በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አሜሪካ ኢራናዊውን የጦር አበጋዝ ከገደለች በኋላ በቀጠናው ውጥረት ነግሰዋል።
ኢራን የጄነራሏን መገደል "እበቀላለሁ" ስትል የዛተች ሲሆን እኤአ በ2015 ለፈረመችው የኒውክሌር ስምምነት እንደማትገዛም አስታውቃለች።
የ62 ዓመቱ ሶሌይማኒ ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን የጦር እንቅስቃሴ በበላይነት ይመሩ ነበር። አሜሪካ ለዚህ ተግባራቸው 'አሸባሪ' የሚል ስያሜ ሰጥታቸው ስትከታተላቸው መኖሯ ተዘግቧል።
የጄነራሉ አስክሬን ወደ ኢራን የተወሰደ ሲሆን፣ በመገደላቸው የተቆጡና ሀዘናቸውን ለመግለጽ የወጡ ኢራናውያን የቴህራንን ጎዳናዎች አጨናንቀውት ታይተዋል።
አዲሱ ጄነራሉን ተክተው የተሾሙት ግለሰብ፣ ኢስማኤል ቃኒ፣ አሜሪካን ከመካከለኛው ምስራቅ ጠራርገን እናስወጣታለን ሲሉ ዝተዋል።
በሀገሪቱ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ቀርበው " ሶሌይማኒ የጀመረውን ለማስቀጠል ቃል እንገባለን። ለኛ ካሳ የሚሆነው አሜሪካ ተጠራርጋ ከመካከለኛው ምስራቅ ስትወጣ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ሶሌይማኒን የገደለው የአየር ጥቃት ኢራቃዊው ጦር ጄነራልንን፣ አቡ ማህዲ አል ሙሀንዲስ፣ ገድሏል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአውሮፕላናቸው ውስጥ ሆነው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኢራቅ ከሀገሯ እንድንወጣ ከጠየቀች፣" አይተውት በማያውቁት መጠን ማዕቀብ እንጥልባቸዋለን። የኢራናውያኑ ማዕቀብ ምን አለውና" ብለዋል።
አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ 5000 ወታደሮች ያሏት ሲሆን ከኢራቅ ጦር ጋር በጋራ በመሆን አይኤስን ሲዋጉ ነበር።
እሁድ እለት ጥምር ጦሩ እንቅስቃሴውን ለጊዜው ያቋረጠ ሲሆን የኢራቅ ህዝብ እንደራሴዎች የውጪ ኃይሎች ሀገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ህግ አርቅቀው ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ኢራን በትናንትናው እለት ባወጣችው የአቋም መግለጫ እኤአ በ2015 የለፈረመችው የኑውክለር ስምምነት እንደማትገዛ ገልጻ፣ እንዳሻት እንደምትንቀሳቀስ አስታወቃለች።
የኢራን ካቢኔ ዋና ከተማዋ ቴህራን ላይ ከመከረ በኋላ ነው አቋሙ የወጣው።













